Thursday, December 20, 2012

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ም/ቤት ጠቅላላ ጉባኤ በዋሺንግተን ዲሲ


ኢትዮጵያ ብሄራዊ ሽግግር ም/ቤት ጠቅላላ ጉባኤ በዋሽንግተን ዲሲ በፊታችን የካቲት (ፌብሪዋሪ) ወር ይከናወናል
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ም/ቤት ላለፉት ስድስት ወራት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያከናዉን ቆይቷል። ከም/ቤቱ ምስረታ በኋላ የአካባቢ ምክር ቤቶችን (ቻፕተሮችን) በተለያዩ አገሮች በማቋቋም፤ ድርጅታዊ አቅምን በማጎልበት፤ የትግል ሂደት አቅጣጫን በመቀየስ፤ ከሌሎች ድርጅቶች ጋረ ትብብር በመፍጠርና እንዲሁም አቅሙንና የትኩረት አቅጣጫውን ኢትዮጵያ ውስጥ በማድረግ በርካታ ስራዎችን አከናውኗል። የም/ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ በዳላስ ቴክሳስ የምስረታ ስብሰባው ላይ በወሰነው መሰረት የስድስት ወራቱን የስራ እንቅስቃሴ ለመገምገምና ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ቀጣይ እቅዶችን ለመንደፍ በአሜሪካን ዋና ከተማ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ጽ/ቤቱ ከፌብርዋሪ 22 እስከ 24 ቀን 2013 እኤአ ያካሂዳል። በተለያዩ ሀገሮችና ከተማዎች ቀደም ብለው የተቋቋሙና በመቋቋም ላይ ያሉ የአካባቢ ምክርቤቶች (ቻፕተሮች) ተወካዮች በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ይሳተፋሉ። ስብሰባውም በስድስት ወራቱ ውስጥ የታዩትን ጠንካራና ደካማ ጎኖች በመገምገም የሚቀጥሉት ስድስት ወራት አካሄድን በተመለከተ የተለያዩ የፖሊሲና የተግባር ውሳኔዎችን ያስተላልፋል። በስብሰባውም መዝጊያ ዕለት በፌብርዋሪ 24 ቀን 2013 (እኤአ) ህዝባዊ ስብሰባ በማዘጋጀት በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይና መወሰድ ስለሚገባቸው ፈጣን እርምጃዎች ህዝባዊ ውይይት ያደርጋል። በዚህ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን ሁሉ እንዲገኙ እየጋበዝን ወደፊት ስለስብሰባው ቦታና ፕሮግራም ዝርዝር መረጃዎችን የምናወጣ መሆኑን እንገልጻለን።
የሽግግር ም/ቤቱ አመራር

No comments:

Post a Comment