Wednesday, December 26, 2012
በምርጫው መሳተፍ ገዥው ፓርቲን እንደማጀብ ነው፡፡
ኢሕአዴግ ውጤቱ አወዛጋቢ በነበረው ምርጫ 97 ቀጥሎ በርካታ አፋኝ ሕጎች በማውጣት የፖለቲካ ምህዋሩ እንዳያፈናፍን አድርጎታል ፡፡ ከዚህ ባልተናነሰ ግን በ2000 ዓ.ም. በተካሄደው የአካባቢ ምርጫ የተመራጮችን ቁጥር ከፍ እንዲል በማድረግና ተቃዋሚዎችን በማዋከብ የአካባቢ መስተዳደር ምክር ቤቶች ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ለማድረግ ሠርቷል፡፡
በመሆኑም ሁለት ዓመት ዘግይቶ በ2002 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ከፓርላማው ጠቅላላ መቀመጫዎች 99.6 በመቶ የሚሆነው እንዲያገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጎለታል ተብሎ ይታመናል፡፡ በተቃራኒው በአካባቢ አስተዳደሮች ምንም ቦታ ያልነበራቸው ተቃዋሚዎች፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ገብተው ተፅዕኖ ለመፍጠርና ለመቀስቀስ ሳይችሉ ቀርተው ከጨዋታ ውጪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በመጪው ሚያዝያ ወር የአካባቢና የአዲስ አበባ መስተዳደር ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ነች፡፡ ባለፉት አራት የአካባቢ ምርጫዎች ዋነኛ ተቃዋሚዎች ራሳቸውን ከምርጫ ማግለላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት በሒደቱ ለመሳተፍ ፍላጎት አጥተው ነው በሚል መንግሥት ይተቻቸዋል፡፡
የአካባቢ ምርጫ እንደ ዋነኛው አገራዊ ምርጫ የመንግሥት ሥልጣን የሚቆጣጠሩበት ባይሆንም፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ለማሳደር የቀበሌና የወረዳ መስተዳደሮች መቆጣጠር እጅግ ጠቃሚ መሆኑን በምርጫዎች ላይ ጥናት የሚያደርጉ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡
ሒደቱ እጅግ አስፈላጊ የሚሆንባቸው በርካታ ምክንያቶች ሲኖሩ፣ በቀዳሚነት የሚነሳው ግን የኅብረተሰቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ ከዋነኛው ምርጫ በበለጠ ሁኔታ የሚያረጋግጥ መሆኑ ነው፡፡
የተቃዋሚዎች ቀልብ እስከምን?
የመጀመርያውን የ1987 ዓ.ም. ምርጫን ጨምሮ እስካሁን በተካሄዱት የአካባቢ ምርጫዎች ዋነኛ ተቃዋሚዎች እምብዛም የሚሳተፉበት አልነበረም፡፡ የምርጫ 97 አወዛጋቢ ውጤትን ተከትሎ በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ከአንድ ዓመት በላይ ዘግይቶ በ2000 ዓ.ም. በተካሄደው የአካባቢ ምርጫም፣ በወቅቱ ከነበሩት ዋነኛ ተቃዋሚዎች መካከል ኦፌዴንና ኅብረት መንግሥት በአባሎቻቸው ፈጸመብን ባሉት ወከባና በአንዳንድ አለመግባባቶች ምክንያት በመጨረሻው ሰዓት ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል፡፡
በወቅቱ ከሌሎች ተቃዋሚዎች በተለየ ሁኔታ ‹‹ሦስተኛ አማራጭ›› በሚል የፖለቲካ አቋም ሲያራምድ የነበረው የኤዴፓ ፕሬዚዳንት ከሃዲው አቶ ልደቱ አያሌው ግን፣ ለዲሞክራሲያዊ ሒደቱ ክብር ሲባል ፓርቲያቸው መወዳደሩን ነበር የተናገሩት፡፡
መጪውን የአካባቢ ምርጫ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ የተቃወሙ 33 የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ኮሚቴ መሥርተው አቤቱታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ምርጫ ቦርድ ማስረጃ አልቀረበባቸውም በማለት ጥያቄያቸውን ሳይቀበል ቀርቷል፡፡ ጊዜያዊው የጋራ ኮሚቴ በበኩሉ ቦርዱ አሁንም የገዥውን ፓርቲ ፍላጎት ብቻ እያገለገለ ነው በማለት የቦርዱን ምላሽ ተቃውሟል፡፡
በሚያዝያው የአካባቢ ምርጫ ይሳተፉ እንደሆን ወይም ራሳቸውን ከሒደቱ ያገልሉ እንደሆነ ኮሚቴው ለቀረበለት ጥያቄ ግን ቁርጥ ያለ ምላሽ የለውም፡፡ ውዝግቡ ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲና ምርጫ ቦርድ ተቃዋሚዎች በአካባቢ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት የሌላቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የማይገኝበት በመሆኑ በሚል ምክንያት የሚያቀርቡዋቸው ቅሬታዎችም ለእንቢተኝነታቸው እንደ ሽፋን እየተጠቀሙበት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ መድረክና መኢአድ የሚገኙበት የተቃዋሚዎች የጋራ ኮሚቴ ግን ለዚህ የአካባቢ ምርጫ ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጥና በቅድመ ሁኔታነት ያስቀመጣቸው ቅሬታዎች መፍትሔ እንዲያገኙ ይፈልጋል፡፡
የአካባቢ ምርጫ - አዲስ መልክ
ከምርጫ 97 በፊት ሲካሄዱ የነበሩ የአካባቢ ምርጫዎች ዋናውን ብሔራዊ ምርጫ ተከትለው የሚካሄዱ በመሆናቸው ብዙም የተለየ ውጤት የሚጠበቅባቸው አልነበሩም፡፡ በመጪው ሚያዝያ ወር ለሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ የተለየ ጉልበት የሚሰጠው ግን ለአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤትም ምርጫ የሚደረግ በመሆኑ ነው፡፡ በምርጫ 97 ከአንድ መቀመጫ በስተቀር የከተማውን ምክር ቤት አጠቃላይ መቀመጫዎቹ ያሸነፈው ቅንጅት፣ በምርጫው ውዝግብ ምክንያት የከተማውን አስተዳዳር ያልተረከበ በመሆኑ፣ ለሁለት ዓመታት በባለአደራ አስተዳደር ከቆየ በኋላ በድጋሚ ምርጫ የተደረገው ከዚሁ ከአካባቢ ምርጫ በተመሳሳይ ጊዜ ነበር፡፡
የቀበሌና የወረዳ ምክር ቤቶች በ10 እና በ12 አባላት የሚወከል የነበረ ቢሆንም፣ በ2000 ዓ.ም. አንድ ምክር ቤት ወደ 300 አባላት እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ በአጠቃላይም በአገሪቱ እስከ 3.6 ሚሊዮን አባላት ይፈለጉ ነበር፡፡ መንግሥት የምክር ቤቶቹ አባላት ቁጥር ማነስ የኅብረተሰቡን ፍላጎት እንዳይረዱና አፋጣኝ ምላሽ እንዳይሰጡ ምክንያት ሆኗል በሚል የምክር ቤቶቹ ቁጥር የጨመረ ቢሆንም፣ ተቃዋሚዎች ይኼንን ዕርምጃ ሆን ተብሎ እነሱን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ የተደረገ ተግባር መሆኑን ቅሬታ ያሰማሉ፡፡ አሁንም ከምርጫው በፊት መፈታት አለባቸው በሚል 33 የፖለቲካ ፓርቲዎች ካቀረቡባቸው አሥራ ስምንት አቤቱታዎች በተጨማሪ ለምክር ቤቶቹ የሚወዳደሩ አባላት ቁጥር እንዲቀንስ ይጠይቃሉ፡፡
ኢሕአዴግ በቅርቡ በጠራው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ዋነኛ አጀንዳም የአዲስ አበባ መስተዳደር ምክር ቤት ምርጫ እንደነበረ ይነገራል፡፡ በከተማዋ በተንሰራፋው ከፍተኛ ሙስናና ኔትወርኪንግ ከፍተኛ ኃላፊዎች ከኃላፊነት እንዲባረሩ መነሻ የሆነው የኢሕአዴግ የአዲስ አበባ ጽሕፈት ቤት ግምገማ ምን ዓይነት ውጤት እንዳመጣ፣ በከተማዋ ያለውን የኑሮ ሁኔታና የሕዝቡ አዝማሚያም ገዥው ፓርቲ ገምግሟል፡፡ ምርጫውን ለማሸነፍም ስትራቴጂ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን እየተነገረ ነው፡፡
ከምርጫው ራሳቸውን የማግለል አዝማሚያ እያሳዩ ያሉት ዋነኛ ተቃዋሚዎችም መወሰን ያቃታቸው ይመስላል፡፡ ገዥው ፓርቲ ትልቅ አጀንዳ አድርጎ እየመከረበት ያለውን የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤት ምርጫን ጥለው መውጣት የፈለጉ አይመስልም፡፡ ለምርጫ ቦርድና ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያቀረቡዋቸው እንደ ቅድመ ሁኔታዎች እየተቆጠሩ ያሉት ቅሬታዎች ሳይመለሱላቸው በምርጫው መሳተፍ ደግሞ ገዥው ፓርቲን እንደማጀብ እየቆጠሩት ነው፡፡
የፓርላማና የአካባቢ ምርጫ ትስስር
ቢያንስ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ዲሞክራሲያዊ ነን የሚሉ በርካታ አገሮች ዘመናዊውንና በስፋት የሚተገበረው የውክልና ዲሞክራሲ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች በአንድ ሰው የሚወከሉበት ፓርላሜንታዊ ሥርዓት ነው፡፡
ይኼው አካል በእኛ አገር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመባል የሚታወቀው ሲሆን፣ የአገሪቱ ሕግ አውጪ የመንግሥት አካል ነው፡፡ የአንድ አገር ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት አስፈጻሚ አካል የሚሾመውም በአብዛኛው ከዚሁ አካል ሲሆን፣ አሸናፊው የፖለቲካ ፓርቲ የሚፈልጋቸውን ሕጎች የመከለስ፣ አዳዲስ ሕጎችን የማውጣትና የቆዩትንም ለመሻር የሚጠቀምበት መሣርያ ነው፡፡
በእርግጥም ገዥው ፓርቲ ስለአጠቃላዩ የአገር ዕቅድና ፖሊሲ ለተወካዮቹ አቅርቦ ውይይት የሚደረግበት ሲሆን፣ በግልም ሆነ በተደራጀ ውክልና ያገኙት ተቃዋሚዎችም ገዥው ፓርቲ የሚያወጣቸውን ሕጎች፣ ፖሊሲዎችና የሚወስዳቸውን ዕርምጃዎችን በመፈተሽ ተቃውሞአቸውን ለሕዝበ የሚያሰሙበት ብቸኛ አካል ነው፡፡
ኢሕአዴግ ደርግን አሸንፎ ሥልጣን ከተረከበ ጊዜ ጀምሮ ዲሞክራሲያዊ ያልሆኑ እስካሁን አራት ብሔራዊ ምርጫዎችና የአካባቢ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ በፓርላማ ውስጥ ባገኙዋቸው መጠነኛ መቀመጫዎች አማካይነት ተቃውሞአቸውን የሚገልጹበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ በ97 ዓ.ም. በሦስተኛ ዙር አገራዊ ምርጫ፣ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ እንዲሁም ደግሞ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት (ኅብረት) በጋራ በመሆን ኢሕአዴግን እስከማሸነፍ ደርሰው የነበረ ሲሆን፣ በአገሪቱ ታሪክ ተቃዋሚዎች ከፍተኛውን የፓርላማ መቀመጫ ያገኙበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡
ከደርግ ውድቀት በኋላ በመጀመርያ የተካሄደው የአካባቢ ምርጫ ሲሆን፣ እሱም የሽግግሩን መንግሥት ኮንፈረንስ ተከትሎ በ1984 ዓ.ም. የተካሄደው ነበር፡፡ ይኼው ለወረዳ፣ ለቀበሌና ለዞን ምክር ቤቶች የተደረገውን ምርጫ ብዙዎች ቀጥሎ በ1987 ዓ.ም. ለተካሄደው የመጀመሪያ አገራዊ ምርጫ መሠረት የጣለ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡
የመንግሥት ሥልጣን ለማሸነፍ ፉክክር የሚደረግበትን ዋነኛውን ምርጫ ያህል ትኩረት የሚሰጠው ባይሆንም፣ በሁለት ምክንያቶች ግን የአካባቢ ምርጫ ተፈላጊ መሆኑን ተንታኞቹ ያስረዳሉ፡፡
አንደኛው የአካባቢ ምርጫ ኅብረተሰቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያደርግበትና ከዕለት ተዕለት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወቱ ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ ነው፡፡ አንድ መንግሥት ዲሞክራሲያዊ መሆኑን አለመሆኑን ኅብረተሰቡ የሚመዝንበት፣ በአካባቢው ያሉ አስተዳዳሪዎች ለኅብረተሰቡ ፍላጎት መሥራት መቻላቸውና አለመቻላቸው የኅብረተሰቡ ጥያቄና ቅሬታ በአግባቡ መመለስ ወይም አለመመለሱ የሚያንፀባርቅበት ሁነኛ አጋጣሚ ነው፡፡
ሁለተኛ የአካባቢ ምርጫ በራሱ በቀጥታ የመንግሥት ሥልጣን ለውጥ የሚደረግበት ባይሆንም፣ ዘግይቶ በሚካሄደው ዋነኛ አገራዊ ምርጫ ላይ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ ማሳደሩ ነው፡፡
ኢሕአዴግ ውጤቱ አወዛጋቢ በነበረው ምርጫ 97 ቀጥሎ በርካታ አፋኝ ሕጎች በማውጣት የፖለቲካ ምህዋሩ እንዳያፈናፍን አድርጎታል ፡፡ ከዚህ ባልተናነሰ ግን በ2000 ዓ.ም. በተካሄደው የአካባቢ ምርጫ የተመራጮችን ቁጥር ከፍ እንዲል በማድረግና ተቃዋሚዎችን በማዋከብ የአካባቢ መስተዳደር ምክር ቤቶች ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ለማድረግ ሠርቷል፡፡
በመሆኑም ሁለት ዓመት ዘግይቶ በ2002 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ከፓርላማው ጠቅላላ መቀመጫዎች 99.6 በመቶ የሚሆነው እንዲያገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጎለታል ተብሎ ይታመናል፡፡ በተቃራኒው በአካባቢ አስተዳደሮች ምንም ቦታ ያልነበራቸው ተቃዋሚዎች፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ገብተው ተፅዕኖ ለመፍጠርና ለመቀስቀስ ሳይችሉ ቀርተው ከጨዋታ ውጪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ፡፡
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment