"... ህወሓት በሽርክና የሚያስገነባው ቢሆንስ?"
በጅቡቲ አዲስ የሚገነባው ወደብ ወጪ በኢትዮጵያ እንደሚሸፈን ተገለጸ። ወደቡ በቀጥታ ከትግራይ ከሚነሳው አዲሱ የባቡር መስመር ጋር እንደሚገናኝም ታውቋል። እያደር ይፋ በመሆን ላይ ያሉት ፕሮጀክቶች አቶ ሃይለማርያም አስመራ ድረስ ለመሄድያሳዩትን ፈቃደኛነት “ለኢሳያስ የቀረበ የፖለቲካ አይስክሬም” በማለት አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ፡፡
ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የመሰረት ድንጋይ ለማስቀመጥ ጅቡቲ መጓዛቸውን የዘገቡት ያገር ውስጥ መገናኛዎች ያድበሰበሱት ጉዳይ ይፋ የሆነው ዲሰምበር 18/2012 ለአሜሪካ ሬዲዮ መግለጫ የሰጡት በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝና የታሪክ ምሁር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አየለ በከሬ ናቸው።
ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ እያደገ በመሄዱ ተጨማሪ ወደቦች እንደሚያስፈልጓት የጠቆሙት እኚሁ ምሁር በጅቡቲ የሚሰራው አዲሱ የታጁራ ወደብ ወጪ በከፍተኛ ደረጃ የሚሸፈነው በኢትዮጵያ መሆኑን ይፋ አድርገዋል። አዲስ የሚሰራው የባቡር መስመር ግንባታ ሲጠናቀቅ መቀሌ ከታጁር ወደብ ጋር እንደምትገናኝም አመልክተዋል።
ስለ ባቡር ግንባታ ሲያስረዱ መቀሌን፣ ወልዲያን፣ አፋርንና አዋሽን በማቋረጥ የሚያልፈው የባቡር መስመር ከሌሎች የኢኮኖሚ ተግዳሮት በተጨማሪ በዋናነት “አፋርና ትግራይ” ውስጥ የተገኘውን 1.3 ቢሊዮን ቶን የፖታሽ ምርት ወደ ወደብ ለማጓጓዝ መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል።
በከፍተኛ ደረጃ የተገኘውን የፖታሽ ክምችት የማምረት ስራ እየሰራ ያለው የካናዳ ኩባንያ ስራውን አጠናቆ ማምረት ሲጀምር በጅቡቲ ወደብ በነጻ ለመጠቀም አስቀድሞ ስምምነት የፈጸመ መሆኑ በአሜሪካ ሬዲዮ ጋዜጠኛ አዳነች ፍስሃዬ ተጠይቆ በመላሹ ተረጋግጧል። በዚሁ መሰረት የታጁራ ወደብ ግንባታ እንደተባለው በከፍተኛ ደረጃ ለሚመረተው የፖታሽ ምርት በዋናነት ይውላል መባሉ ሚዛን የሚደፋ አልሆነም። ጉዳዩ “አቶ መለስ ትግራይን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ” አቅደው እንደነበር ካሳበቁት የወ/ሮ አዜብ ንግግር ጋር ይያያዛል የሚል ጥርጣሬም ከወዲሁ ተሰምቷል።
“የታጁራ ወደብ ከአጤ ሚኒሊክ በፊት የነበሩ የሸዋ ነገስታት ይጠቀሙበት የነበረ ወደብ ነበር” ሲሉ የገለጹት ምሁሩ ቀደም ሲል የተተወው ወደብ መሰራቱ ጠቃሚነቱ የጎላ መሆኑን አሁን ካለው ፍላጎት ጋር በማያያዝ አስረድተዋል። እሳቸው ይህንን ቢሉም ትግራይን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግና የኤፈርት የንግድ ተቋማትን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገር የተወጠኑት እቅዶች ይፋ መሆናቸውን ተከትሎ አቶ ሃይለማርያም ደፋ ቀና የሚሉለት የወደብ ግንባታ በቀጣይ ቅሬታዎች ሊበራከቱበት እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀመጡ አሉ።
ምሁሩ ግን እንቅስቃሴው የኢትዮጵያን ብሔራዊ የኢኮኖሚ እድገት በተግባር የሚያሳይ ነው በማለት የተናገሩት በአዳነች ፍስሃዬ “ሌሎችም ፕሮጀክቶች አሉ” በሚል የማስታወሻ ጥያቄ ከቀረበላቸው በኋላ ነው። ቀጥለውም ከዓመት በፊት አቶ መለስ ከኬንያና ከደቡብ ሱዳን አቻቸው ጋር ናይሮቢ ላይ በደረሱት ስምምነት መሰረት በላሞንግ ደሴት ላይ በጋራ ገንዘብ በማዋጣት የሚሰራውን ወደብ ተከትሎ በሚዘረጋው የባቡር መስመር የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍል ተጠቃሚ እንደሚሆን ነው።
434 ቢሊዮን ብር (23 ቢሊዮን ዶላር) የሚፈጀው ይህ ወደብ ሲገነባ ከጁባ ተነስቶ ኬንያ የሚዘልቀው የአውራ ጎዳናና የባቡር መስመርየደቡብ ሱዳንን፣ የደቡብ ኢትዮጵያንና፣ የኬንያን ሰሜናዊ ክፍል በማገናኘት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው የኢኮኖሚ መነቃቃት እንደሚፈጥር ምሁሩ አስረድተዋል። ከአረብ እና ሳውዲ ፈንድ በተገኘ ብድር የሚሰራው ይህ ወደብ የነዳጅ ማጣሪያና ከዚህ አንጻር የተያዙ ብሄራዊ ይዘት ያላቸው ዕቅዶች እንዳሉት በመጠቆም አገራዊነቱ ለማጉላት ሞክረዋል።
አቶ መለስ ህይወታቸው ካለፈ በኋላ በርካታ ፕሮጀክቶች ይፋ መውጣታቸውና የኤፈርት የካፒታል መጠን በምስጢር መያዝ እንደተገጣጠመባቸው ያመለከቱ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር “በቅርቡ መግለጫ የምናወጣበት ጉዳይ ነው። የታጁር ወደብ አቅሙን ድብቅ ያደረገው ህወሃት በምስጢር ሊዝ ከጅቡቲ መንግስት ጋር በግለሰብ ስም ተደራድሮ በስምምነት የሚገነባውና ወደፊት የራሱ (የኤፈርት) የሚሆን ንብረቱ ወይም ላሁኑ በሽርክና የያዘው ቢሆንስ?” የሚል ጥያቄ አንስተዋል። መላምታቸው መነሻ መሰረቶች እንዳሉትና ወደፊት አስፈላጊ ሲሆን ይፋ እንደሚያደርጉትም አስታውቀዋል። አንቀጽ 39ንም ከዚሁ ጋር አስታክከው አስታውሰዋል። መንግስት ፕሮጀክቱ ለሁለቱ አገሮች ጠቀሜታ እንዳለው በማስታወቅ ዝርዝሩን ደብቆ ባለፈው ሳምንት መዘገቡ ይታወሳል።
ገለልተኛ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት “አለመተማመን የኢትዮጵያን ፖለቲካና የወደፊት አቅጣጫ እየበላው ነው” ካሉ በኋላ “መንግስት የጀመራቸውን ስራዎች ይበልጥ ህዝባዊ ለማድረግ ከሁሉም ወገኖች ጋር የፖለቲካ ሰላም በማውረድ ቢያንስ ልማቱ ላይ ያለውን ብዥታ ማስወገድ ካልቻለ የወደፊቱ አደጋና በአገር ስም የሚፈጸመው ስምምነት የልጅልጆቻችንም ከፍለው የማይጨርሱት ይሆናል” ብለዋል። በተለይም አስተያየት ሰጪዎቹ ያሰመሩበት “ቂም የሚቋጥሩ ፕሮጀክቶች ከህዝብ ስለሚርቁ ዋስትና አይኖራቸውምና ኢህአዴግ ከወዲሁ ሊያስብበት ይገባል። ተቃዋሚዎችም መቃወምንና ልማትን ለይተው በመመልክት አገርን ሊያስቀድሙ ይገባል” በማለት ጠንከር ያለ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በሌላ ተመሳሳይ ዜና ጅቡቲ በአባይ ግድብ ከፍተኛ ቦንድ መግዛቷን የትግራይ ዩኒቨርስቲው ምሁር ተናግረዋል። ረዳት ፕሮፌሰር አየለ የቦንዱ መጠን ከፍተኛ እንደሆነ ከመገለጽ ውጪ ትክክለኛ አሃዝ አልተናገሩም፤ ጥያቄውም አልቀረበላቸውም። በአባይ ግድብ ዙሪያ ቦንድ በመግዛት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው አገሮች እንዳሉ ከመሰማቱ ውጪ በግልጽ አገሮቹና የገዙት የቦንድ መጠን እስካሁን ይፋ አልሆነም። ምሁሩ እንደሚሉት እንዲህ ያለው ስምምነት ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ፣ በስምምነት መስራት እንደምትችል የምታሳይበት ነው።የታጁራ ወደብ መገንባት ኢህአዴግ ከሻእቢያ ጋር ለመታረቅ ያለውን የተሰበረ መንገድ አመላካች እንደሆነ የገለጹ አስተያየት ሰጪዎች፣ ሰሞኑን አስመራ በመሄድከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት የጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ደሳለኝን አቀራረብ “የፖለቲካ አይስክሬም” ብለውታል። በማያያዝም በትግራይ ሊገነቡ የታሰቡትና ተገንብተው ያሉት የኢኮኖሚ ተቋማት ሻዕቢያ አሁን ባለበት ደረጃ ከቀጠለ ስጋቱ ከፍተኛ ስለሚሆን በቀልዱ ፖለቲካ ውስጥ እሬት ፖለቲካ መኖሩን አመላክተዋል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
No comments:
Post a Comment