Thursday, December 27, 2012

የስነምግባርና የስነዜጋ ትምህርት አስተማሪዎች የኢህአዴግ አባል እንዲሆኑ ጫና እየደረሰባቸው ነው


ታህሳስ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-መምህራኑ ለኢሳት እንደገለጡት፣ የስነ ምግባርና የስነ ዜጋ መምህራን ከታህሳስ12 እስከ 15 ” የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት የበለፀገች ዴሞከራሲያዊት አገር ለመገንባት ያለው ፋይዳና ሕገ-መንግሥቱን ለትውልድ የማስረፅ አስፈላጊነት” በሚል ርዕስ በአዳማ፣ በሃዋሳ፣ በባህር ዳርና በጅማ ከተሞች ስልጠና እየወሰዱ መሆኑን ተናግረው፣ ስልጠናው በዋናነት በአገሪቱ ዲሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብቶች አያያዝና የህግ የበላይነት ላይ ውይይት ያደርጋል ተብሎ ቢጠበቅም፣ በስልጠናው ላይ የታየው ግን መምህራን የኢህአዴግ አባላት እንዲሆኑ መገፋፋትና ማስፈራራት ነው ብለዋል።
መምህሩ የፈለገውን የፖለቲካ ድርጅት የመከተል መብቱ በህገመንግስት የተረጋጋጠለት ቢሆንም፣ ህገመንግስቱን ማስከበር የሚችለውና ህገመንግስቱ እንዲከበር ፍላጎት ያለው ብቸኛ ድርጅት ኢህአዴግ መሆኑ መገለጹና መምህራንም ህገመንግስቱን የማክበርና የማስከበር ሃለፊነት እንዳለባቸው መገለጹን በስልጠናው የተካፈሉ መምህራን ተናግረዋል።
አዲሱ የመምህራን የሙያ ብቃት ማረጋጋጫ ከያዛቸው መስፈርቶች መካከል አንዱ “ልዩ ልዩ አገልግሎት” የሚል መሆኑን ያስታወሱት መምህራን፣ ልዩ  አገልግሎት የሚለው ለኢህአዴግ ታማኝነትን መግለጽ ነው ብለዋል።
ተማሪዎች የሲቪክ መምህራኖቻቸውን ከህገመንግስትና ከዲሞክራሲ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን እንደሚጠይቁዋቸው የገለጹት መምህራን፣ ሆኖም መምህራን ከስራ መባረርን ወይም የደረጃ እድገት መከልከልን በመፍራት ተማሪዎች እንዲህ አይነት ጥያቄዎችን እንዳያነሱ እንደሚከለክሉ ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment