ታህሳስ ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአዲስአበባ ከተማ ተጀምሮ ወደ ክልሎች ይስፋፋል በሚል ትልቅ ተስፋ እየተሰጠበት
ያለውና በቁጠባ ላይ የተመሰተረው የ40 በ60 ቤቶች ፕሮግራም አጀማመር ባለቤቱን አዲስአበባ
አስተዳደርን ግራ በማጋባቱ እስካሁን ምዝገባ መጀመር ባለመቻሉ በተለያዩ የተምታቱ መግለጫዎች
ሕዝቡን ግራ እያጋቡት መሆናቸው ተሰማ፡፡
በአቶ መኩሪያ ኃይሌ የሚመራው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አጠናሁት ባለው መሰረት
አንድ ቤት ፈላጊ በስቱዲዮ፣ባለአንድ መኝታ ወይም ባለሁለት መኝታ መርጦ ውል ከፈጸመ በኃላ
ለአምስት ዓመታት የቤቱን ግምት 40 በመቶ ቆጥቦ ቀሪው 60 በመቶ ከባንክ በሚገኝ ብድር ተሸፍኖ
የቤት ባለቤት የሚሆንበት ዕቅድ ነበር፡፡
ዕቅዱ በተለይ መካከለኛ ገቢ ያለውን የመንግስት ሰራተኖችን ጨምሮ ሌሎች የኀብረተሰብ ክፍሎችን
ተጠቃሚ ያደርጋል በሚል ብዙ የተወራለት ቢሆንም በቀላሉ ሥራ ላይ ማዋል ግን አልተቻለም፡፡
ዕቅዱን አስመልክቶ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን፣የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር እና ብድር ያቀርባል
የተባለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች እርስበርስ የሚጣረሱ መረጃዎችን ለሕዝብ
ከመልቀቅ ጀምሮ ምዝገባ በዚህ ቀን ይጀመራል በሚል ከፍተኛ ሁካታና ሰልፍ ያስከተለ መግለጫዎችን
ሲሰጡ ቢከርሙም ምዝገባውን ግን መጀመር አልቻሉም፡፡
ስለዚህ ጉዳይ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን በቅርቡ አስተያየት የተጠየቁት የከተማ ልማትና
ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ የተሳሳተ መረጃ የሚሰጡ አካላት ላይ እርምጃ
እንደሚወሰድ እስከመግለጽ የደረሱበት ሁኔታ መኖሩንም ምንጫችን አስታውሶአል፡፡
ይህም ሆኖ አቶ መኩሪያ ራሳቸው በጥቅምት ወር 2005 ዓ.ም ለፓርላማው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ
የቤት ፕሮግራሙ ምዝገባ ይጀመራል በማለት ቃላቸውን ቢሰጡም ሁለት ወራት አልፎም ምዝገባው
ሊጀመር አለመቻሉም ውዥንብር ከሚነዙት ውስጥ አንዱ አድርጓቸዋል፡፡
የ40 በ60 የቤት ልማት ፕሮግራም ምዝገባ ለመጀመር አስቸጋሪ ያደረገው በርካታ ያልተመለሱ
ጥያቄዎች በመኖራቸው መሆኑን ምንጫችን ጠቅሷል፡፡ከነዚህም መካከል “መዝጋቢው አካል
ማንነው?አንድ ሰው ቤት እንደሌለው በምን ተረጋግጦ ይመዘገባል?አንድ ሰው ለአምስት ዓመታት
ቆጥቦ በቀጥታ ቤቱን ማግኘት ይችላል ወይ?የተገነቡት ቤቶች ከቆጣቢዎቹ ቁጥር በላይ ከሆነ ምን
ይደረጋል?በዕጣ የሚለይ ከሆነ አንድ ሰው አምስት ዓመት ሙሉ ተቸግሮ የመቆጠቡን ፋይዳ ዋጋ
አያሳጣውም ወይ? በየጊዜው በዕጣ የሚለይ ከሆነ ሰውየው የቤት ባለቤት የሚሆነው መቼ ነው?
እስከዚያስ ገንዘቡ በባንክ ታስሮ መቆየቱ ምን ያህል ተገቢ ነው?የቤቱን ሙሉ ክፍያ በአንዴ መፈጸም
የሚችሉ ቤት ፈላጊዎች እንዴት ይስተናገዳሉ?አንድ ሰው ቁጠባ ጀምሮ ቢያቋርጥ ገንዘቡን እንዴት
ማግኘት ይችላል?ቁጠባውን ያቋረጠው ሰው የጀመረውን መሸጥ ወይም ለሌላ ማስተላለፍ መብት
ይኖረዋል ወይ?” እና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ሚኒስቴሩም ሆነ የከተማ አስተዳደሩ በመመሪያ መመለስ
አልቻሉም፡፡
በዚህ ምክንያት አሁንም ሕዝቡን ከነገ ፣ዛሬ ምዝገባው ይጀመራል ፣የቤት ችግራችሁም ይቀረፋል
በሚል ተስፋ ከመመገብ ባለፈ በትክክለ ምዝገባው የሚጀመርበት ጊዜ አለመታወቁ እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡
ከዚሁ ጋርም ተያይዞ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የኀብረተሰብ ክፍሎች የገነባል የተባለው የ10 በ90 የቤቶች
ግንባታም ተመሳሳይ ችግር ውስጥ በመሆኑ እንዳልተጀመረ ታውቋል፡፡
No comments:
Post a Comment