Wednesday, December 26, 2012

ከአዲስ አበባ ቅ/ሲኖዶስን ወክሎ የመጣው ልዑክ የሰላምና አንድነት ጉባኤውን መግለጫ ተቃወመ


by Deje Selam
  • አስታራቂ ጉባኤው ይቅርታ ካልጠየቀ በውይይቱ አንሳተፍም ብሏል፤
(ደጀ ሰላም ታኅሣሥ 16/2005 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 25/2012)፦ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አባቶች መካከል የተጀመረው ዕርቀ ሰላም ከግብ እንዳይደርስ “የ6ኛው ፓትርያርክ ምርጫ” ጉዳይ እንዲቀጥል አስመራጭ ኮሚቴ መቋቋሙን ተቃውሞ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ራሱ ጠንካራ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። በተለይም አዲስ አበባ ያሉት አባቶች ጉዳዩን በጥሙና እንዲያስቡበት ያሳሰበው ጉባኤው ይህ ሁሉ ልፋት መና እንዳይቀር ተማጽኗል።
ይህንኑ ደብዳቤ በጽሙና የተቃወሙት ከአዲስ አበባ የመጡት ልዑካን ዛሬ ለደጀ ሰላም በላኩት መግለጫ “የሰላምና የአንድነት ጉባኤ ያወጣው መግለጫ የተሳሳተ መሆኑን አበክሮ ገልጿል። “የሰላምና የአንድነት ጉባኤው ታሕሣሥ 12 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ያወጣው መግለጫ በዘለፋ የተሞላ፣ የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊነት የተዳፈረ፣ ሚዛናዊነትን ያልተከተለ፣ አሳሳች ትርጉም የሰጠ፣ የአደራዳሪ ወይም የአስታራቂ መርህን የጣሰ፣ የተጀመረውን የሰላም ጉዞ የሚያደናቅፍ” ነው ብሎታል። አክሎም “ከሁሉም በላይ የሚያስገርመው ነገር ቢኖር ሁለታችንም የጉዳዩ ባለቤቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሉዓላዊነት በመለስ የሰላሙ ጉዞ እንዳይደናቀፍ ጠብቀን በምንገኝበት በአሁኑ ጊዜ አስታርቃለሁ እያለ የሚገኝ አካል ሆን ብሎ የሰላሙን ሂደት ለማደፍረስ ይህን ያህል የቸኮለበት” ጉዳይ ምሥጢር እንደሆነበት የልዑካኑ ቡድን ጠቅሶ በውይይቱ ወቅትም ይኸው አስታራቂ ኮሚቴ ወገንተኝነት ሲያሳይ መቆየቱን ጨምሮ ጠቅሷል።
አክሎም“ኮሚቴው ይህንን ስህተቱን በግልጽ አምኖ ይቅርታ የማይጠይቅ ከሆነና ኃላፊነቱን በአግባቡ ካልተወጣ ከዛሬ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ኮሚቴ አማካኝነት ለመደራደር ፈቃደኛ እንደማትሆን ሊታወቅ ይገባል” የሚል ጠንካራ አቋም አንቀባርቋል። የመግለጫውን ሙሉ ቃል ከዚህ በታች እንድትመለከቱ እንተይቃለን።
ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን።
በስመአብወወልድወመንፈስቅዱስአሐዱአምላክአሜን፡፡ 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሰላምና የአንድነት ጉባኤ ያወጣውን የተሳሳተ መግለጫ አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ
ወአልቦ ማኅለቅት ለሰላሙ  ለሰላሙ ፍጻሜ የለውም፡ ኢሳ. 9፡7
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ልኡክ ሰላምና አንድነት ለመወያየት ከኅዳር 28 እስከ 3ዐ ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በዳላስ ቴክሳስ ጉሳኤ ተገኝቶ ስለሰላምና አንድነት ሥምረት በተካሄደው ስብሰባ የበኩሉን ጉልህ ሚና መጫወቱ ይታወሳል፡፡
ስለ ሰላሙ ሥምረት ያለውንም አቋም ሁለታችን ወገኖች በጋራ ባወጣነው መግለጫ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ለወደፊትም ለሰላሙ መሳካት ያለውን ፍላጎት በጋራ መግለጫው በሚገባ ተገልጿል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የሰላምና የአንድነት ጉባኤው ታሕሣሥ 12 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ያወጣው መግለጫ በዘለፋ የተሞላ፣ የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊነት የተዳፈረ፣ ሚዛናዊነትን ያልተከተለ፣ አሳሳች ትርጉም የሰጠ፣ የአደራዳሪ ወይም የአስታራቂ መርህን የጣሰ፣ የተጀመረውን የሰላም ጉዞ የሚያደናቅፍ ሆኖ ስለተገኘ የቅዱስ ሲኖዶስ ልኡክ ይህንን መግለጫ ለማውጣት ተገዷል፡፡
በመሠረቱ የጉባኤው ኮሚቴ ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ እንደዚህ ያለ ሚዛናዊነት የጎደለው አዝማሚያ እየተከተለ እንደመጣ በየጊዜው ያወጣቸው መግለጫዎችና መፍትሔ ናቸው ብሎ ያቀረባቸው ሐሳቦች ምስክሮች ናቸው፡፡
ይህን ቅንነትና ሚዛናዊነት የጎደለው አካሄድና አመለካከት እንዲያርም በልኡኩ በኩል ተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎች እንደተሰጡት በአንደበቱ ቢክድ እንኳ ኅሊናው እንደሚረታው እርሱ ራሱ አይስተውም፡፡
ከሁሉም በላይ የሚያስገርመው ነገር ቢኖር ሁለታችንም የጉዳዩ ባለቤቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሉዓላዊነት በመለስ የሰላሙ ጉዞ እንዳይደናቀፍ ጠብቀን በምንገኝበት በአሁኑ ጊዜ አስታርቃለሁ እያለ የሚገኝ አካል ሆን ብሎ የሰላሙን ሂደት ለማደፍረስ ይህን ያህል የቸኮለበት ምሥጢር ምን እንደሆነ ሊገባን አለመቻሉ ነው፡፡
ይሁንና እስከ አሁን ድረስ ባይገባንም አሁን ግን ከመግለጫው ይዘትና መንፈስ አንጻር ስናስተውል ሰላሙ እንዲመጣ ያልፈለገ የሰላም ጉባኤ ኮሚቴው ራሱ እንደሆነ በአንደበቱ መስክሮ አረጋግጦልናል፡፡
የጉባኤው ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶስ ላይ በሰነዘረው የድፍረት ድፍረት የሰላሙ ሂደት ቢሰናከል ተጠያቂው እርሱ ራሱ መሆኑን ሊገነዘብና በግልጽ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል፤ ኮሚቴው ይህንን ስህተቱን በግልጽ አምኖ ይቅርታ የማይጠይቅ ከሆነና ኃላፊነቱን በአግባቡ ካልተወጣ ከዛሬ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ኮሚቴ አማካኝነት ለመደራደር ፈቃደኛ እንደማትሆን ሊታወቅ ይገባል፡፡
ይህም ማለት የማስታረቅ ልምድና ብቃት ያለው፣ ፍጹም ገለልተኛና ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት በሐቅ የሚቆረቆር፣ ሚዛናዊነት ያልተለያቸው የተለያዩ የመፍትሔ ሐሳቦችን በማፍለቅ ማግባባት የሚችል ወገን ሲገኝ ቤተ ክርስቲያናችን የሰላም በሯን ትዝጋለች ማለት አለመሆኑን የቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮችና ወዳጆች ሁሉ በግልጽ ሊያውቁት ይገባል፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱ ለሰላም ፍጻሜ የለውም ብሎ ነግረናልና፡፡
በመጨረሻም ማንኛውም ለእውነት የቆመ ወገን ሁለታችን ወገኖች በጋራ ያወጣነው መግለጫ፣ የጉባኤው ኮሚቴ ካወጣው መግለጫ ጋራ ምን ያህል እንደሚቃረንና የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊ ሥልጣን እንዴት እንደሚዳፈር ቃል በቃል በማነጻጸር መረዳት እንደሚቻል እያስገነዘብን ቤተ ክርስቲያናችን ለሰላም ሲባል እስከአሁን ባደረገችው ጥረት ከግማሽ መንገድ በላይ እንደተጓዘች ሁሉ አሁንም ለሰላሙ ሥምረት እጇን እንደማታጥፍ ለሰላም ወዳጅ ወገኖቻችን ሁሉ አበክረን እንገልጻለን፡፡
ወአልቦ ማህለቅ ለሰላሙ
  1. አባ ገሪማ ዶክተር የብፁዕ ወቅዳስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ፣
  2. አባ አትናቴዎስ የደቡብ ወሎ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
  3. አባ ቀውስጦስ በሰሜን ሸዋ የሰላሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
  4. ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ የመ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት መንፈሳዊ ዘርፍ ም/ሥ/አስኪያጅ፣
ታህሣሥ 13 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም
ዋሽንግተን ዲስ፣ አሜሪካ

No comments:

Post a Comment