Tuesday, December 18, 2012

በአርባ ምንጭ ሰራተኞች ያላግባብ እየተባረርን ነው አሉ


ታህሳስ ፰(ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሰራተኞች ጥያቄና ተቃውሞ ስላነሱ ከስራቸው አየተፈናቀሉ መሆኑን ሰራተኞቹ ከአርባ ምንጭ ገለጹ።
ፋብሪካው አቶ ሙስጠፋና አቶ አስራት ወደተባሉ ሁለት ኢትዮጵያዊያንና አንድ ቻይናዊ ባለሀብቶች ከተላለፈ በኋላ፤ ካለፈው አመት ግንቦት ወር ጀምሮ 200 ሰራተኞች በመባረርና በተለያየ ጫና ከስራ እንደለቀቁ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
አብዛኞቹ ሰራተኞች የተባረሩት በአሰሪዎቹ እንደሆነ ታውቋል።
ሰሞኑንም ስብሰባ ላይ ጥያቄ ያነሱና የተቃወሙ 10 ሰራተኞች ከስራ መባረራቸውንና፤ 5ት ደግሞ ከባድ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ምንጮቻችን ከስፍራው ገልጸውልናል።
ፋብሪካው ወደግል ይዞታ ሲዛወር የሰራተኛውን ጥቅምና መብት እንደሚጠብቅ ቃል ቢገባም፤ የሰራተኞች መብት ከእለት ወደእለት እያሽቆለቆለ መምጣቱን ሰራተኞቹ ይናገራሉ።
ለረጅም አመታት በፋብሪካው የሰሩ ሰራተኞች ያለምንም ካሳ፤ ጡረታና የአገልግሎት ክፍያ ከስራቸው እንደተባረሩ፤ የሚደርስባቸውን ጭቆናና የመብት ጥሰት መቋቋም ያልቻሉ ደግሞ ስራቸውን እየለቀቁ እንደሆነ ታውቋል።
ኢሳት ያናገራቸው የጋሙጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታዬ፤ ጉዳዩን እንደሚያውቁ ነግር ግን በሰራተኛና አሰሪው አዋጅ መሰረት የመንግስት ባለስልጣናት የባለሀብቱን ስራ በሚጋፋ መልኩ ጣልቃ እንደማይገቡ፤ በአዋጁ መሰረት ግን መብታቸው የተጣሰ ሰራተኞች ቅሬታቸው እንደሚዳኝ ገልጸዋል።
አቶ ታዬ አክለውም፤ ከስራቸው የተባረሩ 70 ሰራተኞች እንዳሉ እንደሰሙ፤ ስለተባረሩት 200 ሰዎች ግን መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment