ቴዲ አፍሮ ሰውየውን ለምን ወደደው?
ድምጻዊ፤ገጣሚና የሙዚቃ ደራሲ የሆነው ቴዎድሮስ ካሳሁን ቴዲ አፍሮ ለረጅም ጊዜ በተለያየ ምክንያት ከሙዚቃ አልበምና ከመድረክ ስራው ተለይቶ ቆይቶ በቅርቡ #ጥቁር ሰው; በሚለው አዲሱ የሙዚቃ አልበሙ ብቅ በማለት መላውን የሙዚቃ አፍቃሪ በወቅታዊ ብቃቱ መነጋገርያ እስከመሆንና በሙዚቃ አልበሙ ዙርያ የተለያዩ ስሜትና አስተያየቶችን በተለያዩ ጸሃፍትና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች መወያያ ርዕስ ሆኖ መሰንበቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡የዚህ ሙዚቀኛ ጽንፈኛ ደጋፊዎችና በገለልተኛ ሚዛን ባስቀመጡ አድማጮች መካከል በጋዜጣ፤በመጽሄት፤እንዲሁም በኤሌክትሮኒክስ የመረጃ መረብ በነበረ ፍጭት ግጭትና ሚዛናዊና ሚዛን አልባ አስተያየቶችን መቋጫ ለመስጠት የጉዳዩን ባለቤት የሆነውን ቴዲ አፍሮ በወረሃ ግንቦት 28/2004ዓም አዲስ አበባ በሚገኘው ሂልተን ሆቴል # የጥቁር ሰው ; አዲሱ አልበም ምርቃ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ጥያቄዎችን ይዞ ብቅ ያለው የመንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደሆነ የሚነገርለት ebs የካሳ ሾው ፕሮግራም ጋዜጠኛ ጋር እንግዳ በመሆን የነበረውን ቆይታ በተደጋጋሚ መመልከታችን፤ማድመጣችን ይታወቃል፡፡ እዚህ ላይ በተለያየ ምክንያት ከቀን ወደቀን በቁጥር እያነሱ የመጡት የግል የህትመት ሚድያዎች ምስጋና ይድረሳቸውና በቴሌቪዥን መስኮት ቃለ ምልልሱን ለማድመጥ እድሉ ላልገጠማቸው የጥበብ አፍቃሪያን የነበረውን ቆይታ እንደወረደ ለህትመት ማቅረባቸውን ከአንድም ሁለት መጽሄትና ጋዜጦች ላይ ለመመልከት ችያለሁ፡፡ ነገም ሌሎች በተለያየ መልክ ሀሳብና ትንታኔ በመስጠት ፤በመተቸት ቢያቀርቡ ተገቢ ነው ብሎ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ያምናል፡፡
የካሳ ሾው አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሳሙኤል ካሳ ዝግጅቱን በማስተዋወቅ የቃለ ምልልሱን የቆይታ መድረክ መጋረጃውን በመክፈት ለድምጻዊው ምስጋና በማቅረብ ቃለ ምልልሱ የሚካሄድበት ቦታ የቴዲ አፍሮ ቤት መሆኑን በመጠቆም ጀመረ፡፡ ይህ ድምጻዊ ከሌላ ቀን በተለየ ሁኔታ በጥቁር ሰው የምረቃ በዓል ላይ ለብሶት የነበረውን በልዩ ሁኔታ ተሰርቶ ያሸበረቀ በሀገር ጥበብ ልብስ ደምቆ የንጉሳዊያን የክብር ዙፋን በሚመስለው ወይም በማይተናነሰው የሶፋ ወንበር ላይ በኩራት፤እግሩን እንዳነባበረ ተቀምጧል:: ከበስተጀርባው በጥሩ የፎቶ ፍሬም የተጠረዘ የግርማዊ ቀዳማዊ ንጉስ ኃይለስላሴ ፎቶግራፍ ይታያል፡፡ በስተቀኝ ግድግዳውን ተደግፎ በልዩ ሁኔታ የተሰራ በመስታወት ያሸበረቀ የእቃ መደርደርያ ውስጡ በተለያየ ጊዜና ወቅት የነበሩ የንጉሳዊያን ዘውድና መጠቀሚያ የመሰሉኝ ጌጣጌጦች በአይነት ተደርድረዋል፡፡ ከዚህ መደርደርያ አለፍ ብሎ ለአዲሱ አልበም መጠርያ የሆኑት የአጼ ምኒሊክ (ጥቁር ሰው) ምስል በቆዳ ላይ ተወጥሮ በእጅ የተሳለ ፎቶግራፍ ከግድግዳው ተሰቅሏል…….! እንዴት ደስ ይላል…….!፡፡
ቴዲ አፍሮ የጋዜጠኛውን ጥያቄዎች በሙሉ ልብ በተረጋጋና በሚመስጥ ሁኔታ መመለስ ቀጥሏል…..! ፡፡ የካሳሁን ልጅ ቴዲ……! ከዚህ ቀደም በተለያየ አጋጣሚ በጋዜጣ በመጽሄትና በተለያዩ የመረጃ መረቦች በሙዚቃ ስራዎቹና ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ከተለያዩ ጋዜጠኞች ጋር በነበረው ቆይታ ድምጻዊው የሚሰጣቸው መልሶች ለመስማትና ለማንበብ የታደልን የልጁን ግላዊ ስብዕና ጥልቀትና ምጥቀት፤ውስጣዊ ማንነቱን የሙዚቃ ህይወትና ከማህበተሰቡ ጋር ያለውን ጥልቅ ግኑኝነት አውቀን ቆይተናል፡፡ ዛሬ ወቅትና ጊዜያቶች አልፈው አሁን ላይ የደረሰበትን ደረጃ፤አስተውሎት፤ለሚጠየቀው ጥያቄ ‘ሚሰጠው መልስ ጥንካሬ…..! ፤ምጥቀትና ቁጥብነት…..! ፤የቃላት ምጣኔ……!፤የሃረጎቹ አሰካክ….!፤እንደው ስሜታዊ ሆንክ ባትሉኝ ነፍስና ስጋ የለበሰ ስልቱን ጠብቆ በዜማ የተቀመረ አንድ የምወደው ወይም የምትወዱት የሙዚቃ ስልት ቃናው እየጣፈጠ ወደማይታወቀው ጥልቅ ሰማየ ሰማያት በመንፈስ የሚያስገባ፤የሚያደርስ ያህል አይነት እየተሰማኝ አደመጥኩት ደጋግሜ ሰማሁት………! ቴዲ ተለውጧል ፡፡ ሚስጥሩ ምን ይሆን……? ፡፡ ወደሌላ የግል አስተያየት ከመግባቴ በፊት ከጋዜጠኛው ጋር በነበረው ቆይታ ከበርካታ አስደናቂ ጥያቄና መልሶቹ መሃል ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝን ክፍል አንብበን እንመለስ፡፡
© © ©
;- ሀይል በሚለው የሙዚቃ አልበምህ ላይ የሎሬት ጸጋዩ ገብረመድህንን ድምጽ ተጠቅመሃል እና እንዴት አሰብከው?፡፡ ፤- ፀጋዬ ገብረ መድህን ወይም ገጣሚና ሎሬት ባለቅኔ ፀጋዬ ገ/መድህን ከልጅነቴ ጀምሮ እቤት አባቴ ከነበሩት መፅሃፎች አንዱ #እሳት ወይ አበባ ; የሚል በጥሩ ሁኔታ የተጠረዘ የድሮ መፅሃፍ አለ እኔ ሁለት መፅሀፎች አየለዩኝም ነበር፡፡ አንደኛው የስነ ጽሁፍ ችሎታዬን፤አስተሳሰቤን ከቀረፁት ነገሮች አንዱ ብዙዎቻችን ከመፅሃፍ ቅዱስ ጋር የተያያዘ ህይወት ይኖረናል ፡፡ከቤተሰብ እንደወረስነው እንደ ሃይማኖታችን አይነት ማለት ነው……! ፡፡ አንደኛው እሱ ሲሆን ሁለተኛው በስነ-ፅሁፍ ትልቅ ተፅእኖ ያሰደረብኝ ነገር ቢኖር የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን #እሳት ወይ አበባ; የሚል ስነ-ግጥም መጽሃፍ ነው፡፡ ልጅ ሆኜ ያንን መፅሀፍ በቅጡ ባይገባኝም እታገለው ነበር……! ፡፡ እና ከመኝታዬ ጋር አይጠፋም ብዙ ጊዜ……….! ፡፡ እና ያ….. ነገር ከህይወቴ ጋር ተወራራሽ የሆነ ተፅኖ፤አካሄድ ይኖረዋል ፡፡ # ሙዚቃ ህይወቴ ; የሚለውን ሙዚቃ ሰምተኅው ከሆነ # እሱ እንዳለው ያ ሎሬቱ ; ይላል እዚህ ጋር መጥቶ ደግሞ በትክክል የሳቸውን ድምፅ ተጠቅሞ ይናገራል ፡፡ # ቀላል ይሆናል ; በሚለው ዘፈን ውስጥም አንድም ያሰብከው ቦታ ለመድረስ የሚገጥሙን ፈተናዎች ብዙ ቢሆንም ከማሸነፍ መቆም የለብንም…..!፡፡ የሚያጋጥሙንን አስቸጋሪ ነገሮች ሁሉ ጥንካሬ እየሰጡ የሚያፈናጥሩን መድረስ የምንፈልገው ቦታ ነው ፡፡ ስለዚህ የገደሉን ጥልቀት ወይም የተራራውን መቆምና ርቀት እያሰብን ካሰብንበት መቅረት የለብንም………!፡፡ የገደሉን ጥልቀት ስናየው ፍርሀት ሊሰማን ይችላል ወይም የተራራውን ርቀትና አቋቋም ስናየው ፍርሃት ሊሰማን ይችላል ስለዚህ # ፈራን…..; እያለ ወደ ፍቅር ለመሄድ ጥልቅም ቢሆን ከፍታም ቢሆን…….! # ከፍ ካለው እሩቅ ሰማይ ዝቅ ካለው ጥልቅ ምድር ; እንዳለው ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ ትልቁ ጠላት # ፍርሀት ; ነው፡፡ ፍርሃት ሲቆጣጠረን ሁልጊዜ ወደ አሰብነው ነገር መሄድ አንችልም ፡፡ ወደ ምናስበው ነገር ለመሄድ እንዳንችል የሚቆጣጠረን ፍርሃት ደግሞ በምናየው ነገር ላይ ብቻ የተመረኮዘ ነው……!፡፡ ነገር ግን ከተገለጠው ነገር በላይ ያልተገለጠው ነገር ሃይል እንዳለው የማመን ልቦና በኔም ሆነ በሌሎቻችን ላይ ሊኖረን ይገባል………!፡፡ ይህ ማለት የተገለጠው ስጋችን ነው፡፡ ነገር ግን የተገለጠው ስጋችን ያልተገለጠው ነፍሳችን እንደሚመራው መተማመን አለብን፡፡ ነፍሳችንን ማንም ሰው ወጥቶ አይቶት አያውቅም…….! ስጋችን ሲንቀሳቀስ ግን አናያለን ፡፡ ስጋ ግን ከነፍስ ሲለይ ሬሳ ነው የሚሆነው ፡፡ ስለዚህ በምናየው ነገር ከተገደብን የተራራውን ቁመት ወይም አቋቋም ወይም የገደሉን ጥልቀት ነው የምናየው ፡፡ የመንፈሳችንን አቅም ግን የምናገኘው በምናየው ነገር ከማውራት ይልቅ በምናስበው ነገር ውስጥ መዝለቅ እንዳለብን ነው የሚያሳየን፡፡ እና # ቀላል ይሆናል ; የሚለው ዘፈን ከዚህ ጋር የተቆራኘ የመንፈስ ጥንካሬ…….! ከራሴም ጋር ያለውን የህይወት ትግል ከጋራ ጉዞአችን ጋር ከሰው ልጅ ጉዞ ጋር ያለውን ነገር እያሳየ # ፈራን ; እያለ ሚገፋን ሀይል ነው………! ፡፡ # ሀይል የፍቅር ነው ; እያለ፡፡ በፍቅር ነገሩን በእውነት ካየነው ደግሞ ሁሉ ነገር እንዲያሸንፈን ሆኖ አልተፈጠረም፡፡ ትልቁ ነጥብ እኛ ለፍቅር መሸነፋችን ነው እኔ የሚሰማኝ፤የማየውም እንደዛ ነው………..!፡፡
© © ©
አሁን በርግጥ በተረጋጋ መንፈስ ጆሮ ሰጥቶ ቃለ ምልልሱን ላደመጥን…….! የዚህን ብላቴና በያዘው ሙያና ክህሎት ብሎም በተለያየ ማህበራዊ ህይወቱ፤የግል ስብእናው፤በህዝብ ዘንድ ተወዳጅና ተደማጭነቱ ባገኘው ሰፊ እውቅናን ተጠቅሞ እየሰጠ ያለው አስተዋፅኦ እየጨመረ የመጣበትን ሚስጥር በግልጽ የተዳን ይመስለኛል ፡፡ መፅሀፍ የሰው ልጅን አስተሳሰብ ፤የእውቀት ደረጃን ይለውጣል………! ፡፡ ለደራሲያንና ፀሃፍት ምስጋና ይድረሳቸውና መፅሀፍ ለሰው ልጅ እድገት፤ስልጣኔ፤የእውኑ ዓለም የህይወት ግልባጭ መስታወት ሆነው ዛሬም ሆነ ወደፊት በመቀጠል በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ በእውቀት የተሞሉ ማህበረሰብን በመፍጠር ይዘልቃሉ ፡፡ ይህን ለመረዳት እሩቅ መሄድ አያሳፈልገንም ፡፡ ዛሬ የምናወራለት ቴዲ አፍሮ እንደነገረን ከሆነ የህይወቱ ጉዞ የስኬቱ ቁልፍ መፅሃፍ ነው፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ አንዱ ሲሆን የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን # እሳት ወይ አበባ ; ዘመን ተሸጋሪ የግጥም መድብል መፅሃፍ መሆኑን ነግሮናል ፡፡ በርግጥ ቴዴ ከነገረን በላይ በስነ-ፅሁፍ ሙያ ላይ ለተሰማራ፤ በስሜት በውስጡ ለምንገኝ ሁሉ ሞዴል የሚሆን ማስተማርያ መማርያ መፅሃፍ ነው፡፡ እዚህ ላይ ቴዲ ጋሽ ፀጋዬ መፅሀፋቸው፤ስብእናቸው ብቻ ሳይሆን የንግግር ዘይቤያቸው የቃላት አጣጣላቸው እርጋታቸው የድምፃቸው ለዛ ጭምር ተፅእኖ እንዳሳደረበት በግልፅ አይተናል ወይም ሰምቼዋለሁ ፡፡
በእያንዳንዱ የሙዚቃ አልበሙ ታሪክ ቀመስ አስተማሪ የሙዚቃ ስራዎቹ ግጥሞች………! ፡፡ በርግጥ ምን ያህል ጠለቅ ብሎ መፅሀፍ እንደሚያነብ ይመሰክራሉ፡፡ ከአቦጊዳ አንስቶ፤እስከዛሬው ጥቁር ሰው ወይም አጼ ሚኒሊክ ድረስ የተረከበት የሙዚቃ አልበሙ ውስጥ ሊነግረን ወይም በሙዚቃው እያዋዛ ለዛሬ እንዲሁም ለመጪው ትውልድ ሲያስተላልፍ የፈለጋቸው መልእክቶች በመሉ የግድ በወቅቱ ታሪኩ በተፈጸመ ሰዓት መኖር አይጠበቅበትም……….፡፡ በማንበብ ውስጥ በመመሰጥ ውስጥ እውቀት ይገኛል፤ስብዕና ይጨምራል በሰው ፊት ሙሉ ሆኖ ለመገኘት ያስችላል ያንን ነው ድምፃዊው ላይ ያየነው፡፡
ለዛሬ የፅሁፌን ጭብጥ የነገር ዳርዳርታዬን ያጠናከረልኝ የመሰለኝን የቃለ መጠይቁ አንዱ አካል ከሆነው ቆይታ ልመለስ፡፡ ጋዜጠኛው የተለያዩ ጥያቄዎችን መጠይቁን ቀጥሏል……፡፡ ድንገት እንዲህ ሲል ጠየቀው…………..
፡-#መቼም ወደፊት ቴዲ ሁሉም አልፎ ለመጪው ትውልድ በታሪክ ምን ተብለህ እንድትወሳ ወይም እንድትታወስ ነው የምትፈልገው ? ; ፡፡
ብሎ ጠየቀ፡፡ ይህ ብላቴና እንደተለመደው ሳይመጻደቅ በተረጋጋና ወደፊት የማንነቱን ስብዕና የሚያመላክት መልሱን ሰጠ፡፡
፤- # የሰዎች ስሜት ይለያያል ፡፡ የኔ ስሜት ግን በምንም ሁኔታ እንድታወስ ብዬ አልንቀሳቀስም፡፡ እንደውም ህይወቴ የተሞላው በማስታወስ ውስጥ የተያዘ ነው…….! ስለ ዓድዋ ማስታወስ ስለቀደሙ ታሪካችን በማንበብ የተጠመደ ህይወት ነው ያለኝ፡፡ በዚህ ህይወት ለመታወስ ብዬ የጠነከርኩበት እና የተጋሁበት ጊዜ የለም……!፡፡ ስለዚህ መታወስ ካለብህም መታወስ አለበት ብለው የሚሉ ሌሎች ሰዎች ናቸው እንጂ ለመታወስ ብለህ የምታደርገው እንቅስቃሴ እውነተኛ እና ትክክለኛ አይደለም ፡፡ ስለዚህ እስካሁን እኔ የማውቀው በማስታወስ የተጠመደ ህይወት እንዳለኝ ነው ; ፡፡ ይለናን በዚህ ሁኔታ ከአሁን በኋላ ቴዲን በጀመረው የስኬት መንገዱ የሚያቆመው ያለ አይመስልም፡፡ እድሜ ይስጠው እንጂ ከዚህ ድምፃዊ ብዙ እንጠብቃለን ፡፡ አዲስ በጀመረው የትዳር ህይወቱ እንዲባረክ፤ለሃገር ለወገኑ በኪነ-ጥበብና የማህበራዊ ህይወቱ የተሳካ እንዲሆን እየተመኘሁ #ቀላል ይሆናል ; የሚለውን ሙዚቃ በመጋበዝ ልሰናበት፡፡
# ቀላል ይሆናል ;ዳገቱ ላይ አትዛል ጉልበቴ
የተራራው ጫፍ ፍቅር ናት እርስቴ
ቀላል ይሆናል ቀና አድርገኝ ፅናቴ፡፡
ቀላል ይሆናል ቀላል ይሆናል
ደመና ሲያይ መስሎት የጨለመ
አለ ይሄ ሰው ሁሉም አከተመ
ጥቂት ተስፋን ካየናት አርቀን
ነገ ሌላ ይሆናል ጥሩ ቀን፡፡
ቀላል ይሆናል ቀላል ይሆናል
ፈራን ፍቅር ፈራን
ልጅነት የለገሰንን
የፍቅር አምላክ በጥበቡ በረቂቅ ያለበሰንን
በመለኮት የቀባንን
ህብረት ፈራን
ፍቅር ፈራን፡፡
© © ©
# ፍቅር ያሸንፋል….! ;
adem_hussen@yahoo.com# መፅሃፍ መሬት ባልወረደ ግልብ መረጃና ከእውቀት አልባ ጥልቅ ባህር ውስጥ መንጭቆ የሚያወጣን የህይወት ቁልፍ ሚስጢር ነው…..! ;
No comments:
Post a Comment