ታህሳስ ፲፭(አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መደራደር እፈልጋለሁ ህገመንግስቱንም ተቀብያለሁ ሲል በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን መግለጫ የሰጠው ግለሰብ ከድርጅቱ የተባረረ ተራ አባል መሆኑን የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር አስታወቀ::
የኢትዮጵያ መንግስት ከኦብነግ አንድ አንጃ ጋር መደራደሩን ቢያስታውቅም ኦብነግ ሀሰት ነው ሲል አስተባብሏል: በኦብነግ ውስጥም የተፈጠረ አንዳች አንጃ አለመኖሩን ገልጧል::
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር ከፍተኛ አመራር አቶ ሀሰን አብዱላሂ ለኢሳት በሰጡት መግለጫ አብዲኑር አብድላሂ ፋራህ በኬኒያ የድርጅቱ የውጭ ግንኙነት ተራ አባል ሆነው ሲሰሩ እንደነበር አመልክተው የድርጅቱ የስለላ ቡድን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ስለደረሰበት በዚ ተገምግመው ኦክቶበር 14 ከድርጅቱ የተባረሩ መሆናቸውን ገልጠዋል::
ይሄ የኢትዮጵያ መንግስት ድርጊት ለኛ አዲስ አይደለም ያሉት አቶ ሀሰን ከዚ በፊት ከኦብነግ ጋር በሸራተን ሆቴል ፊርማ መፈራረማቸውን በማስታወስ ከግለሰብ ጋር የተፈራረሙት ፊርማ ያመጣው ለውጥም ውጤትም እንደሌለ ተናግረዋል::
የኦጋዴን ነጸ አውጪ ግንባር በ 64 አገሮች የሚንቀሳቀስ ትልቅ ድርጅት ነው ያሉት አቶ ሀሰን በአሁኑ ሰአት በፖለቲካ አንጻር በከፍተኛ ሁኔታ የተጠናከረበት ፡ በውጊያ አውደ ግንባርም በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንግስት ወታደሮች በየጊዜው እጃቸውን እየሰጡ ያሉበት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል::
አንጃና መከፋፈል የሚባለው የኢትዮጵያ መንግስት ምኞትና ውሸት ነው ብለዋል አቶ ሀሰን አብዱላሂ::
No comments:
Post a Comment