Monday, December 17, 2012

“እኔ ይቅርታ የጠየቅሁት ልጄን በቅርበት ለማሳደግ እና ባለቤቴን ለማገዝ ነው”, ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ


 የጋዜጠኛ ውብሸት ባለቤት።
ዕለተ ቅዳሜ ከጠዋቱ 12፡30 የሚፋጀውን የጠዋት ቁር መቋቋም በሚችል ልብስ ተጀቢቧቡነን
ከፈረንሳይ ለጋሲዮን ተነስተን ጉዞ ጀመርን፡፡ ወደ ፒያሳ፡፡ ከፒያሳ ስታዲየም፡፡ ስታዲየም የአውራምባ ጋዜጣ ሪፖርተርና
የጤና ገፅ አምደኛ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ይጠብቀናል፡፡ እኔ ረዥሙን የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መንገድ እንዲያጋድደኝ፣
በእንግሊዛዊው ፊልፕ ማድሰን የተፃፈውንና በጋዜጠኛ ብሩክ መኮንን ተተርጉሞ “የትንሳዔው ሰማዕት” የሚል ርዕስ
ተሰጥቶት በህዳር ወር 2005 ለሕትመት የበቃውን የአጼ ቴዎድሮስን ታሪክ የሚተርክ መፅሐፍ ይዣለሁ፡፡ የአተራረክ
ስልቱ፣ የታሪክ ፍሰቱ፣ የቋንቋው ለዛና ውበት እንደልብወለድ የሚማርክ፣ እንደፊልም የሚታይ ያህል መስጦኛል፡፡
የአጼ ቴዎድሮስን ታሪክ ጭራሹኑ የማላውቀው እስኪመስለኝ ድረስ እንደአዲስ ግኝት አነበው ዘንድ ግድ ብሎኛል፡፡
በጉዞ ላይ ጥቂት ገጾችን ለማንበብ ነበር የያዝኩት፡፡ ሳሪስ ደርሰን አቤልን እስክናገኘው ድረስ አንድም ገፅ ማንበብ
አልቻልኩም፡፡ የመንገዱ ርዝመት፣ መቆፋፈር እና የትራንስፖርት እጥረት፣ ከታክሲ ታክሲ መገላበጥ አንድም ገፅ
መግለፅ አያስችልም፡፡ በዚያ ላይ ሳሪስ አካባቢ ከእነ አቤል ጋር መገናኘት አልቻልንም፡፡ እናም ስልክ ተደዋውለን
“ወደፊት ቃሊቲ መናኸሪያ እንገናኝ” ተባብለን መመረሽን መርጠናል፡፡
ቃሊቲ ማረሚያ ቤትን ሳልፍ በሃሳብ 5 ዓመታት ያህል የኋሊት ተመለስኩ፡፡ ያኔ እዚህ የእሰረኞች “መናኸሪያ” ውስጥ
ነበርኩ፡፡ ሰዓቴን ተመለከትኩ፡፡ በታክሲ ቃሊቲ ለመድረስ ከ2 ሰዓት በላይ ፈጅቶብኛል፡፡ ነፃ የሚባሉ ሰዎች
እስረኞችን ለመጠየቅ በየቀኑ 4 ሰዓታት ያህል ሰውተዋል፤ በወር በዓመት…የሚያባክኑትን እና ከራሳቸው ህይወት
የሚያጎድሉት ሁሉ ማሰብ ይከብዳል፡፡
በዚህም ሆነ በዚህ – ልኩን በማናውቀው
ጠፍቶት መውጫ በሩ – መግቢያው ስለራቀው…” እንዲሉ፣ ጠያቂዎች ከታሳሪዎች በላይ የሚሰቃዩት ስቃይ ታየኝ፡፡
እስር ቤት በበር በኩል አልገቡም እንጂ የዘወትር “እስረኞች” ናቸው እያልኩ ከሌሎች ጓደኞቻችን ጋር የተቀጣጠርንበት
ቦታ ደረስኩ፡፡ አቤል አለማየሁ እና የአውራምባ ጋዜጣ ትንታግ አምደኞች ከነበሩት ፀሐፊዎች አንዱ ገጣሚ ሰለሞን
ሞገስ (እውነትን ስቀሏት እና ከፀሐይ በታች የተሰኙት የግጥም መፅሐፎች ደራሲ ነው) ተቀላቀሉን፡፡ ጉዞ ወደ አቃቂ
መስመር ሆነ፡፡
ወደ አቃቂ ከተማ የሚያሸጋግረው ድልድይ ስር ከታክሲ ወርደን ሌላ ኮረኮንቻማና አቧራማ መንገድ መጓዝ
ይጠብቀናል፡፡ አቤል፣ ኤልያስና ሰለሞን ከዚህ ቀደም ተመላልሰው ውብሸትን ስለጠየቁት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት
ለመድረስ ከ2 እስከ 2.5 ኪሜ ኮረኮንቻማ መንገድ እንደሚቀር ነገሩን፡፡ ወደማረሚያ ቤቱ ለመድረስ በጋሪ፣ በባጃጅ፣
ወይም ከ20 በላይ ሰው አጉረው በሚጓዙ ሚኒባስ ታክሲ መገልገል ግድ ነው፡፡ እኛም ሰው በሰው ላይ ተደራርቦ
በታጨቀበት ታክሲ ታፍገን 3፡15 ደቂቃ ሲል ቂሊንጦ ደረስን፡፡
በቂሊንጦ በራፍ
በቂሊንጦ እንደቃሊቲ ማረሚያ ቤት የጠያቂ ትርምስ የለም፡፡ አካባቢው ፀጥ ረጭ ያለ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው
እንደደረሰ መታወቂያ አሳይቶና ተፈትሾ መግባት ይችላል፡፡ ከእኔ ጋር የተጓዙት “የአውራምባ ልጆች”ም በጥቂት
ደቂቃዎች ውስጥ ተፈትሸው ወደግቢው ዘልቀዋል፡፡ እኔ ግን ጥቂት ደቂቃ ዘገየሁ፡፡
ሞባይል፣ የኪስ ቦርሳ፣ “ፍላሽ ዲስክ” ወዘተ ለበረኞቹ አስረክቤ ጨረስኩ ስል ኪሴ ውስጥ የተጣጠፉ ወረቀቶች ሲገኙ፣
እሱን ሳስረክብ ደግሞ ቀለማቸው የተሟጠጠ እስኪሪብቶዎች ሲገኙ፣ እሱንም ሳስረክብ በእጄ የያዝኩት መፅሐፍ፡፡…
ብቻ ዘገየሁ፡፡ መፅሐፉ ለእስረኛው እንዲሰጥልኝ አስመዝግቤ እያስረከብኩ ሳለ ድንገት ከአንዱ ፖሊስ ጋር አይን
ለአይን ተገጣጠምን፡፡ ፖሊሱ ከዚህ በፊት (ከቅንጅት መሪዎች ጋር እስረኛ በነበርኩበት ጊዜ) በደንብ ያውቀኛል፡፡ ሞቅ
ያለ ሰላምታ ተለዋውጠን፣ ስለግል ጤንነታችን እየተጠያየቅን እንዲህ አለኝ፡-
“…አንተስ እዚሁ እስር ቤት ይሻልህ ነበር፡፡ ውጪው አልተስማማህም፤ ከሳህ፡፡”
አቤል ጥቂት ደቂቃ መዘግየቴ ግራ ገብቶት ተመልሶ ጠራኝ፡፡ እየሳቅሁ ወደማረሚያ ቤቱ ውስጠኛ ግቢ አመራሁ፡፡
ለምን እንደዘገየሁ ጠየቀኝ፡፡ ፖሊሱ ያለኝን ነገርኩት፡፡ ከት ብሎ እየሳቀ “እኛ ደግሞ ይኼ ልማደኛ በገዛ እግሩ ከመጣ
እዚሁ ይግባ ብለው ገቢ አረጉህ ብለን ጠርጥረን ነበር” አለኝ ከአጥሩ ባሻገር ወደሚገኘው ውብሸት እየጠቆመኝ፡፡
ባለድርብ ማተብ
ገና በሩቅ እንዳየን ነው የውብሸት ታዬ ገፅታ የመደሰትና የመገረም ስሜት ሲረብበት ያስተዋልኩት፡፡ እኔና ፍፁም
ባላሰበውና ባልገመተው መልኩ እዚያ መገኘታችን ያን መሰል ስሜት እንደፈጠረበት የነገረን ወዲያው ነው፡፡
“እናንተ!… እናንተም ትረሱኝ?” ሲል እስከዚያች ቀን ድረስ በአካል ተገኝተን እሱን ባለመጠየታችን ወቀሰን፡፡
ወዲያው ደግሞ የእሱን እስረኝነት በተመለከተ “የተረሳው ጋዜጠኛ” ብዬ በፃፍኩት መጣጥፍ አመሰገነኝ፡፡ ከአፍታ
የናፍቆት ሰላምታና ውይይት በኋላ፣ ከጀርባው የቆመውን እስረኛ እየጠራ “እዚህ መምጣትና አለመምጣት ያለውን
ጥቅምና ጉዳት ታያላችሁ” አለን እኔንና ፍፁምን በቀልድ መልክ፡፡ እናም የጠራውን እስረኛ ወደ እስር ክፍሉ ሄዶ አንድ
ነገር እንዲያመጣ ላከው፡፡
የእስር ክፍሉ ጓደኛው የተባለውን ነገር ይዞ መጣ፡፡ ለአቤል፣ ለኤልያስና ለሰለሞን ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ያዘጋጀላቸው
ከተላጉ እንጨቶች ተፈልፍለው የተሰሩ አምባሮች ናቸው፡፡ ስማቸው የተፃፈበት፡፡ “ለእናንተ ደግሞ ሌላ ቀን” አለን
ቅሬታ እንዳይሰማን በሚመስል ድምፀት፡፡ የእኔን ዓይኖች በአንባሮቹ አሰራርና ውበት ተንከራተቱ፡፡ በተመሳሳይ
መልኩ በእስረኞች የተሰሩና የሚሸጡ አምባሮች አገኝ እንደሆን ጠየቅኩት ከበስተጀርባው ለሽያጭ የተዘጋጁ የእጅ
ስራዎችን እየጠቆምኩት፡፡ አልተገኘም፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ መልኩ ከእንጨት የተሰራ ማተብ አገኘሁ፡፡ የማተቡ
ማሰሪያ የተደረደረ ዶቃ የሚመስል ውብ መስቀል የተንጠለጠለበት ማተብ ገዛሁ፡፡ እናም ባለድርብ ማተብ ሆንኩኝ፡፡
እንዲህ እንዲህ ባለ መልኩ ከውብሸት ጋር በየተራ የልብ የልባችንን እያወጋን እዚያው በዚያው አንድ ውሳኔ ላይ
ደረስን፡፡ ከእስረኞቹ የእደ ጥበብ ውጤቶች ውስጥ ከደቂቃዎች በኋላ ለምንጠይቃት የሙያ አጋራችን ርዕዮት ዓለሙ
በስጦታነት የምናበረክተው ነገር ለመግዛት ወሰንን፡፡ በሁለት ዓይነት ቀለም የተሰራ የአንገት ሹራብ መጠን ያለው
ነጠላ፡፡ የነጠላው ግማሽ አካል ነጭ፣ ግማሹ ደግሞ ቢጫ ቀለም ያለው እንዲሆን ወሰንን፡፡ በአውራምባ ታይምስ
ባልደረቦች ሥም በስጦታነት የሚበረከት የተስፋና የሰላም መልዕክት ያለው እንዲሆን ነው የወሰንነውና የገዛነው፡፡
በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነበር ከውብሸት ጋር ያሳለፍነው የ45 ደቂቃ ቆይታ የተጠናቀቀው፡፡
የውብሸት መከፋት
የ14 ዓመት እስራት የተፈረደበት ውብሸት እስር ቤት ከገባ 1 ዓመት ከ6 ወር አስቆጥሯል፡፡ አካላዊ ጤንነቱ የተሟላ
ነው፡፡ የፊቱ ገፅታ ጥርት ብሏል፡፡ “ቀልቷል፤ አምሮበታል” ማለት ይቻላል፡፡ ደግሞ ደጋግሞ የነገረን መታሰሩ ብዙም
ከባድ እንዳልሆነ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ስሜቱ መጎዳቱን አልሸሸገንም፡፡ ለመንግስት የይቅርታ ጥያቄ ማቅረቡ ከተነገረ
በኋላ የህሊና እረፍት የሚነሱ አሉባልታዎችን መስማቱ ከእስሩ በላይ እንደጎዳውና እንዳሳዘነው ነው የተረዳነው፡፡
“…ማንኛውም ሰው የራሱ አቋም አለው፡፡ ያንን አቋም እንዲይዝ የሚያስገድዱት ሁኔታዎች አሉ፡- የእሱ ብቻ የሆኑ፡፡
እሱ ብቻ የሚያውቃቸው፡፡ እኔም እንደዚያው፡፡ ስለዚህ አቋሙ ሊከበር ይገባል፤ እኔም የሌሎቹን አቋም
አከብራለሁ፡፡”
ውብሸት ይህንን ሲናገር ዓይኖቹ ውስጥ የሚነበበው ቅሬታ አሉባልታው መንፈሱን ምን ያህል እንደጎዳው ያሳብቃል፡፡
ጨርሶ እስከነመታሰሩም የተዘነጋ ሰው ነው፡፡
“….14 ዓመት ነው የተፈረደብኝ፡፡ እስር ቤት ስገባ የሁለት ዓመት ሕፃን ልጄን ትቼ ነው፡፡ ባለቤቴ ስራ የላትም፡፡
የምትኖረው በቤት ኪራይ ነው፡፡ በዚያ ላይ ቀለብ አለ፤ ለትራንስፖርት ወጪ እንኳ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ልጄ ፍትሕ
መማር አለበት፡፡ ለዚህም ገቢ ያስፈልጋል፡፡ የአባት እና የእናት ፍቅር ያስፈልገዋል፡፡ እርግጥ ነው የሥጋ ዘመዶቼ የሆኑ
ሰዎች ባህር ማዶ አሉ፡፡ ምናልባት የአመት በዓል የዓመት በዓል ጊዜ ባለቤቴን በገንዘብ ሊረዷት ይችላሉ፡፡ እሱም
ከስንት አንዴ ቢሆን ነው፡፡ እኔ ይቅርታ የጠየቅሁት ልጄን በቅርበት ለማሳደግ እና ባለቤቴን ለማገዝ ነው፡፡ ሌላ
ምክንያት የለኝም፡፡ ይቅርታ መጠየቅ የለበትም የሚሉትን ሰዎች አቋም አከብራለሁ፡፡ ግን በእኔ ቦታ ቢሆኑ ምንድነው
የሚወስኑት?…”
እውነት ምንድነው የሚወስኑት? ህሊናን የሚፈትን ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄውን እያሰላሰልኩ በጠዋቱ ተነስቼ ወደቂሊንጦ
ያደረግኩትን ጉዞ እና የፈጀብኝን ሰዓት አሰብኩት፡፡ ከ2 ሰአት ተኩል በላይ ፈጅቶብኛል፡፡ ስመለስ ይህን ያህል ሰዓት
ይፈጅብኛል፡፡ የእስረኛው የውብሸትን ባለቤት አሰብኳት፡፡ በጉዞ ብቻ በቀን 4 ሰዓት ትፈጃለች፡፡ ለእስረኛው ቀለብ
ማዘጋጀት የሚወስደው ጊዜ አለ፡፡ ለልጇ ጊዜ መስጠት አለባት፡፡ ሌላም ሌላም ሌላም፡፡ በዚህ ዓይነት የራሷን ሕይወት
የምትኖረው እንዴትና መቼ ነው? ልጁን ፍትሕ ውብሸትን አሰብኩት፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ከመሄድ ይልቅ ወደ እስር
ቤት የሚመላለሰው እስከመቼ ነው? ብላ ብላ ብላ፡፡ ለባለቤቱ አዘንኩላት፡- ለፍትህም አዘንኩ፡፡ አዘንኩላቸው፡፡
በዚህ ዓይነት ሥሜት ውስጥ ሆነን ነው ውብሸትን ተሰናብተነው የወጣነው፡፡ እኛ የእስር ቤቱ ቅጥር ግቢ ተሻግረን
ለመውጣት እግራችንን በሰነዘርንበት ሰከንድ የውብሸት ባለቤትና ልጇ ፍትህ ለመግባት እግራቸውን ሲሰነዝሩ አንድ
ሆነ፡፡ በፀሐዩ ንዳድ ፊቷ እንደመወየብ ብሏል፡፡ በዚያ ላይ የመንገዱ አቧራ ልብሷን አጠቅርሾታል፡፡ የድካም ስሜት
ተጫጭኗታል፡፡ እኛን ስታይ የጠለሸው ፊቷ በፈገግታ ተሞላ፡፡ ወደ እስር ግቢ ከመግባቷ በፊት ለማስታወሻ ፎቶ
እንድንነሳ ጠየቅናት፡፡ የእስር ቤቱ ጥበቃዎች እንደማይቻል ነገሩን፡፡ የሞባይላችንን ካሜራ ወደ እስር ቤቱ ሳይሆን ወደ
ባዶው ሜዳ እንደምናደርግ እና እንዲፈቅዱልን ለመንናቸው፡፡ ፍቃደኝነታቸውን ሳይገልፁን በፍጥነት በየሞባላይችን
ምስላችንን አስቀረን፡፡ የካሜራውን እይታ ወደውጭ ደግነን፡፡ ጓደኛችን ወደውጭ እንዲወጣ እየተመኘን፡፡
ከቂሊንጦ ወደ ቃሊቲ
5፡15 ደቂቃ ሲል ነው ቃሊቲ የደረስነው፡፡ ወደ ማረሚያ ርዕዮት አለሙን ለመጠየቅ 45 ደቂቃ መጠየቅ ይኖርብናል፡፡
“ልዩ” ተጠያቂ የሚጎበኘው ከ6 ሰዓት በኋላ ለ30 ደቂቃ ነው፡፡ ልክ እንደእኛ ሁሉ፣ የእስልምና ተከታዮችን መብት
ለማስከበርና መጅሊሱ እንዲቀየር ጥያቄ ያነሱና የታሰሩት ኮሚቴዎች ጠያቂዎችም ከማረሚያ ቤቱ ውጪ እየተጠባበቁ
ነው፡፡ የመግቢያው ሰዓት ሲደርስ የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮችን ጠያቂዎች በሥም እየተለዩ ይጠሩ ጀመር፡፡ እኛ
ግን የርዕዮት “ልዩ” ተጠያቂነት አስረድተን ወደውስጥ እንድንገባ ተፈቀድልን፡፡ ገባን፡፡ ሌላ 30 ደቂቃ ከጠበቅን በኋላ
ወደ ታሳሪዎቹ አመራን፡፡
ርዕዮት ዓለሙ ነጭ ሱሪ በነጭ ሸሚዝ ለብሳለች፡፡ ከመጠየቂያው የሽቦ አጥር ወዲያ የቆመችው ይህቺ የቀይ ዳማ
ወጣት ገና ከሩቅ ስታየን ተፍለቀለቀች፡፡ ስንደርስ ጣቶቿን በሽቦው አጥር አሾልካ ሞቅ ያለ ሰላምታ አቀረበችልን፡-
እኛም እንደዛው፡፡ እናም አወጋን፡፡ ስላቀረበችው ይግባኝ፣ ከይግባኙ ስለምትጠብቀው ተስፋ ወዘተ ወዘተርፈ አወጋን፡፡
በመጨረሻም የሠላም፣ የመልካም ጤንነት እና የተስፋ መልዕክታችንን ይገልፅናል ያለውን ስጦታ አበረከትልናት፡፡
ወዲያው ነጠላውን በትከሻዋ ላይ አሸጋግራ ጫፍና ጫፉን በደረቷ ላይ አንዠረገገችው፡- በኩራት፡፡ እናም
የመጨረሻው መጀመሪያ ሆነ፡፡
የመጨረሻው መጀመሪያ
ከወደ አቃቂ መስመር ባዶውን እየበረረ የመጣው ሎንቺን ወስጥ ነን፡፡ የመጨረሻው ወንበር መደዳውን ይዘን
የተቀመጥነው የ“አውራምባ ልጆች” ካየነው፣ ከሰማነው፣ ካስተዋልነው እየተነሳን በነፃነት እያወጋን ነው የምንጓዘው፡፡
ሞቅ ያለው የጋለ ወሬአችንን ያቋረጠው ድንገት የተንጫረረው የአቤል እጅ ስልክ ነው፡፡ “ኧረ ባክህ!?” የሚል ግነታዊ
ጥያቄ ሰነዘረ፡፡ ስልኩን ዘግቶ “እናንተ ደዋዩ እኮ ውብሸት በዚህ ሳምንት ይፈታል የሚል ዜና ወጥቷል ነው የሚለኝ”
አለን፡፡
ስታዲየም ዙሪያ ደርሰን የተባለውን ዜና ለማንበብ ቸኮልን፡፡ በእርግጥም “ኢትዮ-ቻናል” ጋዜጣ ዜናውን ይዞ
ወጥቷል፡፡ ከዜናው ርዕስ ጎን በሩቅ ርቀት አሸጋግሮ የሚመለከት የሚመስለው የውብሸት ታዬ ፎቶ አብሮ ታትሟል፡፡
እናም የተባለው እንዲሆን በፅኑ ተመኘን፡፡ የጋዜጣው የተባለው ከሆነ “የእኔና የፍፀም ውብሸትን ጥየቃ የመጨረሻው
መጀመሪያ ሆነ ማለት ነው” አልኩ ለራሴ፡፡ የእስር ቤት የመጨረሻ ጥየቃ ለውብሸት ደግሞ የነፃ ሰውነት ህይወት
ወደድኩ፡፡ እነሆ፡-
“…ደሞ ጊዜው ደርሶ ሁሉንም አይተነው
ሁሉን ለይተነው ሁሉን ጥለን ተውነው
በነፍስ ተወንነው
ተፈፀመ ብለን በመስቀል ዘጋነው… ”
አበቃ!!
* ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ገብረኪዳን የኢትኦጵ እና የአዲስ ዜና ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነበር። ምርጫ 97ን ተከትሎ ቃሊቲ
ከቅንጅት መሪዎች ጋር ታስሮ የነበረ ሲሆን ከዛም ከወጣ በኋላ “የቃሊቲ ምስጢሮች” የተሰኘ መጽሐፍ አሳትሟል።


ለምን ይቅርታ ጠየቀ፣ ፈሪ ነው…ወዘተ የሚሉ አሉባልታዎች ይናፈሱበት እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ እንዲህ
ዓይነት ትችት የሚወረውሩት ወገኖች ግን ለአንድ ቀን እንኳ የእሱን የእስር ቤት ህይወት አላዩም፡፡ ኧረ እንደውም
መጀመሪያ፡፡ እናም ይህንን ፅሁፍ በጀመርኩበት የሙሉጌታ ተስፋዬ “የናቴ ልጅ ወንድሜ” ቅንጭብ ግጥም መደምደም
source: ethionetsa.blogspot.no

No comments:

Post a Comment