Friday, December 14, 2012

በማረሚያቤቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኖሩን መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አመነ


ታህሳስ ፭(አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- መንግስታዊው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች
መኖራቸውን በይፋ አመነ፡፡
ኮሚሽኑ በባህርዳር ከተማ የተከበረውን የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ተከትሎ ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ ላይ የቀረበ
አንድ ጥናት እንዳመለከተው በሕገመንግስቱ የተደነገጉና አገሪቱ ተቀብላ ያጸደቀቻቸውን ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብቶች
በሚቃረን መልኩ በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በታራሚዎች ላይ እየተፈጸሙ መሆኑን ይፋ
አድርጓል፡፡
በማረሚያ ቤቶች በተለይ ልዩ ድጋፍ በሚሹ ሴቶች፣ህጻናት፣አረጋዊያንና የአካል ጉዳተኞች ላይ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ
መብት ጥሰቶች ይበልጥ አሳሳቢ ናቸው ብሏል፡፡እንዲሁም በሁሉም ማረሚያ ቤቶች የምግብ ፣የመኝታ ችግሮች መኖራቸውን
በመጥቀስ ሁኔታው መሻሻል እንደሚገባው ኮሚሽኑ ምክር ሰጥቷል፡፡
በአምባሳደር ጥሩነህ ዜና የሚመራው ይህው ተቋም ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር የሚቀርቡ ሪፖርቶችን
ውሸት ናቸው በሚል እየተከላከለ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ችግሩን በተለሳለሰ አቋምም ቢሆን ለመቀበል
ተገዷል፡፡
በአዲስአበባ ማረሚያ ቤቶች ከሚገኙ ታራሚዎች መካከል 62 በመቶ ያህሉ በአእምሮ ሕመም እየተሰቃዩ መሆኑን
በጥቅምት ወር 2005 ዓ.ም ይፋ በሆነው የጤና ጥበቃ ስትራቴጂ ዕቅድ ላይ መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡
ለኢሳት የደረሱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከግንቦት 7 እና ከኦነግ ጋር ግንኙነት አላችሁ በመባል ከታሰሩት በተጨማሪ፣ በአንዳንድ የሙስሊም መሪዎች ላይ አሰቃቂ ድብደባ እንደተፈጸመ ለማወቅ ተችሎአል።
  • facebook

No comments:

Post a Comment