Wednesday, December 19, 2012

መስፍን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ የ2.6 ቢሊዮን ብር ኮንትራት ተሰጠው


ታህሳስ ፲(አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ባለቤትነቱ የሕወሀት የሆነው መስፍን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ከሶስት የስኳር ፋብሪካዎች የ2.6 ቢሊዮን ብር ኮንትራት እንደወሰደ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘገበ።
ከተቋቋመ 19 አመት የሞላውና የትግራይ መልሶ ማቋቋም ኢንዳውመንት ፈንድ የተሰኘው ግዙፍ ድርጅት አካል የሆነው መስፍን ኢንጂነሪንግ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገነቡ 3 ስኳር ፋብሪካዎች የሚሆኑ የማፍሊያ ቤቶችን (ቦይሊንግ ሀውሶች) ለመገንባት ነው የ2.6 ቢሊዮን ብሩን ኮንትራት የወሰደው።
የመስፍን ኢንጂነሪንግ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አማኑኤል ገብረኪዳን ለኢቲቪ እንደገለጹት፤ ፋብሪካው ከ2 ዓመት በሁዋላ አመታዊ ትርፉን ወደ 600 ሚሊዮን ብር ለማሳደግ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ መስፍን ኢንጂነሪንግ በቦሌ ዞን በ35 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ይገነባል የተባለውን የኢንዱስትሪ ዞን ኮንትራት ወስዶ እየገነባ እንደሆነ ዜናው ጠቁሟል።
መስፍን ኢንጂነሪንግ ከሶስቱ ቦይሊንግ ሀውሶች በተጨማሪ ለስኳር ፋብሪካዎቹ የሚያገልግሉ ላብራቶሪዎችን የመገንባት ኮንትራትም እንደወሰደ ኢቲቪ ጨምሮ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ህግ የፖለቲካ ፓርቲዎች በንግድ ውስጥ እንዳይሰማሩ ቢከለክልም፤ ባለቤትነቱ የሕወሀት የሆነው የትግራይ መልሶ ማቋቋም ኤንዳውመንት ፈንድ፤ በእንግሊዘኛው ምህጻረ ቃል ኤፈርት፤ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች እንደተሰማራና ከሼክ አላሙዲን ቀጥሎ በአገሪቱ ውስጥ በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ቢዝነስ እንደሚያንቀሳቅስ ይታወቃል።
ኤፈርት ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ከመንግስት በሚያገኘው ፖለቲካዊና ወለድ-የለሽ የብድር አገልግሎት በመታገዝ የመንግስት የግንባታ ፕሮግራሞችን ያለተቀናቃኝ በመወስድ የሌሎች የግል ባለሀብቶችን ስራ እንደሚያቀጭጭ አስተያየት ሰጪዎች ይናራሉ።
ስለትግራይ መልሶ ማቋቀም ኤንዳወውመነንት ፈንድ የተጠየቁ የህወሀት አመራሮች ገንዘቡን በትግሉ ሰዓት ያፈራነው ነው ባለቤትነቱም የትግራይ ህዝብ ነው ሲሉ መልስ የሚሰጡ ሲሆን፤ ድርጅቱ ከተቋቋመ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት የውጭ ኦዲት እንፈደማያውቀው የራሱ ህሀወት ባለስልጣናት ይተቻሉ።
ኤፈርት ከመጀመሪያው የድርጅቱ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ስዬ አብርሀ ጊዜ ጀምሮ ከንግድ ባንክ ዋስትና የለሽ የብድር አገልግሎት ያገኝ እንደነበር የሚነገር ሲሆን፤ ከወራት በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበላሹ ብድሮች በሚል የኤፈርትን እዳዎች መሰረዙን መዘገባችን ይታወሳል።
በአሁኑ ሰዓት የኤፈርት የቦርድ ሊቀመንበር የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ናቸው።

    No comments:

    Post a Comment