ታህሳስ ፰(ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ባለፈው አርብ በኬነቲከት ግዛት ኒውስታውን ከተማ በሳንዲ ሁክ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ከተገደሉት 26 ህጻናት መካከል፤ የሁለቱ የቀብር ስነ-ስርአት ዛሬ እንደሚፈጸም ታወቀ።
አዳም ላንዛ በሚባል የ20 አመት ወጣት የተገደሉትን ወጣቶች አስመልክቶ በትናነትናው እለት በኒውስታውን ከተማ በተደረገው የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ፤ ፕሬዚዳንት ኦባማ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።
ግድያው በተፈጸመበት አርብ እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንባ እየተናነቃቸው ሀዘናቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንት ኦባማ በትናነትናው እለት በመገናኛ ብዙሃን በቀጥታ በተላለፈ ንግግራቸው ላይ፤ በህጻናቱና በ6ቱ አዋቂዎች ሞት የተሰማቸውን ሀዘን በድጋሜ ገልጸዋል።
የፕሬዚዳንትን ስልጣኑን ከያዙ ጊዜ ጀምሮ የኒውስታውኑ ግድያ 4ኛ የብዙሀን ግድያ መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ኦባማ፤ “ይሄ አይነቱ አሰቃቂ ግድያ መቆም አለበት፤ እንዲቆምም እኛ መለወጥ አለብን” ብለዋል።
በቀጣዮቹ ቀናትም ይሄንን ችግር ለመፍታት የያዙት ስልጣን የሚፈቅድላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
መጀመሪያ እናቱን የገደለውና መለስተኛ የአእምሮ ችግር እንዳለበት የተነገረው አዳም ላንዛ፤ ወደ ኒውስታውኑ ሳንዲ ሁክ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ሄዶ፤ መስኮት ሰብሮ በመግባት 6 መምህራንና 20 ህጻናትን የገደለው ባለፈው አርብ ሲሆን፤ ገዳዩ በመጨረሻ ራሱን አጥፍቷል።
No comments:
Post a Comment