Saturday, January 26, 2013

ብሔራዊ ቡድኑ በደቡብ አፍሪካ ቆይታው የታላቁ ህዳሴ ግድብን ያስተዋውቃል


አዲስ አበባ ፣ ጥር4 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጨዋቾችና መላው ልዑክ በደቡብ አፍሪካ ቆይታቸው ታላቁን የህዳሴን ግድብ እንዲያስተዋውቁ ጥሪ ቀረበላቸው።
ከአንድ ሳምንት በኋላ በሚጀመረው በዚሁ ውድድር ታላቁን የህዳሴ ግድብ የማስተዋወቅ ትልቅ ሀላፊነት በመቀበላቸው የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታም አባላቱ አረጋግጠዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ለብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾችና ለመላው ልዑክ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በደቡብ አፍሪካ ቆይታቸው እንዴት ባለ ሁኔታ ማስተዋወቅ እንዳለባቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥቷል።
የጽህፈት ቤቱ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ባለሙያ አቶ ዮናስ ሰርፀ ድንግል በግንዛቤው መድረክ ላይ እንደተናገሩት ፥ ተጨዋቾቹ በደቡብ አፍሪካ ቆይታቸው በሀገሪቱ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ለሌሎች የውጭ አገር ዜጎች በተለያየ መድረክና አጋጣሚ ሁሉ ታላቁን የህዳሴ ግድብ የማስተዋወቅ ስራ ይጠበቅባቸዋል።
በደቡብ አፍሪካ ከተለያዩ የውጪ ሚዲያዎች ጋር የመገነኘት እድሉ ስላለም ፥ የአገሪቱን በጎ ገፅታ በማስተወወቅ አገራቸውን ለተቀረው ዓለም በይበልጥ ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥራላቸውም ነው ያስረዱት።
የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው በበኩላቸው  ፥ ቡድኑ ታላቁን የህዳሴ ግድብም ሆነ የአገሪቱን መልካም ገፅታ በቆይታው ለማስተዋወቅ የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል።
የቡድኑ አምበል ደጉ ደበበ በበኩሉ ፥  ተጨዋቾቹ ከሜዳ ውጪ የሚያደርጉትን አልባሳት በመጠቀም ታላቁን የህዳሴ ግድብ በማስተዋወቅ ዙሪያ የተለያዩ ስራዎች እንሰራለን ነው ያለው።
የህዳሴው ግድብ ፕሮጀከት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ታላቁን የህዳሴ ግድብና አገሪቷን በማስተዋወቅ ዙሪያ ለተጨዋቾቹ ገለፃ ማድረጋቸውን አራያት ራያ ዘግባለች።

No comments:

Post a Comment