Saturday, January 19, 2013

መንግስት እግር ኳሱን ፖለቲካዊ መልክ ለማስያዝ ያሰበውን እቅድ እንዲያቆም በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጠየቁ


ጥር ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከ31 ዓመት በሁዋላ   የተገኘውን የስፖርት ውጤት በ አገር ቤት ውስጥ ለፖለቲካ ሲጠቀምበት የነበረው ገዥው ፓርቲ ፤በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው  29ኛው  የ አፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ተመሣሳይ  ፖለቲካዊ  ቅስቀሳ  ለማድረግ ማቀዱ ኢትዮጵያኑን አስቆጥቷል።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አስተባባሪዎች  ፤እንደሚባለው መንግስት ፦<<ባለ ራዕዩ መሪ >>የሚል ጽሁፍ የተፃፈበትንና የአቶ መለስ ፎቶ ያለበትን ቲ-ሸርቲ ተጫዋቾቹም ሆነ ደጋፊዎቹ እንዲለብሱ ካደረገ፤ <<ባለ ራዕዩ>.የሚል ጽሁፍ ያለበትን የአበበ ገላው ፎቶ የታተመበትን ፎቶ እንደሚለብሱ ለ ኢሳት ገልጸዋል።
“ኳሱ ከፖለቲካ ውጪ በሰላም እንዲካሄድ እንፈልጋለን፤ ተጫዋቾቹም ምንም  ዐይነት ጫና እንዳያድርባቸው እንሻለን።መንግስት ከጀመረው ፖለቲካዊ ጨዋታ ካልታቀበ ግን የአበበ ገላውን ቲ-ሸርት ለብሰን ባለ ራዕዩ ማን እንደሆነ በከፍተኛ ስሜት ለዓለም ህዝብ እናሳውቃለን>> ብለዋል- በደቡብ አፍሪካ ያሉት ኢትዮጵያውያን።
በደቡብ አፍሪካ  የሚገኙትና ለአገራቸው ነፃነት ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ የሚታወቁት ኢትዮጵያውያን፤በስፍራው ካሉት የ ኢህአዴግ ደጋፊዎች በብዙ እጥፍ እንደሚበልጡ ያስታወሱ ወገኖች፤መንግስት  ያሰበውን የፖለቲካ ጨዋታ በመተው ስፖርቱ በሰላም እንዲካሄድና ተጫዋቾቹም ከተጽዕኖ ነፃ ሆነው እንዲጫዎቱ ያደርግ ዘንድ መክረዋል።
በሌላ በኩል አርብ ከቀትር በሁዋላ ጆሀንስበርግ የደረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኢትዮጵያውያኑ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።
ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጫዋታዋን የፊታችን ሰኞ ካለፈው ሻምፒዮና ከዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ታደርጋለች።
ፈረንሳዊው የዛምቢያ አሰልጣኝ  ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ለቡድናቸው ከባድ እንደሚሆን ፤ኢትዮጵያ ባቋም መለኪያ ጫዋታዎች ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች አብነት በመጥቀስ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ  ሰውነት ቢሻው በበኩላቸው የምንገባው ለማሸነፍ ነው፤ እናሸንፋለን ብለን እናምናለን።ባናሸንፍ እንኳ ከእኩል መውጣት አንወርድም>>ብለዋል- ቡድኑ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከማምራቱ በፊት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በሰጡት መግለጫ።

No comments:

Post a Comment