Monday, January 14, 2013

በሁስተን ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በድል ተንበሸበሹ


ጥር ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ትናንት እሁድ ሁስተን/አሜሪካ ላይ በተደረገ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንዶቹም ሆነ በሴቶቹ ምድብ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ የአሸናፊነትን ድል መቀዳጀታቸው ታወቀ።
በወንዶች የማራቶን ውድድር አትሌት በዙ ወርቁ 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ17 ሴኮንድ በሆነ ጊዜ በመግባት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሲሆን፣ አትሌት ተፈሪ ባልቻ 2፡12፡50 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ፣  ሌላው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሞላ ሰለሞን ደግሞ 2:14:37 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።
በሴቶቹ ምድብ ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ መሪማ መሃመድ 2 ሰዓት 23 ደቂቃ ከ37 ሴኮንድ በሆነ ግዜ አንደኛ ሆና የአሸናፊነትን ክብር ተቀዳጅታለች። በውድድሩ ላይ የግራ እግሯ ላይ በደረሰባት ጉዳት ውድድሩን በመሃል አቋርጣ የነበረችው መሪማ፣ እግሯን በፋሻ በማሰርና፣ ሕመሟን በመቋቋም አሸናፊ መሆን መቻሏ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን አስችሯታል። ከውድድሩ በኋላ ቃለመጠይቅ ላደረጉላት ጋዜጠኞች እንደገለፀችው ይሰማት የነበረው ህመም ከፍተኛ ነበር። መሪማ ያጠናቀቀችበት ሰዓትም የሁስተን ማራቶን ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ተብሎ ተመዝግቦላታል።
በዚሁ ውድድር ላይ ሌላዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ብዙነሽ ዳባ በመሪማ መሃመድ በ47 ሰከንድ ብቻ ተቀድማ በሁለተኛነት ስታጠናቅቅ፣ አትሌት መስከረም አሰፋ ደግሞ 2 ሰዓት ከ25 ደቂቃ ከ17 ሴኮንድ በሆነ ጊዜ ሶስተኛ ሆና ውድድሩን ማጠናቀቋ ታውቋል።
በግማሽ ማራቶን ውድድርም ባለፈው ዓመት 0፡59፡22 በሆነ ፈጣን ሰዓት አሸናፊ የነበረው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ 1፡01፡54 በሆነ ሰዓት ቀድሞ ሲገባ፣ ሌላው ኢትዪጵያዊ አትሌት ድሪባ መርጋ በሰባት ሴኮንድ ልዩነት ብቻ በፈይሳ ተቀድሞ ውድድሩን በሁለተኛነት አጠናቋል። በሴቶች የግማሽ ማራቶን ውድድርም ባለፈው ዓመትም አሸናፊ የነበረችው አትሌት ማሚቱ ደሳካ 1 ሰዓት ከዘጠኝ ደቂቃ ከ53 ሰኮንድ በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች።

No comments:

Post a Comment