Tuesday, January 8, 2013

በየመን ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደረገው ድብደባ በገመድ እስከማነቅ ከፍቷል/አሰቃቂ ነገር በመስማት በዓልን በእንባ…


በግሩም ተ/ሀይማኖት
የሰው ልጅ ላይ ሊፍጸም የማይገባው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የመን ውስጥ ባሉ የተደራጁ አፋኞች ዜጎቻችን ላይ እየተፈጸመ ነው፡፡ ሰኞ ታህሳስ 29 ቀን በዓልን በገመድ ታንቀው ሲደበደቡ ከነበሩ እና ከሞት ተርፈው ሰነዓ ከገቡ ልጆች ጋር አሳለፍኩ፡፡ ሰውነታቸው ላይ በድብደባ ያረፈውን ቁስል እያየን አንገታቸው ላይ ገመዱ የከረከራቸው ምልክት ሰቅጥጦን ከሞት እንዴት እንደተረፉ እያወጉን በእንባ ታጅበን አሳለፍን፡፡
በዓልን ለማክበር ሁሌም እንደማደርገው ከሰዓት በኋላ ቤቴ ተሰባስበን ምሳ በልተን እንጨዋወታለን፡፡ ካሊድ ለገሰ የተባለ ጓደኛዬ ስልክ ደወለልኝ እና ከባህር የመጡ ሁለት ልጆች አግኝቼ ነበር ይዣቸው ልምጣ? አለኝ፡፡ ከባህር ከመጡማ ይዘሀቸው ና በዓልን አብረውን ያሳልፉ አልኩት፡፡ እኔ ያሰብኩት ብዙ ተንገላተው ደክመው እና ተርበው ስለሆነ የሚመጡት ለራሳችን ያዘጋጀነውን ተቃምሰው በደስታ አብረውን ይዋሉ ብዬ ነው፡፡ በአብዱል ገዊ ግሩፖች
ተይዘው በገመድ ታንቀው የተረፉ ናቸው፡፡ ብዙ ተደብድበዋል…ሲል ካሊድ አከለልኝ፡፡ ደነገጥኩ ከዚህ በፊ እዛ ቦታ ተይዘው፣ ተደብድበው የመጡ ብዙ ልጆች አናግሬያለሁ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ከአንድም ሰው እንኳን በስህተት ጥሩ ነገር አልሰማሁም፡፡ ውስጤ የነበረው በዓል የማክበር ፍላጎት እሳት እንደነካው ላስቲክ ኩምትር ሲል ታወቀኝ፡፡ በበዓሉ ዋዜማ እሁድ ታህሳስ 28 ቀን በነበረኝ ቀጠሮ መሰረት UNHCR ቢሮ ሄጄ ያየኋቸውን ሁለት ኢትዮጵያኖችን እያስታወስኩ ስለ እነሱም አሰላስል ጀመር፡፡ UNHCR ቢሮ ውስጥ ካገኘኋቸው(ካየኋቸው) ሁለት ሴቶች አንደኛዋ ግፋ ቢል ከፍ አድርጌ ብገምታት 16 መት የሚሞላት ልጅ ነች፡፡
ከባህር እንደወረዱ በሚያግቱት ግሩፖች ተይዛ ከደብደባ ብዛት መስማት ትስኗታል፡፡ የቢሮው ሰራተኞች በምን መንገድ ቃለ-ምልልስ እንደሚያደርጉላት ግራ ተጋብተዋል፡፡ መሄድ መራመድ ሁሉ አትችልም፡፡ እግሯን አንፈርክካ ገተት ገተት ትላለች፡፡ ጾታዊ ጥቃት እንደ ደረሰባት ከሁኔታዋ ገመትኩ፡፡ ጆሮዋ ብቻ ሳይሆን ራሷ በድብደባ ችግር ተከስቶባታል፡፡ ፍዝዝ ቅዝዝ…ያለች ናት፡፡ ቁጭ ባለችበት እንቅልፍ ይዟት ጭልጥ ይላል፡፡ ብትት ትልና እንደገና ጭልጥ ትላለች፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሌሊት ራሷን እና ጆሮዋን የተመታችው ሲጠዘጥዛት ስታቃስት፣ ስታለቅስ እንቅልፍ አጥታ ስለምታድር ነው፡፡ ይዛት የመጣችውን ሴት ላናግራት ብሞክርም ኦሮሚኛ ባለመቻሌ በቋንቋ መግባባት አልቻልንም፡፡ ምስጋና ለኡስማን አብዳ ፊቶ አስተርጉሞልኝ ነው ይህን ያህልም የተረዳሁት፡፡ በነገራችን ላይ ከዚህ በፊት ኡስማን አብዳ ፊቶ ማለት ሚስቱ UNHCR በር ላይ በፖሊሶች ተደብድባ የ5 ወር ጽንስ ማስወረዷን ከነ ህክምና ማስረጃዋ አቅርቤ ነበር፡፡ በቅርቡ አሳትመዋለሁ ብዬ ባሰብኩት መጽሀፍ ውስጥ ከሙሉ ማስረጃው ጋር ታሪኩን አቅርቤዋለሁ፡፡
ሁንም ኡስማን ወደ ሁለተኛዋ ሴት እያሳየኝ ‹‹…እሷ ደግሞ እዛ አግተዋት በነበረ ሰዓት እንደ ፈለጋቸው ሲያደርጓት(ሴትነቷን ሲጠቀሙ) ከርመው አርግዛ ነው የመጣችው፡፡…ይሄው ወልዳ አራስ ነች›› አለኝ፡፡ ይሰቀጥጣል በደላችን በዛ፡፡ እዛ ቦታ ታፍነው እርጎዝ ሆነው እና ወልደው ሳይ ከእሷ ጋር አራተኛዬ ነው፡፡ ኢነተር ሶስ የተባለ በሴቶች ጉዳይ የሚሰራ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ በአንድ ቀን 8 ሴቶች ሲመጡ ተደፍረው ህክምና እየተደረገላቸው አይቻለሁ፡፡ ይሄ ሁሉ ለምን ምነው ረሳኸን….ከፈጣዬ ጋር ሙግት ይዤ ስንገታገት የቢሮው ሰራተኛ የሆነው ነቢል የሚሉት መጣ፡፡ ልጅ ይዛ ሲያያት ‹‹ባለፈው ኢንተርቪው ስትገቢ ልጅ የለሽም ነበር አሁን ከየት አመጣሽ? የማነው?..›› ሲል ይጠይቃታል፡፡ ተገዳ ስትደፈር፣ በሴትነቷ ሲጫወቱባት ቆይቶ እርጉዝ እንደነበረች በሰዓቱ መናገሯን ገለፀች፡፡ አሁንም በስቃይ በኦፕሬሽን እንደወለደችው ስትነግረው ሰማሁ፡፡ ወደ ውጭ ሳይሆን ወደ ውስጥ አልቅሼ ምንም ላደርግላቸው ባለመቻሌ እርጉም ደሀ ኪሴን ረግሜ ቤቴ ገባሁ፡፡ ዛሬ ደግሞ…..በዓልን በዓል ለማስመሰል ተሰባስበን ሳለ በነገሩኝ ነገር ተረብሼ በዓሉ በዓል አልመስል አለኝ፡፡ ከእነሱ የሰማሁት አሳዛኝ ታሪክ ደግሞ….
የብታጅራ ልጆች ናቸው፡፡ ማህመድ ሁሴን እና ወርቅዬ ይባላሉ፡፡ ቡታጅራ ባለ ደላላ አማካኝነት ነው (ቤተሰቦቻቸው ደላላዎቹን በህግ እንዲፋለሙ በስልክ ተነጋግረናል፡፡) ስምንት ሺህ ብር ከፍለው ለጉዞ የተነሱት፡፡ ደላላዎቹ በቅብብል የሚሰሩ ናቸው፡፡ ከእነሱ ጋር ሌላም የቡታጅራ ሰው አለ፡፡ ያውም የ8 ልጆች አባት፡፡ ይህ ሰው ከሰመራ ተነስቶ ደዋሌ በሚባለው ቦታ አድርጎ ለስምንት ቀን የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ ወደ ጅቢቲ የሚኬደውን የእግር መንገድ አቅቶት ሜዳ ላይ ወድቆ ቀረ፡፡ እነሱ ስቃያቸውን አይተው አዩ ከሚባለው የጅቡቲ የባህር ጠረፍ ተነስተው የየመኗ ሞካ ይደርሳሉ፡፡ መኪና ቆሞ ነው የጠበቃቸው፡፡ ይሄ ደግሞ እኔ በተደጋጋሚ ከሚያዙ ሰዎች እንዳጣራሁት ጀልባ ጫኞቹና አፋኞቹ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ ተነጋግረው ከጀልባ ሲወርዱ ይጠብቋቸዋል፡፡ መኪና ላይ ጭነዋቸው ለሶስት ሰዓት አካባቢ ተጓዙ፡፡
ግንብ ከታጠረ ትልቅ ግቢ ውስጥ ከተቷቸው፡፡ ‹‹…ሳዑዲያ የሚቀበላችሁን ሰው ስልክ ቁጥር ስጡን ደውለን 1000 የሳዑዲያ ሪያል ከላኩ ትፈታላችሁ፡፡ ያለበለዚያ አንለቃችሁም…እስከዛው በሰላም የያዛችሁትን ሳንቲም ራሳችሁ አውጡ…›› ይሏቸዋል፡፡ ሁሉም ያለውን በተለያየ ቦታ ደብቋል፡፡ አይገኝብኝም ብሎ ዝም…ስልክ ቁጥር ስጡን ሁሉም ዝም፡፡ እያንዳንዱ ሰው በተራ ልብሱን እያወለቀ ራቁቱን ፓንት እንኳን ሳይቀር ማስወለቅ ጀመሩ፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ይህን ድርጊት የሚያደርጉት ተቀጥረው የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ከተለያየ ብሄር አሉ፡፡ ኦሮሚኛ የሚያስተረጉም አለ፡፡ ትግሪኛ የሚያስተረጉም አለ፡፡ አፋርኛ የሚያሰተረጉም አለ፡፡ ታዲያ ማስተርጎም ብቻ እንዳይመስሎት ስራቸው፡፡ እህል ውሀ የማያሰኝ አጣና ይዘው ፌሮ ብረት ይዘው ወገናቸውን ይቀጠቅጣሉ፡፡ አካል ያጎድላሉ፡፡
እነዚህ ወገናቸውን የሚያሰቃዩትን በተመለከተ ሰሞኑን የተከሰተ ነገር ላነሳ ወደድኩ፡፡ አበጋዝ ይባላል፡፡ ሳዑዲያ ድንበር ላይ ለደላላዎች ተቀጥሮ የሚሰራ ሀይለኛ ገራፊ ነው፡፡ አበጋዝ ትክክለኛ ስሙ አይደለም፡፡ ሁሉም የሚያውቁት በዚህ መጠሪያው ነው፡፡ ብዙዎችን አካል በማጉደል የሚታወቅ ጨካኝ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ከሳዑዲያ መጥተው የመን ከሚቆዩት ጋር ተደባልቆ ሰነዓ ከተማ ገባ፡፡ ሀሳቡ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ነው፡፡ በሱ ተደብድበው ብዙ ስቃይ የደረሰባቸው ተሰባስበው ኤምባሲ ከሰሱት፡፡ ውሸታቸውን ነው ብሎ ስለካደ ኤምባሲው በነጻ ለቀቀው፡፡ ኢትዮጵያ ድረስ ተከታትለው ልጆቹ ጠቁመው አሳያዙት፡፡ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ አጣርቶ ወህኒ አውርዶታል፡፡ የመን ያለ ኤምባሲ ቸልተኝነቱን አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት በጅምሩ እንዲቀጥል አሁንም ጥሪ እናሰማለን፡፡
ወርቅዬ ታሪኩን እያፈሰሰልኝ ነው፡፡ ሰውነቱ ደልደል ያለ ነው፡፡ አብሮት ያለው መሀመድ ደግሞ በተቃራኒው ቢያስነጥስ ድፍት የሚል ለንቋሳ ነገር ነው፡፡ ‹‹…ወንዱንም ሴቱንም መለመላችንን እያስቀሩ ያወለቅነው ልብስ ላይ ስማችንን ጽፈን እንድናስቀምጥ ተደረገ፡፡ ሁላችንንም አንድ ክፍል ውስጥ ነው ያጎሩን፡፡ አስብ ሴቱንም ወንዱንም፡፡ ራቁታችንን እያዩን ይስቁብናል፡፡ (እዚህ ጋር በአንድ ወቅት ቃለ-ምልልስ ያደረኩት ልጅ ያለኝን ላክልበት፡፡ ስንያዝ 16 ሰዎች ነበርን፡፡ ሁለት ሴት 14 ወንዶች፡፡ ሁላችንንም ልብሳችንን ካስወለቁን በኋላ ፊታችንን አዙረን ወደ ግርግዳ እያየን እንድንቆም አደረጉን፡፡ ከዛ ከኋላችን እያዩ እነሱ ሴጋ ይመታሉ፡፡ማለት ራሳቸውን በራሳቸው ያረካሉ፡፡)
‹….ልብሳችንን አንድ በአንድ ፈተሹ፡፡ ምንም ሳንቲም ሳያስቀሩልን ወሰዱ፡፡ ስልክ ቁጥር ጽፎ ይዞ ደብቆ ይተገኘ ይገደላል አሉ፡፡ እኔ ይሄ የእህቴ ነው ዱባይ ነች አልኩ፡፡ አንዱንም ሳዑዲያ ያለ ጓደኛዬን ስልክ ሰጠሁ ለመትረፍ ብዬ፡፡ እህቴም ጋር ዱባይ ደወልኩ፡፡ ያላትን ገንዘብ መነሳትህን አላወኩም ኢትዮጵያ ላኩት አለችኝ፡፡ ጓደኛዬም ሳዑዲያ ያለው እሺ እልካለሁ ብሎ በአረቢኛ ካናገራቸው በኋላ ሲደወልለት አላነሳም አለ፡፡ ልብሳችንን ከመለሱልን በኋላ ተጠራሁ እና የተንጠለጠለው ገምድ ውስጥ አንገትህን ክተት ተባልኩኝ፡፡ አማራጭ የለኝም መሳሪያ ይዟል፡፡
ከተትኩ፡፡
ገመዱን ሳቡና አንጠለጠሉኝ፡፡ ትግሪኛ አስተርጓሚው ‹ገና ነው ህይወቱ አልወጣም..› እያለ አቆዩኝ፡፡ በቃ መተንፈስ አቅቶኝ….›› የእሱን ንግግር አቋርጦ መሀመድ ቀጠለ ‹‹ሱባን አላህ..ፍርግጥ ፍርግጥ..አለ፡፡ በቃ እኔማ ሞተ ብዬ አወረዱት የተወሰነ ሰዓት ራሱን አያውቅም ነቃ፡፡…እሱ ሲነቃ ደግሞ እኔን አንጠለጠሉኝ፡፡ ይሄውልህ አንገቴ…››አንገቱ ተከርክሮ ቆስሏል፡፡ ማጅራቱ ላይ ገመዱ የሸመቀቀው ቆዳው ሁሉ ተልጧል፡፡ ምኑን አይተህ አለና ሸሚዙን ወለቅ አደረገው፡፡ ጀርባው የተገረፈበት ተተልትሏል፡፡ ተሰብስበን በዓል እናከብራለን ብለን ተሰብስበን አለቀስን፡፡ ካሊድ ለገሰ(መንግስቱ ለገሰ)፣ ጸሀይ በየነ፣ ሄለን ገብረእግዚአብሄር፣ አስማ ገ/እግዚአብሄር ነብዩ ተስፋዬ ሰብለ ዩሀንስ እና ፉዓድ ነን ትዕይንቱን ለማየት የነበርነው፡፡ በእርግጥ ከዚህ በፊት አይኑ የጠፋ፣ እጅ እግሩ የተሰበረ…ለበርካታ ሆነው
ደፍረዋት ሽንቷን መቆጣጠር ያቃታት ሴት…የጡቷን ጫፍ በላይትር ለኩሰው ያቃጠሏት…ራሱን በመዶሻ በርቅሰውት ራሱን የሳተ፣ ብረት አግለው ብልቷን የተኮሷት…አይቻለሁ አናግሬያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ አዲስ የሰማሁት በገመድ አንቀው
እያሰቃዩ መግደል የበለጠ ሰቅጣጭ ነው፡፡
በመሀመድ ቁስል እና ጠባሳ በማልቀሳችን፣ አይናችን እንባ በማቆሩ ገና ምን አያችሁና የሚል ይመስል ወርቅዬ ትረካውን ቀጠለ፡፡ በተለያየ ጊዜ ስድስቴ ነው የተሰቀልኩት፡፡ አልሞት እያልኳቸው ያወርዱኛል፡፡ በኋላ ላይ ዱላ ይዞ መጣና ግራ ትከሻዬን እስኪ በቃው ወገረኝ፡፡ እጄ ሞተ መሰለኝ ዝልፍልፍ ሲልበት በቀኝ ትከሻዬ ላይ ድብደባውን ቀጠለ፡፡ ቀኙም እጄ ደንዝዞ አልታዘዝህ አለኝ፡፡ በዚህን ጊዜ ጀርባዬ ላይ ይነርተኝ ገባ፡፡ ብጮህ ማን ይድረስልኝ? በመጨረሻ ፌሮ ብረት አንስቶ የጀርባ አጥንቴን ሰበረው፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ደገመኝ…›› አሁንም ብዙውን ሰዓት በዝምታ የሚቆዝመው መሀመድ አቋረጠውና ራሱ ጀመረ፡፡ ‹‹እሪሪ.. ብሎ ጮኸ..በቃ ተዝለፍልፎ ወደቀ፡፡በዚህን ጊዜ በለው…በለው የሚለው አማርኛ ትንሽ ትንሽ የሚችለው አረብ እግር ስር ነበርኩ፡፡ እንዲህ ቢመቱኝ እኔማ ሟች ነኝ ብዬ ‹እንዲያው በእናትህ እኔስ እሞታለሁ፡፡ ያለኝን የወንድሜን ስልክ አሰጣለሁ አታስመታኝ ብዬ እግሩን ሳም አደረኩት፡፡ ደገምኩና ምጥጥ አድረጌ እግሩን ሳምኩት፡፡ በዚህ ሰውነት እሞት ነበር፡፡ እዩት እስኪ ሰውነቱን …›› የወርቅዬን ልብስ ገልጦ ጀርባው ላይ በብረት መተው ያሳበጡትን እና መቀመጥ መቆም ያቃተው የተሰበረ እጥንቱን ቦታ አሳየን፡፡ አንገታቸውን ገመድ ውስጥ ከተዋቸው በዛው የሚሞቱትን እንደቀልድ ወረድ አድርገው ወደ አንድ ጥግ ጣል ያደርጓቸዋል፡፡
‹‹እሪሪሪሪ…….›› ብጮህ ወደድኩኝ፡፡ ግን ወደ የት? ለማን? ምን ሰሚ ማን ተከራካሪ አለንና?… አሁን ይብቃ!!!!!!!…….ምሬት የወለደው የብሶት ጩኸቴን ስሙኝ፡፡ኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡ የወገን ያለህ!!!!!!!!!!!!!!!! ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነኝ የምትሉ ወገኖች ዝም የማይባልበት ሰዓት ላይ ደርሰናል፡፡ እየአንዳንዳችን የየበኩላችንን ልናደርግ ይገባናል፡፡ መንግስት እንዲሰማ ትኩረት እንዲሰጥ ማድረግ የምትችሉ ሁሉ እባካችሁ በርካታ ወገኖች በየቀኑ እያለቁ፣ አካለ ጎዶሎ እየሆኑ፣ መታከሚያ እያጡ በችግር እየተሰቃዩ ነው እባካችሁ…….የየመን ሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርን፣ የየመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ማነጋገር የምትችሉ አካሎች እባካችሁ እባካችሁ፡፡ …..መረጃ ለምትፈልጉ ሰዎች ሁሉ ልጆቹን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የማውቀውን ሁሉ በማድረግ እተባበራለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ የምትሉ፣ ኢትዮጵያን እወዳለሁ የምትሉ ሁሉ ደጋግሜ እንደምናገረው ኢትዮጵያ ያለህዝቧ ባዶ መሬቷን አይደለም የምትወዱት፡፡ ህዝቡ እያለቀ ዝም የሚል ሀገር ወዳድነት እምኑ ላይ ነው፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችሽ ይህን ጉድ ዝም ካላችሁ ለየትኛው ህዝብ ነጻነት ነው የምትታገሉት? አሜሪካ ላለው? አውሮፓ ላለው? ለኢንቨስተሩ?….ኪሱን ላደለበው?…ዝም ካላችሁ ድምጽ ማሰማትም ሆነ መፍትሄ መፈለግ ግድ ካልሰጣችሁ ስልጣል ላይ ተቀምጦ ከለው ስርዓት በምን ትሻላላችሁ?….
ያወራነው ሄ ብቻ አይደለም፡፡ በጣም ብዛት ያለው ጉድ ነግረውኛል፡፡ ሰፋ አድርጌ ልመለስበት ወደድኩ፡፡ ከልጆቹ ጋር የማደርገውን ሙሉ ቃለ-ምልልስ በምስል አስደግፌ ለማቅረብ እሞክራለሁ
ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር ክፍል 9

No comments:

Post a Comment