ጥር ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአዲስአበባ በመንግስት የሚቀርቡ የቤት መስሪያ ቦታና የንግድ ሱቆች ሽያጭ ከግዜ ወደ ግዜ በአስደንጋጭ መልኩ ዋጋቸው እየተሰቀለ መምጣቱን ምንጮቻችን ጠቆሙ፡፡
የአዲስአበባ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ በልደታ ክፍለከተማ የተሰሩ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ጋር ተያይዞ የሚገኙ 150 የንግድ ቤቶችን በጨረታ ለመሸጥ ጥቅምት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ለአንድ ካሬሜትር እስከ ብር 56 ሺ164 ከ11 ሳንቲም እጅግ አስደንጋጭ ዋጋ የሠጡ ተጫራቾች ማሸነፋቸው ታውቋል፡፡
ኤጀንሲው የ149 ቤቶች አሸናፊዎች ስም ዝርዝር ከሳምንት በፊት ይፋ ያደረገ ሲሆን ከጥር 6 ቀን ጀምሮ ቤቶቹን ለአሸናፊዎቹ ማስተላለፍ ጀምሯል፡፡
አስተዳደሩ ለንግድ ቤቶቹ በካሬሜትር የሰጠው መነሻ ዋጋ 6ሺ 600 ብር ሲሆን አሸናፊዎች የሰጡት ዋጋ ግን ከፍተኛው በካሬሜትር 56ሺ164ብር ከ11 ሳንቲም ሲሆን ዝቅተ =ኛው ደግሞ በካሬሜትር 13 ሺ ብር ሆኗል፡፡
በዚሁ መሰረት ከፍተኛ ዋጋ የሰጠው አሸናፊ የተወዳደረው ለ19 ነጥብ 25 ካሬሜትር በመሆኑ በጠቅላላው 1ሚሊየን 81ሺ157ብር ከ12 ሳንቲም ሲሆን ዝቅተኛ የሰጡት አሸናፊ ለ79 ነጥብ 56 ካሬሜትር 1ሚሊየን 34ሺ 280ብር ይከፍላሉ፡፡
ለዚሁ ለልደታ ኮንዶሚኒየም የንግድ ቤቶች ከፍተኛ ብር ከሰጡት ተጫራቾች መካከል በካሬሜትር 52 ሺ600 ብር የሰጡት አንድ አሸናፊ ላሸነፉበት 91 ነጥብ 26 ካሬ ሜትር በድምሩ 4 ሚሊየን 800 ሺ 276 ብር ይከፍላሉ፡፡
ከነዚሁ የንግድ ቤቶች አሸናፊዎች መካከል 23 ያህሉ በካሬሜትር ከ40ሺብር በላይ እጅግ የተጋነነ ዋጋ በመስጠት ያሸነፉ ሲሆን በካሬሜትር ከ20ሺብር በታች አነስተኛ ዋጋ በመስጠት ያሸነፉት 9 ያህል ተጫራቾች ናቸው፡፡
በአዲስአበባ ለንግድና ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል መሬት ከመንግስት ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ከግዜ ወደግዜ የመሬትና የንግድ ሱቆች ዋጋ እየናረ ሊመጣ ችሏል፡፡መንግስት ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከመርዳት ይልቅ በየግዜው የሊዝ መነሻ ዋጋውን እያሳደገ ገቢ ወይም ትርፍ ላይ ብቻ ማተኮሩ ክፉኛ እያስተቸው ይገኛል፡፡
የአስተዳደሩ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽ/ቤት ከቪላ ቤቶች እስከ ባለአራት ፎቅ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችሉ ባዶ ቦታዎችን በተለያዩ ክፍለ ከተሞች አጫርቶ ለመሸጥ በጥቅምት ወር 2005 ባወጣውና በአሁኑ ወቅት ለአሸናፊዎቹ እያስተላለፈ ባለው ጨረታ ውጤት መሰረት ለቦሌ ክፍለከተማ በካሬሜትር 11ሺ700 ብር ሒሳብ ለ420 ካሬሜትር ባዶ ቦታ 4 ሚሊየን 922ሺ 400 ብር ተሸጧል፡፡
ንፋስስልክ ላፍቶ ክ/ከ ደግሞ ከቦሌ በባሰ ሁኔታ ተጫራቾች ለአንድ ካሬሜትር ቦታ 12ሺ500 ብር በመስጠት አሽንፈዋል፡፡ ይህኛው ተጫራች ለ191 ነጥብ 21 ካሬሜትር ቦታ 2 ሚሊየን 390ሺ125 ብር ይከፍላል፡፡
ለመኖሪያ እና ለንግድ ቤቶች መገንቢያ ቦታ ፈላጊዎች አስተዳደሩ ያቀረበው ሊዝ መነሻ ዋጋ ዝቅተኛው በካሬሜትር 191 ብር፣ከፍተኛው 299 ብር ነው፡፡ ይህ መነሻ ብር በተጫራቾች ውድድር በካሬሜትር ከ10ሺ ብር በላይ የሚሰጥበት በመሆኑ አነስተኛና መካከለኛ አቅም ያላቸው ዜጎች በዕድሉ ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም፡፡
አንድ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴ ስለጉዳዩ አስተያየት ተጠይቀው በተለይ ከልደታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ አዲስ የተሰሩት የንግድ ቤቶች እስከዛሬ ታይቶ የማይታወቅ ዋጋ እንደተሰጠባቸው አረጋግጠዋል፡፡ “በጨረታው ላይ ተሳትፌ ያውም ተበድሬ ለማሟላት በማሰብ በካሬሜትር 9ሺብር ገደማ አስገብቼ ነበር፡፡ ነገር ግን የማይታወቁ ነጋዴዎች ጭምር ዋጋውን ከአምስት እጥፍ በላይ ሰቅለውት በማግኘቴ ግርም ብሎኛል፡፡ ሰው በገንዘቡ እንኳን በቀላሉ መጠቀም የማይቻልበት አገር እየሆነ መምጣቱ ብቻም ሳይሆን መንግስትም የለየለት ኪራይ ሰብሳቢ ሆኖ መቀመጡ በጣም አሳሳቢ ነው” ብለዋል፡፡
በልደታ የሚገኙት አብዛኞቹ የመኖሪያ በህወሀት ታጋዮች መያዛቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment