ጥር ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጽያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚያዝያ ወር ለሚያካሂደው የአካባቢና የአዲስአበባ ምርጫ ከታህሳስ 22 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ ቢጀምርም በተለይ በአዲስአበባ ምዝገባው የተቀዛቀዘ መሆኑ ታወቀ፡፡
የምርጫ ጽ/ቤቶች ለመራጮች ምዝገባ ከታህሳስ 22 ቀን እስከ ጥር 21 ቀን 2005 ዓ.ም ክፍት የተደረጉ ቢሆኑም ባለፈው አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ የነበረው የሕዝቡ ምላሽ ለገዥው ፓርቲም አስደንጋጭ እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያለው ምንጫችን ገልጾአል፡፡ምርጫው የረባ ፉክክር የሌለውና የገዥው ፓርቲ አባላት ጭቅጨቃ የበዛበት በመሆኑ ሕዝቡ መሰላቸቱን ምንጫችን ጠቅሶ እስከቀነ ገደቡም ቢሆን መመዝገብ ካለበት መራጭ ሕዝብ ግማሽ ያህሉ
እንኳን ላይመዘገብ እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል፡፡
እንኳን ላይመዘገብ እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል፡፡
በሁኔታው ግራ የተጋቡት የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ሕዝቡን እንደተለመደው አንድ ለአምስት በማቧደን ፣ቤት ለቤት ሄዶ በመቀስቀስ፣ በልማት ስም የተለያዩ ስብሰባዎችን በመጥራት፣የቡና ጠጡ ፕሮግራም በማዘጋጀት የምርጫ ካርድ እንዲወስድና የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል ኢህአዴግን እንዲመርጥ መወትወት ጀምረዋል፡፡
የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደርም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በሚል ሕዝቡን በተለያዩ ስብሰባዎች ወጥሮ የያዘ ሲሆን ይህ ሒደት በተዘዋዋሪ የምርጫ ቅስቀሳ መሆኑ ታውቋል፡፡ ኢህአዴግ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ተቃውሞ ምክንያት በርካታ መራጮች ላይመዘገቡ ይችላሉ በሚል ፍርሀት፣ ካድሬዎቹ የቤት ለቤት ቅስቀሳ እንዲያደርጉ ትእዛዝ ማስተላለፉን መዘገባችን ይታወሳል።
በተያያዘም ዜና ለምርጫ ቦርድ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ባሉት ምርጫ ነክ ችግሮች ላይ መወያየት አለብን በሚል ጥያቄ አቅርበው በቦርዱ አሉታዊ ምላሽ ያገኙት 33 ቱ ፓርቲዎች ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸውን የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባል ገለጹ፡፡
አመራር አባሉ እንዳሉት የምርጫ ችግሮች ያሰባሰባቸው እነዚሁ ፓርቲዎች በጉዳዩ ላይ ሲመክሩ መቆየታቸውን በማስታወስ የምርጫ ችግሮችን ለመፍታት ምርጫ ቦርድ በግልጽ ከኢህአዴግ ጋር አብሮ ወግኖ በቆመበት ሁኔታ ምርጫ መሳተፍ ሒደቱን ከማጀብ ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡
ፓርቲዎቹ በዚሁ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አቋም የፊታችን ቅዳሜ በይፋ እንደሚያሳውቁም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ፓርቲዎቹ ለውይይት ለምርጫ ቦርድ ያቀረቡት ጥያቄ ቦርዱ ለአንድ ወር ጊዜ ያህል ካዘገየ በኋላ “በ2002 ምርጫ ወቅት የተመለሱ ናቸው፣ማስረጃ አልቀረበባቸውም” በሚል ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
No comments:
Post a Comment