Tuesday, January 15, 2013

ከ33 ቱ የፔቲሽን ፈራሚ ፓርቲዎች ባቀረብነው ጥያቄ ዙሪያ በቀጣይ የጋራ አቋም ላይ የተሰጠ መግለጫ


የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድና ገዢው ፓርቲ/መንግሥት ተገደው እንዲሰሙ የማድረግ ህዝባዊ ትግል ይቀጥላል!!
ጥያቄዎቻችን በ “ጆሮ ዳባ ልበስ” ሊታለፉ አይገባም፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድና ገዢው ፓርቲ/መንግሥት ተገደው እንዲሰሙ የማድረግ ህዝባዊ ትግል ይቀጥላል!!
ከ33 ቱ የፔቲሽን ፈራሚ ፓርቲዎች ባቀረብነው ጥያቄ ዙሪያ በቀጣይ የጋራ አቋም ላይ የተሰጠ መግለጫ
1.መግቢያ፤
በአዳማ ከተማ በ2005 ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ላይ ለማወያየት ኢ.ብ.ም.ቦ. በሰበሰበን ወቅት ከተሣታፊ 66 ፓርቲዎች 41ዱ ከጊዜ ሠሌዳው በፊት የውድድር ሜዳውን መስተካከል በሚመለከቱ አበይት የምርጫ ጉዳዮች ልንወያይ ይገባል ከሚለው ኃሣብ በመነሣት እኛ በጉዳዩ ለመግፋት ፔቲሽን ፈረም፡፡ በመቀጠልም በ29/02/05 ዓም 18 ጥያቄዎችን ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ/ኢብምቦ/ ፣ 13 ጥያቄዎችን ደግሞ በ 08/04/05 ለክቡር ጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤትና፣ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ ጽ/ቤት አቅርበን ከቦርዱ ጥያቄኣችሁ “ውኃ አያነሳም” በሚል ሙሉ በሙሉ ውድቅ መደረጉ በ10/04/05 ዓም በቃል ሲገለጽልን ፤ ከጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት፣ ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ ጽ/ቤት መልስ እየጠበቅን መሆኑን ገልጸን መልስ መጠባበቃችንን ቀጠል፡፡
ነገር ግን ጥያቄዎቻችን ግልጽና የማያሻሙ ቢሆኑም ኢብምቦ “ጆሮ ዳባ ልበስ” በሚል ለጥያቂያችን መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ “አጸደቅሁ” ባለው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት በገዢው ፓርቲ አይዞህ ባይነት ወደ ምርጫው አፈጻጸም ገብቷል፡፡
2.በሂደቱ የተገኙ የውሳኔ ኃሣብ መነሻ ነጥቦች፤
2.1. የኢብምቦ ምላሽ የሰጠን የቦርዱ ሰብሳቢ በአዳማ ስብሰባ ላይ፣ የቦርዱ ጽ/ቤት ኃላፊ ደግሞ በ06/03/05 በአዲስ አበባ ቢሯቸው፣ የጥያቂያችንን አግባብነት አምነው የውይይት /ምክክር መድረክ ይዘጋጃል በማለት የሰጡትን መልስ በማጠፍ /ቃላቸውን በመካድ መሆኑ፤
2.2. ከቦረዱ ምላሽና አካሄድ በመነሣት እኛም የቦርዱን “..የገዢው ፓርቲ ወገኝተኝነትንና ጉዳይ ፈጻሚነት..” ፣ ምርጫውን ለማስኬድ እየገፋ ያለው “ ..ለኢህአዴግ ብቻ በተመቻቸ ሜዳ..” መሆኑን፣ የሚሉ አቋሞቻችንን በገለጽንበት- ሂደቱ ወደ ተግባር የተሸጋገረ መሆኑ፤
2.3. የቦርዱ ሰብሳቢ በ24/04/05 በኢቲቪ ቀርበው ጥቄኣችንን በማጣጣል “ ..ከ33ቱ ፈራሚዎች 5ቱ የምርጫ ውድድር ምልክት ወስደዋል…” ፣ “…በርካቶች እየመጡ ጥያቄው እኛን አይመለከተንም እያሉን ነው…” ከማለት አልፈው “… የኮሚቴው አባላት ህጋዊ ውክልና ባይኖራቸውም በሆደ ሰፊነት አነጋግረናቸው ተማምነን ተለያይተናል…”. ሲሉ ፍጹም የክህደትና የመከፋፈል ሴራ የተሞላ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ እንደ ሰብሳቢው መግለጫ 5ቱም ምልክት ቢወስዱ እንኳ የ28ቱ ጥያቄ ውድቅ መደረግ ያለበት በጥያቄዎች ይዘት /ፋይዳ ወይስ በጠያቂዎች ቁጥር? በብዛትስ ቢሆን 28 ፓርቲዎች ጥያቄውን ለማቅረብ ትንሽ ቁጥር ነውን? የሚሉትን ጥያቄዎች አኑረን ይህ ምን ያመለክታል ወደሚለው ስንገባ፤
ሀ/ ቦርዱ በጋራ ባቀረብናቸው ጥያቄዎች ጭንቅ ውስጥ መግባቱን ሲሆን ለዚህም ምላሹን በጽሁፍ ለመስጠት እንኳ ፈቃደኛ ያለመሆኑ ማሣያ ሲሆን፣ እንዲሁም በትብብራችን የተደናገጠውን አይዞህ ባዩን ኢህአዲግ ለመከላከል እየተወራጨ መሆኑን ደግሞ የእነ ወ/ሮ የሺ ፣የአቶ ነጋ እና የፕ/ር መርጋ መግለጫዎች/ምላሾች በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን፤
ለ/ ለእኛ የአካባቢ ምርጫ በህዝቡ ውስጥ መሰረት ለመጣል ዘልቆ መድረሻ በመሆኑ ትኩረት ሰጥተን እየተንቀሳቀስን መሆናችንን በተደጋጋሚ ብንገልጽም፤ ከተሰጠን ምላሽ የምንረዳው ገዢው ፓርቲ/መንግሥት ጥያቄኣችንን ከጥቅም ጋር በማገናኘት የተለየ ትርጉም በመስጠት ለማሳነስ እየጣረ መሆኑን ፤
ሐ/ እስካሁን ድረስ እንኳን ፔቲሽን ፈራሚዎችቹ 5ቱ፤ ከኢህአዲግና አጋር ፓርቲዎችቹ በቀር ጥያቄኣችንን በይፋ/በአደባባይ የተቃወመ ወይም አይመለከተንም ያለ አለመኖሩ፣ይልቁንም ሁሉም ማለት በሚቻልበት ሁኔታ ለጥያቄው በይፋ ድጋፍ የገለጹበት የጥያቂያችንን ትክክለኛነትና ፖለቲካዊ አንደምታ በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን፤
መ/ ምርጫ ቦርድ በህግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ነጻ ፣ፍትሀዊ ፣ተኣማኒና አሳታፊ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማስፈጸም ገለልተኛ ያለመሆኑን፤ ነጻነቱ ፣ ፍላጎትም ሆነ ተነሣሸነት የሌለው መሆኑ..፤
ሠ/ በህዝቡ ውስጥ ጠንካራ የለውጥ ፍላጎትን ይህንንም በምርጫ ለማምጣት ከፍተኛ ተነሳሽነት ቢታይም መራጩ ዜጋ በሚጭበረበር ወይም ድምጹ በሚነጠቅበት ምርጫ የተሰላቸ/ተሥፋ የቆረጠ/ ቢመስልም ከጉዳዩ አሳሳቢነትና ካለው አገራዊ ፋይዳ አኳያ ጥያቄኣችንን በትኩረትና በንቃት እየተከታተለ መሆኑ..፤
ረ/ በጥያቄኣችን የተነሱት ጉዳዮች በምርጫ ባለድርሻ አካላት በአጠቃላይ እንዲታወቁ እተደረገ መሆኑን እንዲሁም የሁሉንም ትኩረት በመሳብ የመወያያ ርዕስ መሆናቸውን፤ …ወዘተርፈ
በአጠቃላይ ከስብስቡ የጋራ ጥያቄ አቀራረብ የተገኘው ትምህርትም ሆነ የእስከዛሬው የጋራ አቋም/ጥረት ያሳደረው ተጽዕኖ እንዲሁም ሂደቱ ያስከተለው ፖለቲካዊ አንድምታ ይበል የሚያሰኝ/አበረታች/ ለቀጣይነቱም ለሁላችንም በዓላማና ተግባር እንድንተሳሰርና ወቅታዊ አገራዊ ጥሪ የሚያስተላልፍ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡
3. የጋራ አቋም
ጥያቄኣችን ከመነሻው በምርጫ የመሣተፍ/ያለመሣተፍ ጉዳይ አልነበረም፤ ዛሬም አይደለም፡፡ ጥያቄኣችን በጥቅሉ- በህገ መንግስቱ መሠረት የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ – መብቶች ተከብረው በዜጎች ይሁንታ/ድምጽ በሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር የህግ የበላይነት የተከበረበት ትክክለኛ መድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እንዲቻል ለነጻ ፣ፍትሃዊ ፣ተኣማኒ፣ አሳታፊ፣ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የውድድር ሜዳው ይስተካከል ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ-ገዥው ፓርቲ “የምርጫ ፖለቲካውን በቁጥጥሩ ሥር በማዋል ለቀጣይ 40 እና50 ዓመታት በብቸኝነት አገሪቱን እገዛለሁ” ለሚለው ዓላማው የኢብምቦ ን በጉዳይ ፈጻሚነት የሚጠቀምበትን ሥውር (አንዳንድ ጊዜም ግልጽ) እጁን እንዲያነሣ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በተሻሻለው የምርጫ ህግ (አዋጅ ቁጥር 532/1999) አንቀጽ 7 በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር መሠረት ኃላፊነቱን በገለልተኝነት መወጣቱን እንዲያረጋግጥ፣ በዚህም ነጻና ግልጽ የውይይት/ምክክር መድረክ በመፍጠር በዚህ ወሳኝ አገራዊ ጉዳይ ላይ በምርጫ ህጉ አንቀጽ 7 (16) መሠረት እንደ ዋነኛ ባለድርሻ ያወያየን/እንመካከርበት ነው፡፡
ስለዚህ በጥያቄኣችን የተነሱ መሰረታዊ ጉዳዮች ባልተሟሉበት ማለትም ባለንበት ተጨባጭ እውነታ እንደ ፓርቲ ስለውድድር ፣ እንደዜጋ ስለ መራጭነት ምዝገባ መነጋገር ለገዢው ፓርቲ የምርጫ ሴራ ይሁንታ መስጠት፣ አልፎም የምርጫ መርሆዎች እንዳይከበሩ በመተባበር በህገ መንግሥቱ መሠረት ዘላቂ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገውን ሠላማዊ ትግልና ጥረት ወደኋላ መጎተት ነው፡፡ ይህም የለውጥ ፍላጎታችንን፣ የኣላማ አንድነታችንን፣ ጽናታችንን ቁርጠኝነታችንን በጥያቄ ውስጥ መክተት ነው፡፡
በመሆኑም ጥያቄኣችንባልተመለሰበት ስለምርጫ ተሣትፎ ማሰብ “ተጨፈኑ ላሞኛችሁን” መቀበል ከመሆኑ በተጨማሪ ጥያቄኣችንን እነርሱ ወደፈለጉት ደረጃ ማውረድ/ማሳነስ ነው፡፡ ስለዚህ በጋራ ይዘን ለተነሳነው ጥያቄ ምርጫ ቦርድም ሆነ ገዢው ፓርቲ/መንግሥት እስከዛሬ ጆሮኣቸውን ቢደፍኑም ዛሬም ጊዜ እንዳላቸው በማስረዳት ተገደው እንዲሰሙ ለማድረግ ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠርና ማስተባበር የተባበረን የተቀነጀ ትግላችንን እንቀጥላለ፡፡
ይህ ማለት መቼውንም እኛ ከምርጫው ሂደት ውጪ አይደለንም፤ ማንም ውጪ ሊያደርገን አይችልም፡፡ እንደዋነኛ የምርጫው ባለድርሻ በሂደቱናላይ ያነሣነው ጥያቄ እሰኪመለስ መራጩን ህዝብ ከጎናችን እንዲሰለፍ በማድረግ በጥያቄኣችን ያነሣናው ጉዳዮች መፍትሔ እንዲያገኙ እኛም በተደጋጋሚ እንደገለጽነው ወደ ሥልጣና መሸጋገሪያው ብቸኛ መንገዳችንን አስከፍተን በተስተካከለ የመወዳደሪያ ሜዳ የመጠቀም / በምርጫ የመሣተፍ/መብታችንን ለማስከበር የሚደረግ ትግል ነው፡፡ ለዚህ ተፈጻሚነት በአጭር ጊዜ በጋራ ማከናወን ያለብን ተግባራት፡-
1. ባሳለፍነው ውሳኔ መሠረት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ፤
2. እየተነጋገርንበት ላለው በትብብር የመሥራት ጉዳይ የተዘጋጀውን የመግባቢያ ሠነድ ረቂቅ በማጠነቀቅ አጽድቆ በሠነዱ መሰረት ወደ ተግባራዊ እ..ቅስቃሴ መግባት፤
3. የመግባቢያ ሠነድ ረቂቅ ላይ ከሚደረገው ውይይት ጎን ለጎን ይህንን የጋራ አቋማችንን ለጉዳዩ ዋነኛ ባለቤትና ባለድርሻ አካላት ማሳወቅ፤ በተለይም ከጉዳዩ ተጠቃሚና ቀጥተኛ ባለቤት(መራጩ ህዝብ) ጋር በህዝባዊ የውይይት መድረክ መገናኘትና መወያየት፤ናቸው፡፡
ስለሆነም መላው የአገራችን ዜጎች እንዲሁም በኢትዮጵያ አሣታፊ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ የበኩላቸውን ድርሻ የሚያበረክቱ አገራት፣ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ተቋማት ከጎናችን ሆነው ነጻ፣ፍትሀዊ፣አሣታፊ፣ተኣማኒና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ጥያቄዎቻችን ምላሽ ያገኙ ዘንድ ተገቢውን ተጽዕኖ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪያችንን አበክረን እናቀርባለን፡፡
በተባበረ ሰላማዊ ሕዝባዊ ትግል ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ከድርጅታችን ይልቅ ለአገራዊ የህዝብ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት በትብብር እንሰራለን!!
ጥር 07 2005 ዓ.ም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment