Monday, January 28, 2013

እነ አዳነ ግርማን ያፈሩ የደቡብ ኳስ ሜዳዎች እንደ አዲስ አበባ የሕንፃ ሲሳይ ሊሆኑ ነው



እነ አዳነ ግርማን ያፈሩ የደቡብ ኳስ ሜዳዎች እንደ አዲስ አበባ የሕንፃ ሲሳይ ሊሆኑ ነው
በኢብራሒም ሻፊ
ሙሉጌታ ምሕረት ወደ ደቡብ አፍሪካ የተጓዘው ብሔራዊ ቡድን አባል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባደረጋቸው አራት የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይም አልተሰለፈም፡፡
እንዲያውም ለብሔራዊ ቡድኑ ከተጫወተ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሄው የሐዋሳ ከነማ አምበል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዞ እንዲፋለም ባለውለተኛ ነው፡፡

ሙሉጌታ በማጣሪያ ጨዋታዎቹ ባይሳተፍም በእርሱ ምክር የተገሩትና የእርሱን ፈለግ የተከተሉት አዳነ ግርማ፣ ሽመልስ በቀለ እና በኃይሉ አሰፋ የብሔራዊ ቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ሙሉጌታ ለእነዚህ ተጫዋቾቹ የሰጠው ምክሩንና ልምዱን ብቻ አይደለም፡፡ “ኮረም ሜዳንም” ጭምር እንጂ!

ኮረም ሜዳ የሙሉጌታ ሜዳ ነው፡፡ ከመኖሪያ ቤታቸው በዕርምጃዎች ርቀት የሚገኘው ይሄው ሜዳ ከአንዴም ለአሥር ጊዜያት በመንግሥት ለሌላ ዓላማ ታጥሮ ነበር፡፡ “ሜዳዬ ነው” ብሎ የሚያምነው ሙሉጌታ ግን እጅ አልሰጠም፡፡ ቀን የመንግሥት ሰዎች መጥተው ካጠሩት ማታ ሙሉጌታ እና ጓደኞቹ የታጠረበትን ዕቃ ያፈራርሳሉ፤ ሽቦም ከሆነ ይቆርጣሉ፡፡ ከሜዳው አጠገብ ትምህርት ቤት በመኖሩ ለረዥም ጊዜ ይሄንን ቦታ “ለማስፋፊያ” ብሎ የተመኘው ትምህርት ቤቱ ነው፡፡

ለዓመታት ቦታውን ሲያጥረው የነበረውም ይሄው ትምህርት ቤት ነው፡፡ ሙሉጌታ ግን ተፋለማቸው፡፡ ለረዥም ጊዜ ጓደኞቹን አስተባብሮ የሽቦ አጥርን ቆርጧል፤ የተገነባ አፈርሷል፡፡ የትምህርት ቤቱ ማስፋፊያ ኮሚቴ አባላት በድርጊቱ ሁሉም እየተማረሩ ነበር፡፡ አፍራሹን አለማወቃቸው ሌላ ሕመማቸው ነበር፡፡ በተለይ በኮሚቴው ተሰሚነት የነበራቸው የራሱ የሙሉጌታ አባት ምሕረት ምን ማድረግ ይሻላል? ብለው ብዙ ተጨንቀዋል፡፡ በወቅቱ በእግር ኳስ ትልቅ ደረጃ እደርሳለሁ ብሎ ይተጋ የነበረው ትልቁ ሙሉጌታ ይሄንን ተመልክቶ አላስቻለውም፡፡ “አፍራሹ እኔ ነኝ” አለ፡፡ “የማፈርሰውም እግር ኳስን መጫወት በጣም ስለምወድ ነው” ብሎ እቅጩን ተናገረ፡፡ አባት በመጀመሪያ ተቆጡ፡፡ ሆኖም ግን ልጃቸው እንዲህ ዓይነት ጥፋት ውስጥ ያገኘበትን ምክንያት በጥልቀት አሰላሰሉ፡፡ ለእግር ኳስ ያለው ጥብቅ ፍቅር በሜዳው ላይ ዓይናቸውን የሚጥሉ ሰዎችን እንደ ጠላት እንዲመለከት እንዳደረገው ተገነዘቡ፡፡ ይሄ ሜዳ የትምህርት ቤቱ ማስፋፊያ ቢሠራበት ልጄና ጓደኞቹ የት ሄደው ይጫወታሉ ብለው ራሳቸውን ጠየቁ፡፡ በቀጣይ ስብሰባ ትምህርት ቤቱ ለማስፋፊያ ሥራ ሌሎች ዘዴዎችን መጠቆም እንዳለበት አስረዱ፡፡ ኮረም ሜዳ መነካት እንደሌለበት በደንብ አብራሩ፡፡

ኮረም ሜዳ ነፃ ወጣ፡፡ ሙሉጌታ የሚጫወትበት ሜዳ አገኘ፡፡ እዚህ ሜዳ ላይ ወጣቱ ሙሉጌታ ተአምር ሲያሳይ አዳነ፣ ሽመልስ እና በኃይሉ ምነው እርሱን በሆንኩ ብለው ተመኙ፡፡ ከኮረም ሜዳ ወደ ሀዋሳ ከነማ ሲያመራ እነርሱ ታሪካዊውን ሜዳ ተረከቡ፡፡ በሙሉጌታ ጀግንነት ነፃ የወጣው ሜዳ ላይ እንደልብ ቦረቁበት፡፡ ዛሬ በደቡብ አፍሪካ የሚያሳዩን ተአምር የኮረም ሜዳ ጥንስስ ውጤት ነው፡፡

ደቡብ አፍሪካ የተጓዘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የደቡብ ኢትዮጵያ ተፅዕኖ ያጎላበታል፡፡ ሲሳይ ባንጫ፣ ደጉ ደበበ፣ አበባው ቡጣቆ፣ ጌታነህ ከበደ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ፣ ሽመልስ በቀለ፣ አዳነ ግርማ እና በኃይሉ አሰፋ የደቡብ ፍሬዎች ናቸው፡፡ ለጥንካሬና ቅልጥፍና ዓሣን እየተመገቡ በምቹ ሰፋፊ ሜዳዎች እግር ኳስን እየተጫወቱ ያደጉ ልጆች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ አንገቷን ቀና እንድታደርግ ያስቻሉት እነዚህ ልጆች የአመጋገባቸው፣ ሲቦርቁ ያደጉባቸው ሜዳዎች እና የሙሉጌታ ምክር ውጤቶች ናቸው፡፡

አሁን ግን ችግር አለ፡፡ ኢትዮጵያ ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በቅታ ነገሮች ቢድበሰበሱም በመንግሥት የተረሳው ስፖርትና እግር ኳስ ትልቅ ችግርን የመጋፈጥ አደጋ ውስጥ ገብቷል፡፡ ላለፉት አሠርታት የእግር ኳስ ተጫዋቾች “ፋብሪካ” እስክትመስል በርካታ ተጫዋቾችን ያፈራችው ደቡብም የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ ለመሆን ተቃርባለች፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወደ ደቡብ ተጫዋቾች ፊቱን ከማዞሩ በፊት የብሔራዊ ቡድኑ አለኝታ ተጫዋቾች በብዛት ብቅ የሚሉት ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ነበር፡፡ መንግሥት በሁለቱ ከተሞች የመኖሪያ ቤቶችን ችግር ለመቅረፍ የእግር ኳስ ሜዳዎችን ለግንባታ ዒላማ ሲያደርግ፤ ከቤቶቹ ግንባታ በኋላ አነስተኛም ቢሆን የእግር ኳስ ሜዳዎችን እገነባለሁ ብሎ ያቀደ አይመስልም፡፡

በአዲስ አበባ ከ35 በላይ አንግል ያላቸው ሜዳዎች ሕንፃ ሲገነባባቸው “ይሄ ነገር ጥፋት ነው” ብሎ “ሀይ” ያለ የለም፡፡ ግንባታዎቹ ተጠናቅቀው ወደ ሥራ ሲገባ ለአካባቢው ሕፃናት መጫወቻ ወይም ስፖርት መሥሪያ ሜዳ አንዱም አላሰናዳም፡፡ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ መጫወቻ ሜዳዎች የማስፋፊያ ሜዳ ሲሠራባቸው ሕፃናቱ እግር ኳስን የመጫወቻ ሜዳ ይቅርና መቆሚያ እንኳን እንደሚያጡ ማንም አልተረዳላቸውም፡፡ ይሄ ችግር የድሬዳዋም ችግር ሆነ፡፡ ውጤቱ ደግሞ ወደ 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በተጓዘው ቡድን ውስጥ በግልፅ ታየ፡፡ ድሬዳዋ በዚህ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ አንድም ተጫዋች አላስመረጠችም፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ ጃንሜዳ እየተጫወተ ያደገውን አሉላ ግርማን፣ አልማዝዬ ሜዳ ቦርቆ ያሳለፈውን አሥራት መገርሳን፣ በመስቀል አደባባይ አስፋልት ሜዳዎች ላይ የፈነጨውን ዳዊት እስጢፋኖስን፣ በፈረንሣይ ለጋሲዮን ሰፋፊ ሜዳዎች የማግኘት ዕድል የገጠመውን ብርሃኑ ቦጋለን እና ለስታዲየም ግንባታ በሚል ኢምፔሪያል አካባቢ የታጠረ ሜዳን ያገኘውን ምንያህል ተሾመን ብቻ አስመርጣለች፡፡ አሁን ግን የአሥራት ሜዳ አልማዝዬ ሜዳ፣ የብርሃኑ የፈረንሣይ ሜዳዎችና የምንያህል ባለውለተኛ ቦታ የሉም፡፡ የአዲስ አበባ ሕፃናትም እግር ኳስን እንዳይጫወቱ የተፈረደባቸው ይመስላል፡፡ በተገኙ ክፍት ቦታዎች ሁሉ ያለምንም ማካካሻ ግንባታ ተለውጦባቸዋል ወይም ተጀምሮባቸዋል፡፡

ስለዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ደቡብ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝና ጋምቤላ ፊቱን አዙሯል፡፡ የደቡብ የእግር ኳስ “ፋብሪካ” ግን እንደ አዲስ አበባው ሊቆም ተቃርቧል፡፡ በሀዋሳ እና አርባ ምንጫ ያለምንም ማካካሻ የእግር ኳስ ሜዳዎች መኖሪያ ቤቶችና ሕንፃ እየተገነባባቸው ይገኛሉ፡፡

የሀዋሳ ከነማው የመሀል ተከላካይ አንዷለም ነጋ (ቢጣ) የተገኘበት “አሮጌው ሜዳ” ትምህርት ቤት ተሠርቶበታል፡፡ ትምህርት ቤቱ ያለ እግር ኳስ ሜዳ በመሠራቱ በርካታ ወጣቶች ከእግር ኳስ ጋር ተራርቀው ቀርተዋል፡፡ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው (ሞሪንሆ) በወጣትነቱ ሕፃናትን ሲያሰለጥንባቸው የነበሩ ሁለት ሜዳዎች ዛሬ የሉም፡፡ አንዱ አጠና ተራ ሆኖ እንጨት ይነገድበታል፡፡ ሌላኛው ተሸንሽኖ የሸቀጥ መሸጫ ሱቅና ልብስ ቤቶች ተወልደውበታል፡፡ የዘላለምን ፈለግ ተከትለው እዚህ ሜዳ ላይ ሕፃናትን ያሰለጥኑ የነበሩ እስከ “ቢ” ላይሰንስ ድረስ የነበራቸው አሰልጣኞች በአሁኑ ወቅት የባጃጅ ባለቤትና ሾፌሮች ናቸው፡፡ እግር ኳስን እርግፍ አድርገው ትተውታል፡፡

በሀዋሳ ከተማና በደቡብ ፖሊስ በዋና እና ምክትል አሰልጣኝነት የሠራው አዲሴ ካሳ እንኳን አሁን ሕፃናትን የሚያሰለጥንበት ሜዳ አጥቶ በምሬት ሙያን ስለመቀየር ያስባል፡፡ ሙሉጌታ ጉዳዩን “በጣም የሚያስፈራ” በማለት ይገልፀዋል፡፡ “እኔ ባገኘሁት አጋጣሚ በሙሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ አስፈላጊነትና የሥልጣኔ ማሳያ አንድ ጎን እንደሆኑ እናገራለሁ” ይላል፡፡ ታዲያ ሰሚ የለም? ብላችሁ ስትጠይቁት “እስካሁን አላገኘሁም፡፡ አሁን ግን የከተማው ከንቲባ አቶ ብሩ ማሞ ጥሩ ነገሮችን እያሳዩኝ ነው፡፡ ቢሯቸው ጠርተው በደንብ ተወያይተናል፡፡ እንደ ጓደኛ ስለተቀራረብን በስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ግንባታ አስፈላጊነት ተማምነዋል” በማለት ይመልሳል፡፡ ከንቲባውንም እጅግ ያመሰግናል፡፡

በተከታታይ የኢትዮጵያ እግር ኳስንና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ለመምራት ዕድሉን ያገኙት የደቡብ ሰዎችስ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ለመፍጠር ሙከራ አላደረጉምን? የመፍትሔ አቅጣጫስ ለማሳየት አልሞከሩም? ሙሉጌታ እዚህ ጋር የንዴት ሳቅ አመለጠው፤ “ወጥተው እንኳን አይተው አያውቁም” በማለት ቁርጡን ተናገረ፡፡ “አሁን ኮረም እና ቄራ ሜዳ ቀርተውናል፡፡ በከንቲባው ዕርዳታ እነዚህን ሜዳዎች ካላቆየን…” በማለት ዝም አለ ሙሉጌታ… በረዥሙ ከተነፈሰ በኋላ “እንደ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ እግር ኳስ በሀዋሳም ይጠፋል…፡፡” ሐዘን የዋጠው ሙሉጌታ ዝምታው በጣም ያሳዝን ነበር፡፡

ከአዘጋጁ፡-
ኢብራሒም ሻፊ በሸገር ኤፍኤም 102.1 የኳስ ሜዳ ፕሮግራም ባልደረባ ነው
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/sport/item/522

No comments:

Post a Comment