Saturday, January 19, 2013

በቦረና ዞን ህዝቡ ለሚሊሻ ማደራጃ ገንዘብ እንዲያወጣ እየተገደደ ነው


ጥር ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በቦረና ዞን የኢሳት ወኪል እንደዘገበው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መንግስት የአካባቢ ሚሊሻ ለማቋቋም በሚል ምክንያት እያንዳንዱ ዞኑ ነዋሪ 70 ብር በነፍስ ወከፍ እንዲከፍል አዟል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ” እኛን መልሶ ለሚበድለን ሚሊሺያ እንዴት ገንዘብ እናዋጣለን” በሚል ተቃውሞውን በማሰማቱ እስካሁን ድረስ፣ በቂ መዋጮ ሊዋጣ እንዳልቻለ ታውቋል።
መንግስት በዞኑ እየተባባሰ የመጣውን ከብሄር ጋር በተያያዘ የሚነሳውን  ግጭት ለማስቆም ባለመቻሉ በሶማሊ ክልል እንደተደረገው የአካባቢ ሚሊሺያ ለማቋቋም ማቀዱ ታውቋል።
ነዋሪዎች ገንዘብ እንዲያዋጡ የተገደዱት ለሚሊሺያዎቹ ማሰልጠኛ  ነው።
በቦረና ዞን በሶማሊ እና በኦሮሞ ተወላጆች መካከል በተደጋጋሚ የሚታየው ግጭት በእየአመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል። በአካባቢው ለሚታየው ግጭት መክንያቱ የመንግስት የዘር ፖሊሲ ነው በማለት የአካባቢውን ነዋሪዎች አነጋግሮ ኢሳት አንድ ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል።

ፍረደም ሐውስ የ 2013 ኢትዮጵያ ነጻነት የሌለባት ናት አለ

ጥር ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአለም ላይ ያሉ አገሮችን ነጻነት ( ፍሪደም) በማወዳደር ሪፖርቱን የሚያወጣው አለማቀፋዊ እውቅና ያለው ፍሪደም ሀውስ የ2013 ሪፖርቱን ይፋ ሲያደርግ እንደገለጠው  ኢትዮጵያ ነጻነት የሌለባት አገር ናት ብሎአታል።
ፍሪደም ሐውስ የአለም አገራትን ነጻነት የሰፈነባቸው ከፊል ነጻነት ያለባቸውና ነጻነት የሌለባቸው አገራት በማለት በሶስት ከፍሎ የተመለከተ ሲሆን ፣ ነጻነት የሌለባቸው አገራት ተብለው የተፈረጁት መሰረታዊ የሆኑት የፖለቲካ መብቶች የሌሉባቸው፣ እንዲሁም የሰቪል ነጻነቶች የተነፈጉባቸው አገሮች ናቸው።
ኢትዮጵያ ነጻነት የሌለባቸው አገሮች ተብላ የተፈረጀችው በአገሩ የፕሬስ ነጻነትን ጨምሮ ሌሎች የሰብአዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች ባለመከበራቸው ነው።
በአፍሪካ ውስጥ ነጻነት የሰፈነባቸው ተብለው የተጠቀሱት አገሮች  ቤኒን፣ ቦትስዋና፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ጋና፣ ሌሶቶ፣ ማሊ፣ ሞሪሺየስ፣ ናምቢያ፣ ሳኦቶሚና ፕሪንሲፒ እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው።
ነጻነት ከሌለባቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ፣ አንጎላ፣ ካሜሩን፣ ቻድ፣ ሁለቱ ኮንጎዎች፣ ጅቡቲ፣ ኢኳቶሪያን ጊኒ፣ ኤርትራ፣ ጋቦን፣ ጋምቢያ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ማሊ፣ ሞሪታኒያ፣ ሩዋንዳ እና ሶማሊያ ይገኙበታል።
ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች በከፊል ነጻነት ያለባቸው ኬንያ እና ዩጋንዳ ናቸው።
የህወሀት/ ኢህአዴግ መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ እና ፖለቲካ መብቶች መከበራቸውን በተደጋጋሚ ቢገልጽም፣ የፍሪደም ሐውስ ሪፖርት እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በ እኤአ 2010 ከነበራት ከፊል ነጻ ደረጃ  ወደ ነጻነት ወደ ሌለባቸው አገራት ደረጃ መውረዷን ነው።

    No comments:

    Post a Comment