Saturday, January 5, 2013

ጠ/ሚኒስትሩ “ነፃ አገር ነው” ብለዋል – ማተሚያ ቤቶች እንዳትፈሩ! Written by ኤልያስ


በስልክ “ጋዜጣ አታትሙ” ብሎ ማዘዝ ቀረ! (የዲሞክራሲ አገር ነዋ)
ሰሞኑን ቴሌቪዥን ተመልክታችኋል ብዬ እገምታለሁ (ፓርላማ በኢቴቪ ማለቴ እኮ ነው!) አንዳንድ ወገኖች ምን እንደሚሉ ታውቃላችሁ? “ፓርላማም ኢቴቪም አያዝናኑም!” በእርግጥ ኢቴቪ አያዝናናም በሚለው እኔም እስማማለሁ (እንኳን እኔ ኢቴቪም ይስማማል!) እኔን ያልገባኝ ምን መሰላችሁ? ፓርላማው አያዝናናም የተባለው ጉዳይ ነው፡፡ እንዴ — የት አገር ነው ፓርላማ የሚያዝናናው? የየትም አገር ፓርላማ እኮ (ሲንጋፖርና ታይዋንን ጨምሮ) ትላልቅ የአገር ጉዳዮች የሚታሹበትና የሚፈተጉበት እንዲሁም ህግ የሚወጣበት እንጂ ሰርከስ የሚቀርብበት የመዝናኛ ፕሮግራም አይደለም፡፡
በነገራችሁ ላይ በፓርላማ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፤ በክላስተር ስለተሾሙት ባለስልጣናት ጉዳይ ላነሱት ጥያቄ ጠ/ሚኒስትር ኃይማርያም ሲመልሱ፣ ክላስተር በእኛ አገር የተጀመረ ሳይሆን በሲንጋፖርና በታይዋንም እየተሰራበት እንደሆነ አስረድተዋል (እንደ ፀረ ሽብርተኝነት ህጉ ቃል በቃል የተቀዳ ነው ባይሉም!)
ፓርላማው የመዝናኛ ፕሮግራም አይደለም ብንልም ትንሽ ዘና የሚያደርግ ነገር ቢታከልበት ግን ብዙ ተከታታይ ያገኛልና ቢታሰብበት አይከፋም፡፡ እኔ የምለው ግን— አንዳንዴ እንኳን ምናለ ኢቴቪ ሳቅ በኢፌክት ቢጨምርበት! የፓርላማ ፕሮግራም ላይ እንጂ ዜና ላይ አልወጣኝም (ካልሆነ እኮ ከሰራዊት ፍቅሬ ቶክ ሾው ተመክሮ መውሰድም ይቻላል) አያችሁ– ፖለቲካ “የቻይና ቋንቋ” የሚሆንባቸው አንዳንድ ወገኖች ስላሉ የሚያስቅ ነገር ቢኖር በእሱ እያዋዙ ይውጡታል – ፖለቲካውን! እንደውም ትዝ ይላችሁ እንደሆነ — ከአንድ ከሁለት ዓመት በፊት ፓርላማ ውስጥ አዝማሪና ገጣሚዎች እየገቡ በየመሃሉ ያዝናኑ የሚል ሀሳብ ሰንዝሬ ነበር (እንደመድረክ ፓርቲ የሰማኝ የለም እንጂ) አሁንም ግን አልረፈደም፡፡ እንደውም ያ ሃሳቤ በትክክል መተግበር ያለበት አሁን ይመስለኛል። እንዴ — ፓርላማ ውስጥ እንኳን ሳቅ ደረቅ ፈገግታ እንኳ ጠፋ እኮ! እኔ የምለው— የኢህአዴግ የምክር ቤት አባላት ለጠ/ሚኒስትሩ የሚያቀርቡትን ጥያቄዎች ፓርቲው አዘጋጅቶ ነው አይደል የሚያከፋፍላቸው? (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ!) እናላችሁ –ለምንድነው የጥያቄው ወረቀት አንዳንድ ቦታ ላይ (ሳቅ) የሚል በቅንፍ የማይፃፍበት? አንዳንዴ በትእዛዝም ቢሆን እንዲስቁ ብዬ እኮ ነው! (ሳቅ ሲጠፋስ?)
እኔ የምለው ግን … ኢህአዴግ ትንፍሽ ላለው ነገር ሁሉ ምላሽ መስጠት የግድ ነው እንዴ? (አንድ ያስቸገረኝ ወዳጅ አለ) ይገርማችኋል — “ነውጠኛ” ነው (የጐዳና ነውጥ ግን አይወድም!) እናላችሁ — አንድ የኢህአዴግ አመራር በፓርላማ ወይም በሬዲዮ አሊያም በቲቪ ወይም ደግሞ በፕላዝማ ወይም በዩቲውብ ከተናገረ በቃ … ወኔው ይመጣበታል፡፡ ራሱን እንደተቋም ነው መሰለኝ የሚመለከተው ቁጭ ብሎ ደብዳቤ ይፅፋል – ለኢህአዴግ ምላሽ መሆኑ እኮ ነው! ኢህአዴግን አላወቀውም — እንኳን ለፅሁፍ ለተቃዋሚዎችስ መች ተበገረ!
አሁን እንግዲህ ወደ ዋናው አጀንዳ እንዝለቅ፡፡ ቆይ ግን —- የጠ/ሚኒስትሩን የፓርላማ ማብራሪያ እንዴት አያችሁት? አንዱ የኢህአዴግ “ፍሬሽ ካድሬ” ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ? “ትንሽ ማስቦካት ይቀረዋል እንጂ ደህና ነው!” ብሎኝ ቁጭ አለ (ካድሬው ምን ነካው?) አያችሁልኝ … ይሄ ጀማሪ ካድሬ እንዴት እንደሚያስብ! ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ግን ሁሉም እንደሳቸው እየመሰላቸው “ማተምያ ቤት ስልክ እየደወሉ የእገሌን ጋዜጣ እንዳታትሙ የሚሉ የመንግስት ደሞዝ ተከፋዮች አሉ” ሲባሉ “አብዳችኋል እንዴ? ነፃ አገር እኮ ነው!” ይላሉ፡፡ በነገራችሁ ላይ ካሁን በኋላ ስልክ እየደወሉ የእገሌን ጋዜጣ አታትሙ የሚሉ ባለስልጣናት ስለማይኖሩ ማተምያ ቤቶች መፍራት የለባቸውም (ጠ/ሚኒስትሩ የዲሞክራሲ አገር ነው ብለዋላ!)
እናላችሁ — ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ “ማስቦካት”ን እንደ አመራር ጥበብ የሚቆጥሩ ካድሬዎች ባሉበት አገር “ጥያቄ ውስጥ የሚገባ የዲሞክራሲ አስተሳሰብ” እንደሚነግስ ለአፍታም መጠራጠር የለባቸውም፡፡ እኔ የምለው … ስለ ስኳርና ጤፍ ተጠይቀው ምን ነበር ያሉት? “እጥረት ያጋጥማል እንጂ ጠፍቶ አያውቅም” አሉ ልበል? (ኸረ እንኳንም አልጠፋ!) ግን እኮ … የጤፍ ዋጋ ያልቀነሰው ምርቱ ጤፍ ከሚመገበው ሰው ጋር ባለመመጣጠኑ ነው ያሉ መሰለኝ (ቢሆን ነዋ!) እንግዲህ እኛ ከሳቸው አናውቅም! እኛ የምናውቀው ምን መሰላችሁ? በቀደም ዕለት ለጤፍ ዋጋ አለመቀነስና ለእጥረቱ ጉዳይ መፍትሄው ምን እንደሆነ ሳይነግሩን ከፓርላማ መውጣታቸውን ብቻ ነው (ከሃላፊነት መሸሽማ የለም!)
ባለፈው ጊዜ ዘይትና ስኳር ጠፋ ተብሎ “ፒፕል” ሲንጫጫ፣ አንድ ሥልጣናቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የመንግስት ሃላፊ በቲቪ መስኮት ብቅ አሉና “የስርጭት ችግር እንጂ የአቅርቦት ችግር የለም!” ብለውን አረፉት (ቢሆን ነው ብለን ዝም አልን!) እኔ የምላችሁ ግን—- ካርድ ወሰዳችሁ እንዴ? የፓርቲ አባልነት እኮ አይደለም — የምርጫውን ማለቴ ነው! ጠ/ሚኒስትሩ ተቃዋሚዎች ለአዲስአበባና አካባቢ ምርጫ ትኩረት ለምን እንደማይሰጡ ሲያስረዱ ምን ነበር ያሉት? ከምርጫ በኋላ የሚያስገኘው ጥቅም ስለሌለ ግዴላቸውም ያሉ መሰለኝ ! ግን እኮ ጥቅም ከሌለው ምንም አይሰራም (ለሲቪ ብቻ?) ለማንኛውም ግን አሁን “መድረክ” ሳይቀር በምርጫው እሳተፋለሁ እያለ ስለሆነ ውዝግቡን ትንሽ ረገብ ያደርግልናል ብዬ አስባለሁ፡፡
የምርጫ ነገር ከተነሳ አይቀር የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ፣ ለአንድ ጋዜጣ በሰጡት ቃለምልልስ ላይ የተናገሩትን ባካፍላችሁ ደስ ይለኛል (ንግግራቸው ልቤን ስለነካኝ እኮ ነው!) ቦርዱ ለገዢው ፓርቲ የማድላት ነገር ይታይበታል የሚል ስሜት የሚያንፀባርቅ ጥያቄ ሲጠየቁ ምን አሉ መሰላችሁ? “ፓርቲዎችን እንደልጆቼ ነው የማያቸው” (“ሳላበላልጥ በእኩል ዓይን” ለማለት እኮ ነው) አንድ ጠማማ ወዳጄ ግን “እንዴ ሳይወልዷቸው?” አይለኝ መሰላችሁ፡፡ እኔን ከሁሉም ያስደሰተኝ ግን ምን መሰላችሁ? “ኢህአዴግ አውራ ፓርቲ ነኝ” ይላል ሲባሉ የሰጡት መልስ ነው “እኔ አውራና ደካማ ፓርቲ አላውቅም፣ ሁሉም ለእኔ እኩል ናቸው!” በማለት መልሰዋል (ደስ አይሉም?)
እኔ ግን ይቅርታ አድርጉልኝና አንዳንዴ ኢህአዴጐች ደስ ይሉኛል፡፡ ለምን በሉኛ – በቃ ከላይ እስከታች ቃላቸው አንድ ነው! በአንድ ጉዳይ ላይ የፓርቲው ሊ/መንበር፣ ምክትል ሊ/መንበር፣ የፅ/ቤት ሃላፊ፣ ፀሃፊ፣ካድሬ ወዘተ — የሚሰጡት መልስና ማብራርያ በሚያስገርም ሁኔታ አንድ ነው (ሌባ የማይሰርቃቸው!) ቆይ ማስረጃ ልጥቀስላችሁ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ሰሞኑን ፓርላማ ውስጥ ተገኝተው ጋዜጦችን አናትምም ስለሚሉ ማተምያ ቤቶች የሰጡትን ምላሽ ሰምታችኋል አይደል? ከዚህ ቀደም የኢህአዴግ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ሬድዋንና የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በዚሁ ጉዳይ ዙርያ ተጠይቀው የሰጡትን ማብራርያ እኮ ነው የደገሙት (በቃ አንድ ነው ስላችሁ!) ሌላ ማስረጃ ልጨምርላችሁ እንዴ? (እንድንተማመን ማለቴ ነው!) ጠ/ሚኒስትሩ ተቃዋሚዎች ሁልጊዜ ለአካባቢ ምርጫ ትኩረት እንደማይሰጡና ለአገራዊ ምርጫ ግን እንደሚተራመሱ ሲናገሩ ሳትሰሙ አትቀሩም። ባይገርማችሁ … አቶ ሬድዋንም እዚሁ ጋዜጣ ላይ በሰጡት ቃለምልልስ፤ ተቃዋሚዎች በአገራዊ ምርጫ እንጂ በአካባቢ ምርጫ የመሳተፍ እምብዛም ፍላጐት እንደሌላቸው በተመሳሳይ ቃና ገልፀው ነበር። አያችሁልኝ … ኢህአዴጐች ሲባሉ ቃላቸው አንድ እንደሆነ! ዲሞክራሲ በሚል ተልካሻ ምክንያት እያንዳንዱ አመራር ያሻውን መዘባረቅ አለመደባቸውም (የፓርቲው ባህል አስቀናኝ!) ትንሽ ግራ ያገባኝ ምን መሰላችሁ? ከትላንት በስቲያ ማታ የምርጫ ቦርዱ ሃላፊ ለኢቴቪ በሰጡት መግለጫ፣ተቃዋሚዎች ለአገራዊ ምርጫ ሲሆን እንደሚተራመሱና ለአካባቢ ምርጫ ግን ደንታ እንደሌላቸው በመናገር የኢህአዴጎችን ቃል መድገማቸው ነው (እናት ክፍላቸው ለየቅል ነው ብዬ እኮ ነው!) ለማንኛውም ግን በበዓል ዋዜማ ላይ ነንና ለኢህአዴግም ለተቃዋሚዎችም ለምርጫ ቦርዳችንም እንዲሁም ለመራጮች ሁሉ መልካም የገና በዓል እመኛለሁ!!
source: http://www.addisadmassnews.com

No comments:

Post a Comment