Saturday, January 5, 2013

በኬንያ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ከተማ ልቀቁ ተባሉ


Dadaab refugee camp, Kenya
ወቅቱ 2003 አጋማሽ ላይ ነው። ሁለት የኢህአዴግ ሰዎች ድንበር አቋርጠው ናይሮቢ ይገባሉ። በናይሮቢ አድርገው ወደ ሌላ አገር ለመኮብለል ጊዜያዊ ማረፊያ መጠነኛ ሆቴል ይከራዩና ለሁለት አንድ ላይ ያርፋሉ። አንደኛው ከሰዎች ጋር ቀጠሮ እንዳለው አስታውቆ ወደ ጉዳዩ ይሄዳል። ቀጠሮው ቦታ ቆይቶ ለጓደኛው ስልክ ሲደውል “እንዳትመጣ፣ ጓደኛህን ከተኛበት ገብተው የማይታወቁ ሰዎች ወስደውታል” የሚል መልዕክት ይደርሰዋል። ከዚያን ቀን ጀምሮ ስለጓደኛው ሰምቶ አያውቅም። እሱም አገር ቀይሮ በስደት በመንከራተት ላይ ይገኛል።
ኬንያ ሶስት ዓይነት ስደተኞች አሉ። በኢኮኖሚ ድቀት የዕለት ጉርስ ፍለጋ የሚሰደዱ፣ በፖለቲካ ሳቢያ ኢህአዴግን ሽሽት አገር ለቀው የወጡ፣ በኢህአዴግ ልዩ ተልኮ ስደተኛ መስለው ኬንያ የሚኖሩ፤ ከናይሮቢ በስልክ ለጎልጉል መረጃ የሰጡት ወገኖች እንደደሚሉት በየጊዜው እየታፈኑ ወደ አገርቤት የሚላኩ ጥቂት አይደሉም። ይህ የሚሆነው ደግሞ በኬንያ ውስጥ ኢህአዴግ እጀ ረጅም በመሆኑ ነው። በዚህም ሳቢያ ለፖለቲካ ስደተኞች እያንዳንዷ ቀን የሰቀቀን ነች። ራስን የመጠበቅ!!
የኬንያ መንግስት “ለደህንነቴ ቅድሚያ” በሚል ሰሞኑንን ያስተላለፈው መመሪያ በስደት ናይሮቢ የሚኖሩትን ወገኖች ያስደነገጣቸውም ለዚሁ ነው። በኬንያ የሚኖሩ ስደተኞች ከተማ ለቅቀው ወደ ካምፕ እንዲገቡ በተላለፈው ትዕዛዝ መሰረት መመሪያው የሚመለከታቸው ኢትዮጵያዊያን የመፍትሄ ሃሳብ የላቸውም። ግን ጭንቀታቸውን ለማሰማት ያህል ይናገራሉ።
በናይሮቢ የዓለም የስደተኞች ኮሚሽንን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ካሉት ስደተኞች መካከል አንዱ ብርሃኑ በየነ ይባላል። በዝዋይ ማረሚያ ቤት ታስሮ ተገርፏል። እሱ እንደሚለው የኬንያ መንግስት ሁሉንም ስደተኞች ባንድ መነጽር ሊመለከት አይገባም። በጅምላ ከዘጠኝ አገሮች ተሰድደው ኬንያ ለገቡት ጥገኝነት ጠያቂዎች በግል የፋይል ቁጥራቸው ወደ ካምፕ እንዲገቡ መመሪያ ተላልፏል።
በአዲሱ ዓመት ግርግር ጉዳዩ ተጓተተ እንጂ መመሪያው ተግባራዊ መሆኑ አይቀሬ ነው። የስደት ማመልከቻቸውን አስገብተው በተባበሩት የስደተኞች ኮሚሽን እውቅና ናይሮቢ እንደፍጥርጥራቸው ተቀምጠው ጉዳያቸውን የሚከታተሉም ሆኑ፣ በስደት ካምፕ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ከቀላል የርስ በርስ ጸብ በስተቀር በወንጀል፣ በግድያና በጸያፍ ተግባር አይታወቁም። ከዚህም በላይ ለናይሮቢ ነዋሪዎች ስጋት የሚሆኑበት አንድም አግባብ እንደሌለ ብርሃኑ ያስረዳል።
በኬንያ ስደት ካምፖች ሙቀታቸው ከፍተኛ፣ ለመኖሪያ የማያመቹ፣ ለአካባቢ ወለድ በሽታዎች የተጋለጡ፣ በቂ የመኖሪያ ግብአት ያላሟሉ ከመሆናቸው በላይ ትልቁ ችግር የደህንነት እንደሆነ ያመለከተው ብርሃኑ አብዛኞችን ስጋት ላይ ስለጣለው ጉዳይ “ተመሳስለው በስደተኛ ስም ኬንያ የገቡት የኢህአዴግ የስለላ ሰዎች በየቀኑ ሰዎችን ያድናሉ። ወደ ኢትዮጵያ ይወስዳሉ። በዚህ መልኩ የታፈኑ በርካታ ናቸው። አንድ ላይ ተሰባስበን እንዴት እንቀመጣለን? ይህ እጅግ አሳሳቢና ከፍተኛ መዘዝ የሚያስከትል የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው” ሲል የኬንያ መንግስት ውሳኔውን ሊያጤን እንደሚገባው ያሳስባል።
ይህ ብቻ አይደለም በኬኒያ ያለው ሙስናም ሌላው ስጋት ነው። “በኬንያ ገንዘብ ካለ ሁሉንም ማድረግ ይቻላል። ኢህአደግ ገንዘብ አለው። ገንዘብ ከተከፈለ ዋስትናችንን አሳልፎ የመስጠት ውሳኔም ሊወሰን ይችላል” የሚለው ግርማ ጉተማ “ኦነግን ፍርሃቻ በየስርቻው የሚንቀሳቀሰው ኢህአዴግ ይጥቀመው እንጂ ማንኛውንም ነገር የማድረግ ሞራል ስላለው ዋስትናችን የተመናመነ ያህል ይሰማኛል” ይላል።
ሁሉም እንደሚሉት የኬንያ መንግስት ውሳኔውን ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ድምጻቸውን በያሉበት ሆነው ሊያሰሙ ይገባል። በየአቅጣጫው ጉዳዩን በማስመልከት ለኬንያ መንግስትና ለሚመለከታቸው ክፍሎች የስጋቱን ደረጃ ማሳወቅ ለነገ የማይባል አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነ አበክረው ያስረዳሉ። በኬንያ ከደቡብ ኢትዮጵያ፣ ከአማራና ከኦሮሚያ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር አብላጫውን ቁጥር ይይዛል።
Dadaab refugee camp, Kenya
ዳዳብ የስደተኞች ካምፕ ኬኒያ ሐምሌ 2003(ፎቶ:AlertNet)
በኬንያ በተደጋጋሚ በደረሰ የቦንብ ጥቃት ሳቢያ ዜጎች ከስደተኛ የሶማሌ ዜጎች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውና፣ የሶማሌ ዜጎችን በመቃወም የኬንያዊያን ጥያቄ ገፍቶ በመምጣቱ መንግስት ሁሉም ስደተኞች ወደ ካምፕ እንዲገቡ የሚያስገድድ መመሪያ አውጥቷል። የኬንያ የመከላከያ ሃይል በሶማሌ የአልቃይዳንና የአልሸባብን ሃይል ከዩጋንዳ፣ ከብሩንዲና ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር በመሆን ማጥቃቱ ለቦንብ አደጋው እንደ ምክንያት ቢገለጽም፣ የኬንያ መንግስት ውሳኔውን ያሳለፈው አጠቃላይ አገሪቱ ውስጥ ለገቡት ስደተኞች ሁሉ ነው።
በዓለም ትልቁ የሚባለውና አብዛኛዎቹ ከሶማሊያ የሚመጡት ስደተኞች የሚገኙበት የዳዳብ ካምፕ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን የሚገኙ በመሆናቸው ተጨማሪ ስደተኞችን ሊጨምር ባይችልም ሌሎች አዳዲስ ካምፖችን በማሰራት ስደተኞችን ወደዚያው ለማጎር እየታሰበ እንደሆነ ከኬኒያ የሚወጡ ዜናዎች ይጠቁማሉ፡፡

No comments:

Post a Comment