Tuesday, January 1, 2013

በ”ሜጋ” የታክስ አከፋፈል የቀድሞ ስ/አስኪያጅ አቶ እቁባይ በርሄ ታሰሩ



አቶ እቁባይ “ገመና” የቴሌቪዥን ድራማ በማሰናዳትና በማቅረብ ይታወቃሉ
በኢህአዴግ ገንዘብ ከተቋቋሙት የንግድ ተቋማት መካከል አንዱ በሆነው ሜጋ ኢንተርፕራይዝ፣ የገቢ ግብር፣ የሰራተኞች ታክስ እንዲሁም ቫት ተሟልቶ አልተከፈለም በሚል በቀረቡ ሶስት ክሶች የቀድሞ ስራ አስኪያጅ አቶ እቁባይ በርሄ ሃሙስ ጥፋተኛ ነህ ተብለው ታሰሩ።
ሜጋ ኢንተርፕራይ ወደ 40 ሺ የሚጠጋ የትርፍ ግብር ሳይከፍል እንደቀረና ይህም ገቢውን በማሳነስ የተፈፀመ እንደሆነ የሚገልፅ ነው አንደኛው ክስ። ሌላኛው ክስ፤ አራት መቶ ሺ ብር የቫት ክፍያን የሚመለከት ሲሆን፤ ሶስተኛው ክስ ከሜጋ ኪነጥበባት ማዕከል ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተገልጿል።
ሜጋ የኪነጥበባት ማዕከል ከሜጋ ኢንተርፕራይዝ ጋር የተያያዘ አመሰራረት ቢኖረውም፤ ከኢንተርፕራይዙ እንዲነጠል ተወስኖ ሳይቋጭ ቆይቶ ነበር የሚሉ ምንጮች፤ በሰራተኞች ታክስ አከፋፈል ላይ ጥያቄ አስነስቷል ይላሉ። ከሰራተኞች ደሞዝ መቆረጥና መከፈል የነበረበት ታክስ ገቢ አልሆነም በሚለውም ክስ አቶ እቁባይ ጥፋተኛ ናቸው ተብሎ ተወስኖባቸዋል።
አቶ እቁባይ በርሄ ከሜጋ ኢንተርፕራይዝ በ2001 ዓ.ም በመልቀቅ በግል ስራ የተሰማሩ ሲሆን፤ ገመና የተሰኘውን ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በማሰናዳትና በማቅረብ ይታወቃሉ። በሜጋ ኢንተርፕራይ የታክስ ክፍያ ላይ ክስ የቀረበው ከ1997 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም ያለውን ጊዜ እንደሚሸፍን ተጠቁሟል። የቅጣት ውሳኔ ለመጪው ሃሙስ በቀጠሮ ተላልፏል።
በኢህአዴግ ገንዘብ የተቋቋሙ የንግድ ድርቶች ከመንግስት አድልዎ ያገኛሉ በሚል በተደጋጋሚ የሚሰነዘሩ ወቀሳዎችና ትችቶች በሜጋ ላይም ሲቀርቡ እንደነበር ይታወሳል። 
በ1997 ዓ.ም ከዋና ዋና የምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የነበረው ቅንጅት፤ ሜጋ ታክስ አይከፍልም በሚል ውንጀላ ሰንዝሮ ነበር።

No comments:

Post a Comment