ይድረስ ብልፅግናና ነፃነትን በትልቅ አገር ውስጥ የመገንባት ዕይታ ላላቸው ሁሉ!ሽንቁር ስናሳድድ ጋኑ እንዳይፈነዳ!
ስለአምስት ዓመቱ ፀረ ፋሽስት የአርበኝነት ትግል የሚያወሳ አንድ መጽሐፍ እያነበብኩ ነበር፡፡
ሌላውን ቀዳሚ ዘመን ልተወውና በአምስት ዓመቱ ቆይታ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ወንድና ሴቱ፣ መከራ እየጠበሰና የማይበላ እየበላ የተሳተፈበት የአርበኝነት ትግል፣ እኔና የዛሬው ትውልድ የቱን ያህል በደምና በአጥንት ላይ እንደተቀመጥንና ለአገሬ የአቅሜን ሠርቻለሁ ወይም ለውጥ አምጥቻለሁ ባይነታችን ለዚች አገር እጅግ እንደሚያንስ የተማርኩበት ነበር፡፡ በዚህ ትምህርት ተደምሜና ኩራቴ ተሸማቆ እያለ የኢትዮጵያ መንግሥት የአቶ መለስ ዜናዊን ሞት ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. በይፋ ገለጠ፡፡ የአገሬ ሕዝብ በጭምጭምታ ሰምቶ የጨረሰው ቢሆንም ብሶቱን ውጦ፣ ያሁኑን ከወደፊቱ አገናዝቦና የመለስ ዜናዊን ደግ ደጉን አስተውሎ ያሳየው ሐዘን ደግሞ ሌላ አስደማሚ ትምህርት ሰጠኝ፡፡ የኢትዮጵያ የጠብ ፖለቲካ ለዚህ ሕዝብ ምን ያህል እንደጠበበው እንድገነዘብና አንገቴን እንድሰብር አደረገኝ፡፡ ልቦናችንን ካልደፈንን በቀር ትምህርቱና ኃፍረቱ ከላይና ከሥር ያሉትን ፖለቲከኞች ሁሉ የሚመለከት ነው፡፡
ከ1968 ዓ.ም. አንስቶ የፍጥጫ ፖለቲካ ውስጥ ከገባን 37 ዓመታት አደረግን፡፡ ሕዝብ ግን በእኛ ፖለቲካ እንደማይመዘንና ከእኛ ፍጥጫ በላይ እንደሆነ አስመሰከረ፡፡ ለሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ ሳይሆን መተማመኛ ለሌለው ለራሱ ኑሮም አዘነ የባሰ እንዳይመጣ፡፡
የማወራለት ሐዘን ከአስከሬን አቀባበል እስከ ቀብር በመንግሥት ስለተቀናበረው ተራ በተራ ቤተ መንግሥት የመድረስ፣ ሠልፍ የመውጣትና በአደባባይ ሻማ የማብራት ምደባ ስለተካሄደበት፣ ፎቶ ያለበት ካኒቴራ በመቶ ብር ግዙ እየተባለ ስለታዘዘበት፣ ቅን ሐዘን በፕሮፓጋንዳነት ተጎሳቁሎ ለታለ አይሰጥ ኑሮ ከዚህ በላይ እንባ ሲበዛ ተብሎ ስለተተረተበት የሰሜን ኮሪያን የመሰለ የሐዘን ትርዕይት አይደለም፡፡ የማወራው በየደረስኩበት የተመለከትኩትን፣ ቀደም ብሎ እህል እየሸመተ እንዴት እንሆን ይሆን እያለ ሲጨንቀው የነበረ ሰው በየቤቱና በየመንገዱ ከልቡ ይገልጽ ስለነበረው ስሜት ነው፡፡ በጣም መራር ብሶት የነበራቸው ሰዎች እንኳ በጠቅላይ ማኒስትሩ ሞት ደንግጠው ከእሱ የተሻለ ሰው ከቀሪዎቹም ከተቃዋሚዎቹም ማን አለ ብለው ሲጨነቁ ተመልክቻለሁ፡፡ ከአቶ መለስ ያልተጠበቀ ሞት በኋላ እንዴት እንሆናለን የሚል ጭንቀት የፈጠረው በሕዝብ ውስጥ ብቻ አልነበረም፡፡ የመንግሥትም ሰዎች ጭንቅ ውስጥ እንደነበሩ የሚጠቁሙ ምልክቶች አሉ፡፡ የሞቱን ተደብቆ መሰንበት ወሬና ሌላ ሌላውን ትተን የሕዝቡ በጎ ምላሽ የፈጠረባቸው ግርምትና እፎይታ ብቻውን ለማሳያ ያህል በቂ ነው፡፡
የሕዝቡም ሆነ ሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ጭንቀት አልፎ ሂያጅ ንፋስ አይደለም፡፡ እውነተኛ መሠረት ያለውና ያላበቃለት ነው፡፡ ከዝምታችን፣ ከሰላማችንና ከመቻቻላችን ሥር በቁጥጥርና በፕሮፓጋንዳ እየተድበሰበሰ የቆየ ረመጥ አለ፡፡ ለሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለታዘነ፣ ሐዘኑ ለፕሮፖጋንዳ ሽመና ውሎ የስም ግንባታ ሐውልት ኅብረተሰቡ ኅሊና ውስጥ ለማነፅ ወይም በመለስ የመሐንዲስነት ውዳሴ ውስጥ ለመጠለል ስለተሞከረ፣ ከሰባትና ከስምንት ዓመታት ወዲህ የመጣ ልማት የ21 ዓመት እንዲመስል ተደርጎ ስለቀረበ፣ ልማቱን የማፋጠን ተግባር ለራሳችን ሳይሆን የሟቹ ራዕይ ከንቱ እንዳይቀር ብለን የምንሠራው እስኪመስል የተጠናከረ ቃል ኪዳን ያጎረፈ የፕሮፖጋንዳ ስጋጃ ስለተሸከሸከ ከሥር ያለው ረመጥ አይጠፋም፡፡ እንደ በፊቱ ብሶቶች እንዳይወጡ ፕሮፓጋንዳ ማልበስና በተንሰራፋ ቁጥጥር ሽንቁሮችን እየተከታተሉ መጠቅጠቅ ከቀጠለ ሄዶ ሄዶ ጋኑ እንዳይፈናዳ ቤት እንዳይቃጠል ያሳስባል፡፡ ድንገቴዎች መቼ እንደሚከሰቱና ምን ይዘው እንደሚመጡ እንደማይታወቅ የአቶ መለስ ሞት ምስክር ነው፡፡ ስለዚህ የገዢው ፓርቲ ወገኖች በፀጥታ መረባቸውና በፕሮፓጋንዳ ምርታቸው ሳይዋጡ ተቃዋሚዎችም ከመንግሥት ይምጣ ሳይሉ ለትግግዝ ፊታቸውን ሊመልሱ ይገባል፡፡
ከፕሮፓጋንዳ ስጋጃው ሥር ምን ይንተከተካል?
በቤት ኪራይ፣ በቀለብ፣ በትራንስፖርት፣ በጤና፣ ወዘተ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዋጋዎች የሚያረጁበትና ሰው ምኑን ከምኑ እያደረገ ነው የሚኖረው ያሰኘው የኑሮ ውድነት አገሪቱን የወጠረ አንድ ዓብይ የብሶት ምንጭ ነው፡፡ ስንዴና ዘይት በሸማቾች ሱቆች በማከፋፈል ዘርፈ ብዙ ውድነትን ለማስታገስ ‹‹መሞከርና›› የየወሩን የዋጋ አጨማመር ካለፈው ዓመት ጋር እያነፃፀሩ ‹‹ንረት ቀነሰ›› እያሉ መለፈፍ በተጋጋመ እሳት ላይ ተጋድሞ ከመዘባነን አይለይም፡፡ ብሶቱ እንዳይወጣ የቱንም ያህል አፈና ቢካሄድ የኑሮ ውድነቱ እየጨመረ መሄዱ የብሶቱንም ክረት ስለሚያሳድግ ሄዶ ሄዶ አፈና የሚዘነጠልበት ቀን መምጣቱ አይቀርም፡፡ ከዚያ በፊት በቶሎ ውድነትን የምር የሚያቀልል መፍትሔ ማበጀት ብልህነት ይሆናል፡፡
ከመንግሥት ተቀፅላነት የወጣ ነፃ የሕዝብ እንቅስቃሴን በቀሰፈ አጠቃላይ የመብቶች አፈና ውስጥ ከሌሎቹ የነፃነት ብሶቶች ይበልጥ በዛሬው ሰዓት ፊት ለፊት የሚወራጨው በሃይማኖቶች ውስጥ ባለው የመንግሥት ጥልቅ ባይነት የተመረረው ብሶት ነው፡፡ ይህንን ብሶት በተለመደው የፀጥታ አፈናና ‹‹ከጥያቄዎቹ በስተጀርባ ፖለቲካዊ ዓላማ አለ››፣ ‹‹ሃይማኖትን ሽፋን አድርጎ አመፅ ለማስነሳት ነው›› ወይም ‹‹የአክራሪነት አደገኛ እንቅስቃሴ ነው›› እያሉ ስም በመለጠፍና በማሰር መታገል፣ በኦርቶዶክስ ክርስትናም ሆነ በእስልምና የእምነት መሪዎች አመራረጥም ውስጥ እጅን በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር ሰዶ አቦካለሁ ቢባል ውጤቱ መመለሻ ላይኖረው ይችላል፡፡ ኃላፊነት የሚሰማውና አስተዋይ አዕምሮ ያለው፣ አንድ ግጭትና ግድያ ምን ያህል (እንደ ኬንያ ሞምባሳ) የጣጣ ሰበብ ልትሆን እንደምትችል፣ የአንድ ብሶት ፍንዳታ ከሌሎች ብሶቶች ጋር ተላልሶ ሊያጥለቀልቅ እንደሚችል ይመለከታል፡፡
እኔ የፈቀድኩልህን እምነት፣ አለባበስና አኗኗር ካልተከተልክ ወዮልህ የሚል ሃይማኖታዊ አፋኝነት ኅብረተሰብን እንዳያብጥ መከታተል ኃላፊነት ነው፡፡ እስልምናን ያነገበ አፋኝነት አገራችን ውስጥም እንደገባና ከዚህ በፊት ጥፋት እንዳደረሰም የሚታወቅ ነው፡፡ ገና ወደፊትም ምዕራባዊ ጣልቃ ገብነትም ሆነ ውስጣዊ ኋላ ቀርነትና መናጨት የሚፈጥረውን አለመረጋጋት መራቢያ እየደረገ መፈታተኑ አይቀርም፡፡ ለዚህ ማገጃ ቢሆነኝ ብሎ አፈናን መጠቀም የ‹‹አክራሪነት›› ረዳት ከመሆን አይተናነስም፡፡ የሃይማኖት ሰላምን ለማረጋገጥም ሆነ ወደ መካከለኛ ዘመን ሊመልስ የሚሞክር ‹‹አክራሪነትን›› መጠጊያ ለማሳጣት፣ መድኃኒቱ ሃይማኖቶች መንግሥት የጠላውን እንዲያወግዙ፣ የወደደውን እንዲያሞግሱ (አጨብጫቢ እንዲሆኑ) ከማድረግ መራቅና አደረጃጀትና አንቅስቃሴያቸውን ከመቆጣጠርና ከመዘወር መቆጠብ፡፡ የእምነቶችን እኩልነትና መከባበር በተግባር ማረጋገጥ (እንደኋላ ቀር እየታዩ ‹‹ባህላዊ እምነት›› ለሚባሉት ጭምር)፤ ብዙ ሃይማኖቶች ባሉበት ይቅርና አንድ ሃይማኖት ባለበትም አገር ቢሆን መንግሥትና ሃይማኖት ተጋብተው ንዑስና ክፍልፋይ እምነቶች በእኩልነት አስተናግደው የማያቁበትን (የትናንትም የዛሬም) ታሪካዊ ሀቅ በማኅበራዊ ግንዛቤነት ፅኑ መሠረት ማስያዝ ነው፡፡ ፀረ ምዕራብ አሸባሪነት በአንድ በኩል፣ ምዕራባዊ ጣልቃ ገብነትና እስልምናን እንደ አደጋ የመመልከት አባዜ በሌላ በኩል እየተተነኳኮሱ አንዳቸው ሌላቸውን በሚያባብሱበት ዓለም ውስጥ፣ እጅግ ብርቅ የሆነው የአገራችን የሃይማኖት ሰላሳ መዝለቅ የሚችለው በዚህ አያያዝ ነው፡፡ ከአፈና ወጥቶ እዚህ ዲሞክራሲያዊ አያያዝ ውስጥ አለመግባት የአገሪቷ ሰላም እንዲቆስል መተው ይሆናል፡፡
በራሳቸው ለማጥለቅለቅ አቅም የሌላቸው በግርግር አጋጣሚና አራጋቢ ካገኙ ግን በቀላሉ ተጋግመው የማይፈለግ ውስብስብ ሊፈጥሩና አቅጣጫ ሊያስቱ የሚችሉ ችግሮችም አሉ፡፡ ከተዛባ አገዛዝ የበቀሉ ክልል ገብና ክልል ዘለል ተገፋን/ተበለጥን የሚሉ የብሔር /የጎሣ ቅሬታዎች፣ ‹‹መጤ›› እና ‹‹በቀል›› የሚሉ ግልብ ፍረጃዎች አሉ፡፡ አድሎዎቹና ከፋፋይ አመለካከቶቹ እስካልተቃኑ ድረስም ቅሬታዎቹ የውስጥ ለውስጥ ኑሯቸውን ይቀጥላሉ፡፡ የወሰንና የመሬት ይዞታን የተመለከቱ ውዝግቦች፣ ከሰፈራና ከሰፋፊ መሬት ኪራይ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎችም ተጠምዝዘው ከብሔር/ጎሣ ነክ ቅያሜዎች ጋር ሊቀላቀሉና የግጭት መሳበቢያና መክፈቻ ለመሆን የተጋለጡ ናቸው፡፡
ከዚህ እልፍ ሲባልም፣ ዘመናቸው ያለፈና በፖለቲካ የመርታት አቅማቸው የከሰረ ቢሆንም የመነጠል ዓላማ ያላቸው እንቅስቃሴዎችም አልታጡም፡፡ ለመነጠል ትግል መክሰር ከዛሬዋ ኤርትራና ከኦነግ ታሪክ በላይ ተጨማሪ ማሳያ አያስፈልገንም፡፡ ስለ ኦነግ ክስረት ለማስተዋል ሌንጮ ረታ (የቀድሞ የኦነግ አመራር አባል) በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ተጠይቆ የአርባ ዓመት የትግል ዘመንን ኦሮሞ የሚባል ብሔር በኢትዮጵያ መኖሩን ለዓለም ከማሳወቅና በሽግግር መንግሥት ከመሳተፍ ውጤት ጋር ካስተያየበት ንግግር በላይ ምስክር አያስፈልገንም፡፡ ከኦነግና ከአሮጌ መንገዱ መንኮታኮት በኋላ ተመሰቃቅላ የመከራና የሥርዓት አልባነት ምርጥ ምሳሌ የነበረችው የሶማሊያ ልምድ የዓመታት ትምህርት እየሰጠም ሳለ፣ በነፃነት ስም በጠመንጃና በፈንጂ የኦጋዴንን ሰላም የሚያምስ ቡድን ማኅበራዊ መደበቂያ ማግኘት ባልነበረበት ነበር፡፡ ያልነበረበት እንዲኖር እስትንፋስ ሲሰጥ የቆየው አገዛዙ ነው፤ የንግግር መፍትሔን፣ የተቃውሞ ነፃ እንቅስቃሴንና ነፃ የምርጫ ውድድርን በመሰነግ፡፡ ከዚህ ቡድን ጋር በቅርቡ ተጀመረ የተባለውም ድርድር ዘላቂ የሰላም ውጤት የሚያስገኘው ስነጋው ከቀረ ብቻ ነው፡፡ ለቁርሾና ለጠብ አራጋቢዎችም የተመቹ ታሪክ መሳይ አስተሳሰቦችም የበኩላቸውን ሥራ ኅሊና ላይ ይሠራሉ፡፡
‹‹የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የጭቆናና የትግል ታሪክ›› (ከ615-1700) የተባለውን መጽሐፍ የጻፈው አህመዲን ጀበል፣ በመረጣ በመዝለልና በማጠልሸት ስልት ከዚህ ቀደም እየተዛባ ይጻፍ ስለነበረው ታሪክ የተቸ ቢሆንም፣ ከክርስትና አኳያ የተጻፉ ታሪኮችን ሚዛናዊ አይደሉም እንዳለ ሁሉ፣ ከእስልምና አኳያ የተጻፉትንም በዚያ ውሱንነት ውስጥ ሰፍሮ ከሁለቱም እውነትን ለመፈልፈል አልሞከረም፡፡ በእስላማዊ ወገናዊነት ጎን ቆሞና እዚያው ‹‹መረጣ››፣ ‹‹ዘለላ›› እና ‹‹ማጠልሸት›› የተባለው ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ የእነ አፄ ልብነ ድንግልን ግፍ ሲያወራ የኢማም አህመድ ኢብራሂምን ግን የሕዝብ አመፅና የነፃነት መሪነት አድርጎ ስሏል፡፡ በክርስቲያናዊውም በእስላማዊም ገዢዎች የመሸናነፍ ትግሎች ውስጥ ሃይማኖት ሕዝብን ለማትመም የዋለበትን ፖለቲካዊ ዘይቤ የሃይማኖት እንቅስቃሴ አድርጎ በልሙጡ ከመውሰድ ዘልቆ አልተረዳውም፡፡ ሃይማኖታዊ ወገናዊነትና ገለልተኛ ሆኖ ታሪክ የመጻፍ ተግባር የተምታታበት በመሆኑ ምክንያት ‹‹ሱኒ›› እና ‹‹ሺአ››ን በቃላት መፍቻው ውስጥ ሲተረጉም እንኳ የራሱን ደጋፊነትና ተቃዋሚነት ከማሳረፍ አላመለጠም፡፡ በአጭሩ አንዱ ወይ ሌላው ሃይማኖት መንግሥታዊ ርዕዮተ ዓለም በነበረበት በዚያ አሮጌ የአገዛዝ ዘመን ገዢ ሃይማኖትን በውድም በግድም የማስፋፋትን አስገራሚ አልባነትንና የክርስትናም ሆነ የእስልምና መስፋፋት ከኃይልና ከዘመቻ ጋር የተቆላለፈበትን የታሪክ እውነት አጠቃላይ የዕይታ መነጽሩ ያደረገ ትንታኔ ማካሄድ አልቻለም፡፡
በዚህም ምክንያት ያለፈው ሃይማኖታዊ ጭቆና የዘመኑ ተፈጥሯዊ ባህርይ እንደነበር (ነብር ሳር ጋጠ እንደማለት ጉድ ያሰኝ የነበረው በጭቆና ፈንታ እኩልነት ተቋቁሞ ቢሆን እንደነበር) የተረዳ ግንዛቤን ለማስተላለፍ አስተዋጽኦ አላደረገም፡፡ በሌላ አባባል፣ መጽሐፉ የአተያይ መከላከያ ስለሌለው ተሳስቶ ለሚያሳስት ቅስቀሳ ከመመቸት ራሱን አላዳነም፡፡
የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ መሥራችና ሊቀመንበር የኦሮሞና የኩሽ ወገኖች አመለካከት እንዲሆን ያሳተመው ‹‹ገዳ ሥርዓትና የተደበቀው የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ›› የሚል መጽሐፍ ብሔረተኛ ፖለቲካ የወለደውን የ16ኛ ክፍለ ዘመንን ‹‹አገርን የማስመለስ›› እና የ19ኛ ክፍለ ዘመንን ‹‹ቅኝ የመግባት›› ታሪክ ከማንገብም የባሰበት ነው፡፡ ከገዳ ውጪ መኖርን ኦሮሞን እንደ መካድ አድርጎ የሚቆጥር፣ የኦሮሞን ሽንፈት ሁሉ ከገዳ በመውጣት የሚተረጉም፣ የዮሐንስን፣ የምኒሊክንና የኃይለ ሥላሴን አሟሟት በዋቃ (በኦሮሞ አምላክ) ቅጣት የመጣ፣ የኮለኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በሕይወት መኖር ግን (የኦሮሞን መሬት ስለመለሰ) በመለኮታዊ ምሕረት የተገኘ አድርጎ የሚተረጉም ነው፡፡ ይህ ቀላሉ ነው፡፡ ‹‹ሴም›› እና ‹‹ኩሽ›› የሚባሉት ስያሜዎች ሁለት የቋንቋ ወገኖችን ከማሳየት ባሻገር ዝርያን የማይገልጹ መሆናቸውን፣ በኢትዮጵያ ያሉት ‹‹ኩሽ›› እና ‹‹ሴም›› የሚባሉት ሁለቱም ወገኖች የአፍሮ እስያ ጥቁር ሕዝቦች መሆናቸውን አያውቅም ወይም ማወቅ አልፈለገም፡፡ በኢትዮጵያ የብሔረሰቦች ዕድገት ታሪክ ውስጥ ኩሽ ቋንቋ ተናጋሪዎችና ሴም ቋንቋ ተናጋሪዎች መዛነቃቸውንና ዛሬ ከምናየው ኩሽ ቋንቋ ተናጋሪነት ጀርባ ሴም ተናጋሪዎች፣ ከሴም ተናጋሪዎች ጀርባም ኩሾች የመኖራቸው ሀቅ እሱ ጋር አልደረሰም፡፡ ሴምን የኩሽ ሥልጣኔን ያጠፋ ‹‹መጤ ዓረብ››፣ ኩሽን ግን አገር በቀል አድርጎ የሚያይ፣ የ‹‹ኩሽ›› ተናጋሪና የኦሮሞ ግፈኛ ገዢና አገዛዝ በታሪክ ያልተከሰተ ይመስል፣ ‹‹ሴሞች››ም በግፍ ያልተገዙ ይመስል፣ የግፍ አገዛዝንና ክፉ ልቦናን ከ‹‹ሴም›› ጋር አዛምዶ በዲሞክራሲ አብሮ ለመኖር የማይመቹ ዓይነት አድርጎ ሴሞችን ያጥፋፋል፡፡ እስከ ሶማሌ ድረስ ኩሻዊ ትስስርን በማቀንቀንም ሴሞችን ለመበቀል የሚሻ የሚመስልና ከአማርና ከትግራዊ ቡድኖች ጋር የተጣመሩ የኦሮሞ ቡድኖችን ‹‹የሴም ካምፕ›› እንደገቡ አድርጎ የሚፀየፍና ‹‹የኩሽ ካምፕ›› እንዲጠናከር በሚያደርገው ትግል የሚኮራ ነው፡፡
እነዚህን መሰል አስተሳሰቦች ኅብረተሰቡ ውስጥ መርዝ የማበጀት አቅም ላይኖራቸው የሚችለው ዲሞክራሲያዊና ፍትሐዊ አስተዳደር እየተሟላ መምጣት ከቻለና አብሮም የሚያጋልጣቸው የታሪክ ማረሚያ ከኖረ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ደምግባት ለመስጠትም ሆነ የነገሥታትን ዝና ለመካብ ሲባል ቆርጦ ቅጠላ የተደረገበት የታሪክ ጽሑፍ ችግር የለብንም፡፡ ዘመናዊ በመሰለ ግን ከፖለቲካ ፍላጎት ተመዞ በተጻፈ ድርሰታዊ ታሪክም እስከዛሬ የተወላገደው ትግላችን አያንሰንም፡፡ በይለይት ዕይታና በጮርቃ ጀብደኛነት በደሎችን ከዘመናቸው አውጥተው ስለመዘዛቸው ሳይጨነቁ በዛሬ ዓይን እየፈረዱና እያግለበለቡ ደም ያንተከተኩና ግጭት የጠሩ ትንታኔዎችም ይበቁናል፡፡ ዛሬ የሚያስፈልጉን የታሪክ ትንታኔዎች የታሪክ ክንዋኔዎችን በዘመናቸው ባህርይና ውሱንነት ውስጥ የሚረዱና ዛሬ ያሉንን አገራዊና አካባቢያዊ የህልውና ጉዳዮችን ላለማድማት የሚጠነቀቅ አስተዋይነትን ከሀቀኝነት ጋር ያዘመዱ ናቸው፡፡ በዚህ በኩል ክፍተት የዘጋ የታሪክ ሙያተኞች እንቅስቃሴ አለ ከማለት ይልቅ ሙያተኞቹ ለጠበኛ የፖለቲካ ፍጥጫ አንገት ደፍተዋል ቢባል እውነት ይሆናል፡፡
ፍጥጫው ቢፈርስና ዘራፍ ባይ ሳይኖር በሰከነ ስሜት ታሪካችንን ለመመርመርና ለማደራጀት ምን ያህል እንደሚቀልና መነቃቃት እንደሚኖር ማሰብ ነው፡፡ በአጠቃላይ እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮችን ከአፈናና ከፕሮፓጋንዳ ምንጣፍ ሥር አስተጃጅሎ ማኖር አንድ ቀን ጦሽ ለሚል ውስብስብ ችግር አገሪቱንና ሕዝቦቿን ማጋለጥ ነው፡፡ አቶ መለስ በነበረበት ወቅትም ሆነ አሁን ከእሱ ወዲህ የሚያስተማምን የፖለቲካ ሰላም በአገሪቱ ውስጥ እንልተፈጠረ መካድ ጥቅም የለውም፡፡ ሕዝብን በጥቅሉ የረታ ፓርቲ በሌለበት፣ የጥላቻ ፖለቲካ ከሁለት በኩል የትኛውንም ድንጋይ አንስቶ የሚወረውር በሆነበት እውነታ ላይ የድንገቴ ነውጥ አይጓጓለትም፡፡ የድንገቴው የውጤት ዕድል እንደምንም ወደ ዲሞክራሲያዊ ሁኔታ ከመዞር አንስቶ የታጠቀውን መንግሥታዊ ኃይል በገዢና በአማፂ ወገን/ወገኖች እየተቋረሱ፣ ጦሱ ለብሔር የሚተርፍና መድረሻው የማይታወቅ አውዳሚ ውጊያ ውስጥ እስከመግባት የሰፋ ነው፡፡
የታጠቀ መንግሥታዊ ኃይል ፓርቲያዊ ወገንተኝነትና የዲሞክራሲ ግንባታ አይግባቡም
ሌላው የድንገቴ ትርምስ ቀዳዳ በገዢው ክፍል ውስጥ የሚከሰት ቀውስ ነው፡፡ የ‹‹ዘመናዊቷ›› ኢትዮጵያ ታሪክ ከኃይለ ሥላሴ አንስቶ እስከዛሬ ድረስ በገዢው ክፍልና በሥልጣን ማስከበሪያው የታጠቀ ኃይል ትስስር ላይ የቆመ ነው፡፡ የመንግሥትም የደፋ ቀና ጉዞ ከታጠቀ ኃይልና ከተመላኪነት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ የአፄው መንግሥት የታጠቀውን ኃይል መቆጣጠር ሲሳነውና የንጉሡ ተመላኪነት ሲቦተረፍ በወታደራዊ ግልበጣ ተወገደ፡፡ ወታደሩንና ሕዝቡን በዚያም በዚህ አፍዝዞ ያንድ ሰው ተመላኪነትና አምባገነንነት ሆኖ ያደገውም ደርግ፣ ብሎ ብሎ የወደቀው በአመለካከቱ የቀረፀውን የወታደርና የደኅንነት ኃይል ታማኙ አድርጎ ማንቀሳቀስ ሲሳነው ነው፡፡ የተካው ሕወሓት/ኢሕአዴግም የሥልጣኑን መሠረት የጣለው የደርግን ሠራዊትና የደኅንነት መረብ አፍርሶ በራሱ ሠራዊት ላይ የተማከለ የሥልጣን ማስከበሪያ አውታር በማቋቋም ነው፡፡ ገዢው ክፍልና የታጠቀው መንግሥታዊ ኃይል እስከተጣበቁ ድረስ በታጠቀው ኃይል ቁጥጥር ውስጥ የሚደርስ ለውጥ ገዢዎቹን ያምሳል፡፡ ገዢዎቹም ውስጥ የሚደርስ መታመስ የታጠቀውን ኃይል መንካቱ አይቀሬ ነው፡፡ ሕወሓት በ1993 ዓ.ም. በተሰነጠቀ ጊዜ ወታደሩ እንዳይከፋፈልና እንዳይዋጋ ተሰግቶ የነበረው የወታደሩ ዋና ተቆጣጣሪ ቡድን ሕወሓት ስለነበረ ነው፡፡ መለስ ክፍፍሉን አሸንፎ የሁሉም ጠቅላይ መሆን የቻለው በሠራዊቱና በደኅንነቱ ውስጥ የተቀናቃኞቹን ተፅዕኖ በውስወሳ፣ በማግለልና በሹም ሽር በማምከን ነው፡፡ የመለስ ኢሕአዴግ የ1997ን የምርጫ ውጤት መቀየርና ቅዋሜን መሰባበር የቻለውም የታጠቀውን ኃይል ወገንተኝነት ተጠቅሞ ነው፡፡ ከዚያ በኋላም የአጠቃላይ ሠራዊቱን ወገንተኝነት በዘመቻዊ አጠባና ምንጣሮ ለማደስና ለማጥበቅ አልዘገየም፡፡
ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ከባልደረቦቹ አነጋገር የተገኙ ፍንጮች እንደሚጠቁሙት ሕመሙ ቶሎ ያቀላጥፈዋል ተብሎ ባይጠበቅም ብዙም ዕድሜ የማይሰጠው እንደነበር ሳይታወቅ አልቀረም፡፡ በ2002 ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ይቅርብኝ እኔ እያለሁ ሥራውን ሌላ ሰው ይልምድ ስለማለቱም በእንጥብጣቢ ተነግሮናል፡፡ የመተካካትን ነገርና የውዳሴ መለስ ግንባታንም ምን እንዳመጠው ይኸው በስተኋላ ተከስቶልናል፡፡ በሕይወት እያለም የተኪዎች ዝግጅት ሳይታሰብበት እንዳልቀረ መገመት አያዳግትም፡፡ እንደዚያም ሆኖ ሁሉን ነገር ራሱ ነበር የሚቀይሰውና የሚመራው ሲባል ተኪዎቹ የቱ ጋር ራሳቸውን ችለው መወሰንና ሐሳብ ማፍለቅ እንደተለማመዱ ማየት ያስቸግራል፡፡ ቢያንስ ከተቃዋሚዎች ጋር ያለውን ፍጥጫና ንቁሪያ ያቃለለ የፖለቲካ ሁኔታ ለተተኪዎቹ ለማመቻቸት ለምን እንዳልተሞከረም ያስገርማል፡፡ ያም ሆነ ይህ፣ ሁሉንም (ጦሩን፣ ፓርቲውንና ምክር ቤት የሚባለውን ሁሉ) ተቀጢላው ያደረገው መሪ ሞት ድንገተኛ መሆኑ አልቀረም፡፡ በድንገቱም እውነተኛው የማዘዝ ኃይል ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ወጥቶ የጦርና የደኅንነት አውታሩን ወደሚቆጣጠሩት ሰዎች አካባቢ መንሸራተቱ ኦቶማቲክ ነው፡፡
ከ97 ልምድ በኋላ የታጠቀውን ኃይል የታማኝነት ጥራት የመጠበቁ ሥራ ተከታታይነት የነበረው እንደመሆኑም የሥልጣን ማስከበሪያው ኃይል በመለስ ታማኞች /አምላኪዎች እጅ ውስጥ መሆኑ የሚገመት ነው፡፡ እንደዚያም ቢሆን ግን የአውራው መሄድ ለታናናሾች መተያየትና እህስ እህስ መባባል በር መክፈቱ የማይቀር ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉት የፍትጊያ ዝንባሌዎች ምናልባቶች ከነመልካቸው አስቀድመው ሊታወቁ አይችሉም፡፡ በታማኞች መሀል የሚነሳ ልሙጥ የሥልጣን ፍላጎት፣ በአዲሶቹና በነባሮች መካከል ያለ ክፍተት፣ በመሪነት በተቀመጠው/በተቀመጡት ሰዎችና ከጀርባ ባሉት ባለኃይሎች መካከል የሚፈጠር የመተማመን ክፍት ሁሉ የፍትጊያ መገለጫ ሊሆን ይችላል፡፡ በመለስ ታማኝነት ውስጥ አድፍጦ የኖረ ከተቃዋሚዎች ጋርም ሆነ በቅርብ ከተገለሉ ሰዎች ጋር የተያያዘ የፍትጊያ ዝንባሌም ሊያደባ ይችላል፡፡ ሬሳ ተቀምጦ አለልክ የጦዘው የመለስ ውዳሴና ራዕዩን የማሳካት ፉከራና ቃልኪዳን የሕዝብን ወኔ ከማነሳሳት ባሻገር የአንጃ ሽኩቻን የማዳፈን ወይም መለስን ተገን አድርጎ ወደ ላይ የመውጣትም ጥበብ ሊሆን ይችላል፡፡ በቀብር ስንብቱ ላይ አዜብ መስፍን ‹‹የመለስ ዓላማና ፖሊሲ ካልተበረዘና ካልተነካካ በምችለው ሁሉ አገለግላለሁ›› ማለቷም የሚፈለፈል መልዕክት ያለው ነው፡፡ እንደ ዝንባሌዎቹ ግፊትና አቀማመጥ የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሥልጣን ዕድልም በፍትጊያ ዝንባሌዎች አመጣጥ፣ ብርታትና አዘማመድ የሚወሰን መሆኑ አይቀርም፡፡ የጀርባ ትዕዛዝ የሚቀበል፣ ምሪት ሲስት ‹‹ዋ!›› የሚባል፣ አልረባ ካለም ታምሜያለሁ አስብሎ ዘወር እስከ ማድረግ አሻንጉሊት መሆን አንዱ የምናልባት ጫፍ ነው፡፡ በአመራር ብልኃት፣ በምክር ቤትና በሕዝብ ዘንድ ተሰሚነት በማትረፍ፣ ያንጃ ዝንባሌዎችንም ወደራስ እየመነዘሩና አንገት እያስደፉ ሥልጣን ያለው መሪ መሆን ሌላው የምናልባት ጫፍ ነው፡፡ በሁለቱ ጫፎች መሀል ደርሞ ረገብ ያሉ አማራጮች ይኖራሉ፡፡
የመንግሥት አውታሩ ከነወታደራዊ አካሉ የፓርቲ ታማኝ እንዲሆን መደረጉ እስከቀጠለ ድረስ ግን የሥልጣን ሽኩቻ እያደባ በተለያየ አጋጣሚ ብቅ ማለቱ፣ እንዳልዘረጠጥ እያሉ የመግዣ ኃይልን የማፅዳቱ ታሪክ ይቀጥላል፡፡ የተወጠኑት የልማት ተግባራት ቢሳኩና እንደሚባለው ድህነቱ ቢቀረፍ ፍትሐዊ አስተዳደር እስከሌለ ድረስ ያለ ጭንቅ የመግዛት ማዕረግም አይገኝም፡፡ ባህሬንን የሚያምሰው የኢኮኖሚ ችግር እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡ በድምፅ ካርድ የተመረጠ መሪ ወታደሩንና ደኅንነቱን ለመያዝ ሳይጨነቅ ቢሮ ሲገባ ሥልጣኑንም መቀዳጀት የሚችልበት፣ የሥልጣኑም ቀጣይነት በሕገ መንግሥትና በተግባሩ ብቻ የሚወሰንበት ሥርዓት ሀ ብሎ የሚጀምረው ወታደሩ፣ ፖሊሲና ደኅንነቱ፣ የምርጫ አስፈጻሚና ሌሎች ተያያዥ አካላት ከግለሰብና ከፓርቲ ታማኝነት ጋር ሳይጣበቁ፣ በሕጋዊው ጎዳና በኩል ማንም መጣ ማን እንደ ተቋም በገለልተኛነት የሚቀበሉና አገራዊና ሙያዊ ተልዕኳቸው ላይ የሚያተኩሩ አድርጎ በማደራጀት ነው፡፡ የፖለቲካ ትርምስ ሳይፈጠር፣ የመፈናቀልና የሙያ ብክነት እገጭ እገው ሳይኖር ከሕዝብ ጋር በእርጋታ እዚህ ሒደት ውስጥ ለመግባት አሁን ያለንበት ምዕራፍ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡
የ37 ዓመታት ሸለቆን እንድፈን
ችግሮች መዘዝ ሳያመጡ እንዲመክኑ፣ አንድ ‹‹የፖለቲካ መሐንዲስ›› ላይ ብቻ ላለመጠምጠም፣ እሱ አንድ ነገር ቢደርስበትና የሚገዛው ፓርቲ ቢዝረከረክ መሄጃ እንዳይጠፋን፣ ብሶቶች እየከረሙ የማይንጡበት፣ የአክራሪነትና የአሸባሪነት መለምለሚያ አፈርና ውኃ የማያገኝበት ምዕራፍ ውስጥ ለመግባት፣ ከአሮጌ የአገዛዝና የፖለቲካ ባህል ለመላቀቅ፣ የመጀመሪያው ጥርጊያ መንገድ ከየፖለቲካ ጎራዎች አጥር ወጥቶ ጠበኛነትን ማፍረስ ነው፡፡ ከጠብ ፖለቲካ በመውጣት ከተቃዋሚ በላይ ተጠቃሚው ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ነው፡፡ በመዘርጠጥ ጭንቅ ተጠምዶ ሁሉን ነገር ሚስጥራዊ ከማድረግና የተቃውሞ ንፋስ ከማሳደድ አዙሪት የመላቀቅ ዕድል ይከፈትለታል፡፡
እንደ ዳንኪራ እየተደረሰ የሚከናወን ክስና ፍርድ ማካሄድንና የአፈና እውነታን ለመደበቅ የፕሮፓጋንዳ ስጋጃ እየሸመኑ ሲያነጥፉ የመዋል ባህልን ሙጥኝ የሚያሲዝ ምክንያት ይቋረጥለታል፡፡ ሁሉን ነገር (ሐዘንን ጨምሮ) በድርጅታዊ መንገድ ለማቀናበር ካልሞከረ ከሕዝብ ነፃ እንቅስቃሴ ጋርም ከልብ የመገናኘት በር ይከፈትለታል፡፡ እንዳይፈነዳ የሚያስፈራራ እምቅ ብሶት አይኖርምና ከማድባትና ከመንጫጫት ይልቅ ይህን እንሥራው እያሉ በሐሳብና በተግባር መተጋገዙ ያይላል፡፡ የዚህ ዓይነት የእርቅ ፖለቲካኛነትና የእርቅ መንግሥትነት ሁኔታ ውስጥ መግባት ለአገሪቱ የዲሞክራሲና የልማት እመርታ ዓብይ ትርጉም ያለው ነው፡፡
የእርቅን ጥያቄ ሥልጣን በአቋራጭ የማግኛ ዘዴ ወይም የሥልጣን ተራ እኛም ደርሶን እንቅመስ ማለት አድርጎ ገዢው ፓርቲ ሲወስደው ቆይቷል፡፡ በተቃዋሚዎችም በኩል የሽግግር መንግሥት ወይም የተውጣጣ መንግሥት ካልተመሠረተ በቀር የተሻለ ለውጥ እንደማይመጣ አድርገው የሚያስቡ፣ ከዚያም አልፎ የሽግግር መንግሥትን ለሥልጣን ማቋረጫነት ለመጠቀም የሚፈልጉ እንዳሉ እውቅ ነው፡፡ በቅርቡም ለማንኛውም ተዘጋጅተን እንጠብቅ በሚል ዓላማ ተብሎ የሽግግር ምክር ቤት እንደተቋቋመ ሰምተናል፡፡ የዚሁ ምክር ቤት የአመራር አባላት የሆኑ ሰዎችም ምንድነው ጀርባችሁ? ምን ገድል አላችሁ? ይህን ማቋቋም ዳያስፖራውን መናቅ አይሆንባችሁም እየተባሉ በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮም ሲፋጠጡ አዳምጠናል፡፡ ምክር ቤቱን ያቋቋሙት ሰዎች ለምን ተጠረጠሩ? ለምን አብሮ ለመሥራት ያናገሯቸው ሰዎች/ቡድኖች ለምን ሐሳባቸውን አልተቀበሏቸውም? ይህ ሁሉ የዚህ ጽሑፍ ጉዳይ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ አንገብጋቢ ጉዳይ ክፍተት ወይም ትርምስ ከተፈጠረ ሥልጣን ለመያዝ ተዘጋጅቶ መጠበቅ ሳይሆን፣ ትርምስ መንገድ እንዳያገኝ ያሉትና መጪዎቹም ፓርቲዎች የተቻቻለ ዲሞክራሲያዊ ሕይወት ውስጥ እንዲገቡ የመወነጃጀልና የጠላትነት ፖለቲካዊ ግንቡ ይናድ ነው፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በአመፅ በማፍረስ››፣ በ‹‹ሽብርተኛነት›› ወይም ‹‹ሽብርተኛ በመርዳት›› ስም የተካሄዱ ውንጀላዎች፣ ፍርዶችና እስራቶች ሁሉ ተነስተው በኢትዮጵያ ልማትና ዲሞክራሲ ግንባታ ውስጥ የተሻለ ሕይወትን የሚያስቡ ሁሉ መቀራረብ፣ መነጋገርና ድርሻ ማዋጣት የሚችሉበት በር ይከፈት፡፡ ወደ ውይይት ከመምጣትም በላይ ላሉት ሕጋዊ ፓርቲዎችም ሆነ ተንጠባጥበው ወደፊት ለሚመጡ ሰላም ፈላጊዎች ሁሉ ያለማሳበቢያ ክፍት የሆነና ሕይወት ያለው የምክክር ሸንጎ ይደራጅ ነው፡፡ ‹‹የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ወይም ሥልጣን አጋሩን›› የሚል ጥያቄ (አሁን ባለው የገዢና የተቃዋሚ የፖለቲካ ሚዛን ሁኔታ) የማይጨበጥና ያንኑ የኢሕአዴግን አሰልቺ ማሳበቢያ የሚጠቅም፣ እንዲያውም ዛሬ ዓለም ትኩረት ከሰጠው ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ቅብብል ጎን ሆኖ ለማምታታት የተመቸ ነው፡፡ ይህንን ያስተዋለና በቋፍ ያለውን የአገሪቱን ብሶተኛነት የጠየቅነው ካልተሟላ የራሱ ጉዳይ ከሚል ድርቅና መውጣትን የሚፈልግ መሆኑን የተገነዘበና እርቃዊ ሁኔታው እየሰመረ ከሄደ፣ ሥልጣን መቋደስም ቢሆን የፖለቲካው ደመና ለውጥ ከሚያመጣቸው መልካም ነገሮች ውስጥ በጣም ትንሹ ነገር እንደሆነ የገባው የፖለቲካ ሰውም የሚያነጣጥረው ከሁሉ በፊት ጠብ ይፍረስ በሚል ዒላማ ላይ ነው፡፡ ‹‹ወያኔ የሽግግርን መፍትሔ ካልተቀበለ ጉድ ይፈላበታል›› የሚል ዓይነት ዛቻ የሚያሰሙም ዛቻና ጥያቄያቸውን እርባናውን ቢመዝኑት ይመከራል፡፡
በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ለራሱና ለአገሪቱ ብሎ ጠብን ለማፍረስ፣ ሲሆን በራሱ ተነሳሽነት ካልሆነም ልመና ቀረሽ ሲጠየቅ ያደርገው እንደነበረ በትዕቢት መሳለቁንና እንዳይታማ ያህል የይስሙላ ፈቃደኝነት አሳይቶ የመግፋት ዘዴውን ትቶ የምር ተግባር ውስጥ መግባት ይጠበቅበታል፡፡ ‹‹ዛሬ 80 ሚሊዮን ሕዝብ መለስን እንደተካው አይተናል›› ያለና በኢትዮጵያ ሕዝብ የተገረመ መንግሥት የተናገረውን የሚያምንበት ከሆነ፣ (በእርግጥም ተቃዋሚዎች ተዳክመው ባሉበት በአሁኑ ሁኔታ የተስፋፋውና በተቀባይነት የተሻለው ገዢው ፓርቲ ነውና) ወደኋላ ለማለት ሰበብ አይኖረውም፡፡ በተቃዋሚዎችም በኩል ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እርቅ ሲጠየቅ ብናይም (በተለይ መድረክ በተደጋጋሚ ለመነጋገር ጠይቆ ሰሚ እንዳጣ ይታወቃል)፣ ብዬ ነበር ለማለት የሚሆን መግለጫ ከመወርወር ያለፈ ነገር አልታየም፡፡ ዛሬም ከመግለጫ ባለፈ፣ እርቅ ፈላጊ ተቃዋሚዎች እርቅና መቀራረብን፣ አመለካከታቸውና እንቅስቃሴያቸው እስካላደረጉትና እንቅስቃሴያቸው የመበራከት ክብደት ካልፈጠረ ዋጋ የለውም፡፡ ስለሰላም መጨነቅ ተንበርካኪነት የሚመስላቸውና ከአቋሜ ወይ ፍንክች የሚሉም ወገኖች ‹‹ከፀረ ሰላም ጋር ድርድር የለም›› የሚል ሰበብን በመጠቀም ረገድ ጠላቴ ለሚሉት መንግሥት የምርጥ ወዳጅ አገልግሎት እየሰጠሁ ይሆን ብለው ራሳቸውን ቢጠይቁ መልካም ነው፡፡ የዲሞክራሲ ትግሉ ኃጢያት ከመከመርና ማንም የሚያውቀውን (መለስ ራሰ በራ ነበር ከማለት የማይሻል) ነገር ከመደጋገም የዘለለ የአስተሳሰብ ፍሬያማነት (ሴንስቢሊቲ) ይፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ የወቅቱ ፖለቲካ ላይ አንዳችም አሻራ ማሳረፍ የማይችሉትን የደርግ ባለሥለጣናትን ለማስፈታት የባከነው የሃይማኖት መሪዎች እርቅና ምሕረት ጠያቂነትም አገራዊ ፋይዳ ያለው ሚና መጫወት የሚችለው አሁን ነው፡፡
ገዢው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች ሊያጤኑት የሚገባ አንድ ሀቅ አለ፡፡ ዛሬ የምንገኝበት ወቅት ከ1997 ዓ.ም. በጣም የተለየ ወቅት ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም. በተቃዋሚው በኩል የነበረው የቆሙበትን መሬት በውል ያላስተዋለ በአንድ የምርጫ ጀምበር ሥልጣን የመላፍ ችኩልነትና የገዢውን ክፍል ጥምብ እርኩስ የማውጣት አባዜ ከነንቀቱና ስላቁ፣ ገዢው ክፍል ከሥልጣን ወርዶ በመፈጥፈጥ ፍርኃት ደንብሮ፣ ለአጭር ጊዜ ያየናትን የዲሞክራሲ ሁኔታ ሥር ሳትይዝ እንዲያጠፋት ማመካኛ እንደሆነ የሚታወስ ነው፡፡ ዛሬ ከአንድ ፓርቲ ገዢነት መዳፍ የምትገኝ ዲሞክራሲያዊ ሁኔታ ምን ያህል ተሰባሪ ሸክላ እንደሆነችና ምን ያህል እንክብካቤ እንደምትሻ ትምህርት ተገኝቷል፡፡ የዲሞክራሲ መብትን መጠቀምና ሳያስመነትፉ የማቆየት ነገርም መንገድ እየወጡ ከመንጫጫት በላይ አስተዋይነትንና ዘዴኛነትን የሚጠይቅ እንደሆነ፣ ተቀራርቦ ለመነጋገር ይልፈቀደ ግትር አቋም የቱን ያህል መቀመቅ እንደሚከት፣ የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ ትኩስ ልምድ ትምህርት ይሰጣል፡፡ በአካባቢያቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበሩት ሊቢያና ሶሪያ በይፋና በስውር ጣልቃ ገብነት እገዛ በተካሄደ/እየተካሄደ ባለ የሞት ሽረት ጦርነት እንዳይሆኑ ሆነዋል፡፡ ሊቢያ ከጋዳፊ ጋር የነበረባትን ጦርነት ብትጨርስም ፍርስራሽ እንደታቀፈች ልዩ ልዩ የታጠቁ ቡድኖችና ንዑስ ፍላጎቶች ገና ይፍተለተሉባታል፡፡ ጦርነት ያላበቃባት ሶሪያ ጣጣዋ ከሊቢያም እንዳይብስ ያሰጋል፡፡ የበርማ ገዢዎችና ተቃዋሚዎች እየሸሹት ያሉት ይህንን የመንኮታኮት መንገድ ነው፡፡ የመንኮታኮቱ አዙሪት ብሎ ብሎ በኢትዮጵያ እንዳይነሳም መፍትሔው ገዢም ሆነ ተቃዋሚዎች በጊዜ ከግትርነት ወጥተው መደራደር መቻላቸው ነው፡፡ ኪሳራው ከበዛ ትርምሳም የመንግሥት ለውጥ ይልቅ በእጅ ባለ ልማት ላይ ፖለቲካዊ እርቅ የሚያመጣቸውን በጎ ነገሮች መጨመር የብዙዎች ኢትዮጵያውያን የዛሬ ፍላጎት መሆኑን ሁሉም ወገን ያጢነው፡፡ ከዚህ አኳያ የአቶ መለስ ሞት ሲነገረው ገዢውንም ተቃዋሚውንም ያስገረመው የኢትዮጵያ ሕዝብ በእርቅ ሁኔታ ውስጥ የነፃ እንቅስቃሴ ዕድል ቢያገኝ ደግሞ ከግርምትም ግርምት እንደሚፈጥር አያጠራጥርም፡፡
ቅኝ ተገዢነትን እምቢ ያለና ያሳፈረ ታሪክ ያለው ሕዝብ፣ ከፋሽስት ጣሊያን ጋር ባካሄደው የአርበኝነት ትግል ጊዜ እንኳ ግፍ ያዘንብበት ለነበረው የፋሽስት ምርኮኛ ፍርድ ያለመንፈግ የትግል ቅርስ ለነበረው ሕዝብ፣ ዛሬም የአቶ መለስ ዜናዊን መልካም ጎን አይቶ በደግ የመሸኘት ጨዋነትን ላስተማረ ሕዝብ፣ የጠብ ሸለቆን ተሻግሮ ይችን ታህል የፖለቲካ ሰላም እንዲጎናፀፍ ዕድል መስጠት እጅግ ቢያንሰው እንጂ አይበዛበትም፡፡
No comments:
Post a Comment