Thursday, December 13, 2012

ቃለ መጠይቅ ከኘሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም

ይህ ቃለ መጠይቅ ሰኞ በ21/1/2ዐዐ5 ዓ.ም. በኘሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም መኖሪያ አፓርትመንት ውስጥ በሚገኘው
የግል–ቢሮአቸው የተካሄደ ሲሆን በአቶ መለስ ሞት ዙሪያ፣ ትተዋቸው ባለፏቸው – መታሰቢያዎች(legacy)፣ እንዲሁም 
በመፃዒ የኢህአዴግ እና የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታዎች ላይ ያነጋገራቸው የሰማያዊ ፓርቲ ልሳን የሆነው የ“ሰማያዊ” ሚድያ ዋና 
አዘጋጅ ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ ነው፡፡ መልካም ንባብ! መልካም ንባብ! 

ሰማያዊ፡- በቅድሚያ ለቃለ-መጠይቁ ስለተባበሩን በጣም ነው የምናመሰግነው፡፡ በቀጥታ ወደ ጥያቄው ስገባ፡- በጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ሞት ምን እንደተሰማዎ ቢገልፁልንና ከዚያ ብንጀምር….. 

ኘሮፌሰር መስፍን፡- የአቶ መለስ ሞት ድንገተኛ ነው፤ ድንገተኛ በመሆኑም ያስደነግጣል፡፡ ለማናችንም ቢሆን ሞት የማይቀር መሆኑንም ብናውቅ፤ እንኳን እንደዚህ በድንገት ሲሆንና ታመውም ቆይተው በሚሞቱበት ጊዜ ማዘን አይቀርም፡፡ ምንም አይነት ሰው ይሁን! እኔ በመለስ ሞት ያደረብኝ ስሜት፤ ከዚህ በፊት በጠ/ሚኒስትርነቱ ወይም በኘሬዚዳንትነቱ አሊያም በፈላጭ ቆራጭነቱ ያደረገው ነገር አይደለም፡፡ ድንገት በመሆኑ፣ ዕድሜ ለንስሃ ሳያገኝ መቅረቱ ያሳዝናል፡፡ …እና …መቼም…እእእ…የሱ ሞት ለብዙዎቻችን እንደዚሁ እንደማንም እንደሰው የሰው ባህርይ ሆኖ የመጣ መሆኑን ብንገነዘበውም፤ ለጓደኞቹ ደግሞ እንደዚህ አልነበረም ይመስለኛል፡፡ እነሱ ይበልጥ የደነገጡ፣ የተደናበሩ፣ ሞትን ለመደበቅ የሞከሩ፣ የማይደበቀውን ለመደበቅ የሞከሩ በመሆናቸው ትንሽ የመለስን ሞት እእ….. አንድ ያጠላበት አጉል ነገር ነበረና እሱ ያሳዝናል፡፡ እሱም በራሱ በኩል ሆነ፤ ለርሱም የሚቆም ሰው የሚመለከተው፣ ለቤተሰቡ ያ ሁኔታ እና ለመደበቅ የተደረገው ሽር-ጉድ (እስካሁንም ድረስ ብዙ ነገር ተደብቋል) ያ ደግሞ ይበልጥ ያሳዝናል- ከሞቱም ይበልጥ ያሳዝናል-አሟሟቱ! ይኸው ነው፡፡ 

ሰማያዊ፡- በዚህ ዙሪያ ግን በዚያን ሰሞን በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አቶ በረከት ሰምኦን ተጠይቀው፡- “ይሄ በፓርቲያችን የተለመደ ባህል ነው፤አዲስ አይደለም፡ ፡ የአንድ ሰው መታመም ወይም መሞት ብዙ ስለማያስደንቀን በአደባባይ መግለፁንም ያን ያክል አሳሳቢ አድርገን አናየውም” ብለው ነበረ፡፡ በዚህ ረገድ ሌሎች ደግሞ፡- “የኢትዮጵያ ህዝብ የማወቅ መብት ነበረው፤ ሊደበቁ የሚገቡ ነገሮች
ብሔራዊ የደህንነት ምስጢሮች ወይም የመከላከያ ምስጢሮች ተብለው ሊያዙ የሚችሉ የመኖራቸውን ያህል ስለአንድ የአገሩ ጠቅላይ-ሚኒስትር ግን ለዚያውም የህዝብ ኃላፊነት ቦታ እና ስልጣን እንደመያዛቸው፤ህዝቡ በይፋ ማወቅ ይገባው ነበረ” ብለው የሚከራከሩም አሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የጋናውን ኘሬዚዳንት ሞትና ወዲያው ለህዝቡ በይፋ መገለፁን ብሎም በተገቢው ወቅት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር መካሄዱን እንደአብነት ጠቅሰው ያስረዳሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?
ኘሮፌሰር መስፍን፡- እንግዲህ በረከት እኛ ሲል እነማን ናቸው እነሱ? እኛ የሚለው! እንደዚህ ልዩ ባህል ያለው!
የተለየ የሆነው! ከኢትዮጵያ ህዝብ ባህል፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ ልማድ ውጭ የቆመ ማን ነው እሱ? ማነው በረከትና
ቡድኑ? ኢህአዴግን እንደሆነ ኢህአዴግ አንድ የፖለቲካ ቡድን ነው፤ግንባር ነው፤ ብዙዎች አሉበት ውስጡ-ሰዎች!
አሁን እንደዚህ ‘መርዶ ባህላችን አይደለም’ ሲሉ ከዚህ በፊትም ሰምቻለሁ በሌላ አጋጣሚ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ
ውስጥ ነው ያሉት እኮ! የኢትዮጵያን ህዝብ ነው የሚያስተዳድሩት፤ ለኢትዮጵያ ህዝብም ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ካልሆነ ይሄ የተለመደው የነሱ ግዴታቸውን ቸል የማለት እና ‘እኛ ነን ሁሉንም ነገር የምንወስነው- ልማድንም
ባህልንም የምንወስነው እኛ ነን፤ ከእኛ በላይ ማንም የለም! ህዝቡም ቢሆን የራሱ ባህል የለውም! የማወቅም
መብት የለውም፤ ማለት ይችላል በረከት ከዚህ በፊት በሌላም ነገር እንዳለው፡፡ ነገር ግን ይሄ ቅድም እንዳልኩት፡-
በመለስ ሞት ምክንያት ተደናብረው እንጂ በረከት ስቶት አይደለም፡፡ በመሆኑም፡- በድንብርብር ውስጥ ሆነው
አንዴ ‘ታሟል!፣ አንዴ ‘ደህና ነው!፣ አንዴ አሁን ነው!፣ “እንዲህ ነው…. እንዲህ ነው….” እያሉ ቆይተው ስለነበረ፤
በእውነቱ የነሱን መደናበር እና በትክክለኛው አእምሮ ውስጥ እንዳልነበሩ የሚያሳይ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment