Sunday, December 9, 2012

የዕርቀ ሰላም ውይይቱ ተጠናቋል – ዛሬ መግለጫ ይሰጣል፤ በአቡነ መርቆርዮስ ጉዳይ ተጨባጭ ስምምነት ላይ የተደረሰ አይመስልም


በአሜሪካዋ የቴክሳስ ግዛት ዳላስ ከተማ ከኅዳር 26/2005 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የሰነበተው የአባቶች ዕርቀ ሰላም ውይይት በመልካም ሁናቴ በመካሔድ ላይ ቆይቶ ቅዳሜ የተጠናቀቀ ሲሆን ዛሬ እሑድ መግለጫ በመስጠት ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቃል።
በአጀንዳዎቹ ላይ በመግባባትና በመከባበር ውይይቱን ያደረገው ጉባኤው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ከሥልጣናቸው እንዴት ሊወርዱ እንደቻሉ በአገር ውስጥም በውጪው የሚገኙት አበው ልዑካን የታሪክ ምስክርነታቸውን ከሰጡ በኋላ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ኢትዮጵያ  መመለስ አስመልክቶ ረቡዕ ዕለት ሰፊ ውይይት መደረጉንና ሳይጠቃለል በይደር መገታቱን መዘገባችን ይታወሳል።
በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ባሉ አባቶች እና ምእመናን ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው የአራተኛው ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ጉዳይ ዋነኛው የመነጋገሪያ አጀንዳ በሆነበት በዚህ ጉባዔ ከሁለቱም ወገን የተለያየ ሐሳብ ከመቅረቡ አንጻር ለጊዜው ከስምምነት ላይ የተደረሰበት አይመስልም።
ከአገር ቤት የመጣው ልዑክ “ቅዱስነታቸው በመረጡት ቦታ በጸሎት ተወስነው ይቀመጡ” ሲሉ በውጪ የሚገኙት አበው ደግሞ “ከነሙሉ ማዕረጋቸው ወደ መንበራቸው ይመለሱ” የሚለውን ሐሳብ አቅርበዋል። በሁለቱም በኩል ሐሳቡ ዕልባት ሳይሰጠው ቀርቷል። ጉባዔው ዛሬ መግለጫውን ሲሰጥ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ በሌላ ጊዜ ድጋሚ ተገናኝቶ ይወያይ እንደሆነ የደረሰበትን የውሳኔ ሐሳብ ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ስለ አቡነ መርቆርዮስ መመለስ ግልጽ ደብዳቤ የጻፉትን የፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስን ሐሳብ አስመልክተው ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ጣቢያ ቃለ ምልልስ የሰጡት ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ አቡነ ናትናኤል ከትናንት በስቲያ አርብ “ፓትርያርኩ በተወሰነላቸው ቦታ እንዲቀመጡና ለአገራቸው አፈር እንዲበቁ” እንጂ ሌላ ነገር እንደማይጠበቅና እንደማይወሰን መናገራቸው የዕርቅና የሰላም ውይይቱ ሳይጀመር የተፈጸመ አስመስሎት ሰንብቷል። ለሰላም ውይይት ምንም ዓይነት በር መዘጋት እንደሌለበት ከማመን አንጻር አሁንም ውይይቱ እንዲቀጥል የሁሉም ተስፋ ነው። የመግለጫውን ሙሉ ሐሳብና ዝርዝር ጉዳዩን እንደደረሰልን እናቀርባለን።

No comments:

Post a Comment