Wednesday, December 5, 2012

መንግስት የህዝብን ብሶት አልሰማ ብሎአል ሲሉ ፕሮፌሰር በፈቃዱ ደግፌ ተናገሩ


ህዳር ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ታዋቂው የኢኮኖሚክ ባለሙያ የሆኑት ፕ/ር በፈቃዱ ደግፌ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ መንግስት የህዝብን ብሶት አልሰማ በማለቱ አንድ ቀን ያልጠበቀው አደገኛ ሁኔታ ሊፈጠርበት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ” ህዝቡ የሚሄድበት ቦታ አጥቷል፣ ብሶታል” ያሉት ፕ/ር በፈቃዱ ከአረብ አብዮት የምንማረው ህዝብ መሪ ሳያስፈልገው በብሶቱ ብቻ ሆ ብሎ ሊነሳ የሚችል መሆኑን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ቃለ ምልልስ የሰጡት ፕ/ር በፈቃዱ ደግፌ የኢትዮጵያ ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን ኢህአዴግ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለሙስና ስራ መስራት እንደማይቻል የገለጹት ፕሮፌሰሩ፣ ጉቦ ባይኖር ኖሮ ይህ አገር አይኖርንም ነበር ሲሉ በአገሪቱ የተስፋፋው ሙስና የደረሰበትን ደረጃ አመላክተዋል።
ሙስናን ለማጥፋት በህግ የሚተዳዳር፣ በህግ የሚገዛ መንግስት መኖር እንዳለበትም ፕ/ር በፈቃዱ መክረዋል።
ምንም እንኳ ለእድገት የሚያስፈልጉ መሰረተ-ልማቶች ቢሰሩም፣ የህዝቡ ኑሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መሄዱን ፕሮፌሰሩ  ተናግረዋል። “ህዝቡ ቀጭጯል፣ የሚበላው   የለውም ” ያሉት ፕ/ር በፈቃዱ፣  መንግስት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት በመስጠት የህዝቡን የምግብ ፍላጎት ማርካት እንዳለበትም መክረዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የዋጋ ግሽበት በዋናነት ከገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተያያዘ ነው የሚለውን ለመቀበል እንደሚቸግራቸው የገለጹት ፕ/ር በፈቃዱ፣ በእርሳቸው እምነት የዋጋ ግሽበቱ ዋነኛው መንስኤ በአገሪቱ ውስጥ በቂ ምርት አለመመረቱ ነው ።

No comments:

Post a Comment