Saturday, December 1, 2012

የእስራኤል ኩባንያ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን ማኔጅመንት ሊረከብ ነው



-    ሌሎች 50 ኩባንያዎች በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት ለማድረግ ጠይቀዋል
-    እስራኤል በአፍሪካ ኅብረት መድረክ አለማግኘቷ ቅሬታ ፈጥሮባታል

በታደሰ ገብረማርያም
የእስራኤል ኤሌክትሪክ ኩባንያ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን ማኔጅመንት ተረክቦ ለሦስት ዓመታት ያህል ለመምራት የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቅቋል፡፡ ሌሎች ወደ 50 የሚጠጉ የእስራኤል ልዩ ልዩ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ወይም ኢንቨስት ለማድረግ መጠየቃቸውን በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር በላይነሽ ዘቫዲያ ገለጹ፡፡

የእስራኤል ኤሌክትሪክ ኩባንያ 20 መሐንዲሶች በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ሥራውን ይጀምራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አምባሳደሯ አስረድተዋል፡፡ የእስራኤል የኤሌክትሪክ ኩባንያ የኮርፖሬሽኑን ማኔጅመንት ለሦስት ዓመታት ለመምራት የሚያስችለውን ሥራ ያገኘው ለዚህ ተብሎ የወጣውን ዓለም አቀፍ ጨረታ በማሸነፉ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በሁለት እንዲከፈል የተወሰነ ሲሆን፣ የኃይል ሽያጭ፣ የደንበኞች አገልግሎትና አስትዳደራዊ ጉዳዮች ለእስራኤሉ ኩባንያ ይሰጣሉ፡፡ ሁለተኛው ኃይል የማመንጨትና የማስፋፋት ሥራዎች በኮርፖሬሽኑ አማካይነት ይከናወናል፡፡ ከዚህ ቀደም መንግሥት የቀድሞውን ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ማኔጅመንት ለፈረንሳዩ ፍራንስ ቴሌኮም መስጠቱ ይታወሳል፡፡

ሌሎቹ 50 ኩባንያዎች ለመሰማራት የሚፈልጉት በሶላር ኢነርጂ፣ በውኃ ቴክኖሎጂ፣ በመስኖ ልማት፣ በጤናና በሌሎችም በርካታ የልማት ዘርፎች መሆኑን አምባሳደሯ አስረድተው ከኩባንያዎቹ መካከል የተሟላ አቅም፣ ብቃትና የአሠራር ጥራት ያላቸውን ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል የማጣራት ሥራ ኤምባሲው በማከናወን ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫ፣ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት፣ ለማንኛውም ዓይነት እርሻ ተስማሚ የሆነ ለምና ድንግል መሬትና በርካታ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት መሆኗ፣ የውጭ ባለሀብቶችን ወይም ኩባንያዎችን ቀልብ ለመሳብ መቻሉን አምባሳደር በላይነሽ አስረድተዋል፡፡

“ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ እያደገች፣ የቀድሞ አስከፊ ገጽታዋን እየለወጠችና ተስፋ ሰጪ የሆነ የዕድገት አቅጣጫን ይዛ ትታያለች፡፡ አሁን የተያያዘችውን የዕድገት ጎዳና አጠናክራ ከቀጠለች በቅርብ ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ትሰለፋለች፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድም ታላቅ አገር ያደርጋታል፤” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እስራኤል ከባዶ ተነስታ ያንን ደረቅና በረሃማ መሬት አልምታ፣ የተማሩ ሰዎችንና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን አፍርታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ካደጉ አገሮች ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች ብለው፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የትም የማይገኝ ሰፊና በርካታ የተፈጥሮ ሀብት እያላት በድህነት አረንቋ ውስጥ መዘፈቅ የለባትም የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያና የእስራኤል ግንኙነት ከንግሥተ ሳባ ወይም ከሦስት ሺሕ ዘመን በፊት ጀምሮ ተያይዞ የመጣ መሆኑን ለማንም የተሰወረ አይደለም፤›› ያሉት አምባሳደር በላይነሽ፣ በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑንና ይህ ዓይነቱም ግንኙነት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉን አቀፍ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ለዚህም እውን መሆን በቴክኖሎጂ ዕውቀት ሽግግርና በባህል ልውውጥ ዙሪያ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አምባሳደር በላይነሽ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጎንደር፣ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ኮከብ ፅባህ ትምህርት ቤት አጠናቅቀዋል፡፡ ከዚያም ኑሮአቸውን እስራኤል በማድረግ በመጀመሪያ የእብራይስጥ ቋንቋ መማራቸውንና ከዚያም በሒብሩ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዎችን ካገኙ በኋላ፣ በ1985 ዓ.ም. የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባ ሆነዋል፡፡ ባለትዳርና የሦስት ልጆች እናት ሲሆኑ ባለቤታቸው ጎንደር ተወልደው የተማሩት ደግሞ አዲስ አበባ ነው፡፡

‹‹ወደ እስራኤል የሄድኩት በ17 ዓመቴ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ከወጣሁም 28 ዓመት ሆኖኛል፡፡ በሌላ አገር ከሚኖሩት ትውልደ ኢትየጵያውያን መካከል እኔ አምባሳደር ሆኜ መመለሴ የመጀመሪያው ያደርገኛል፡፡ ሌሎችም ዳያስፖራዎች ይህ ዓይነቱ ዕድል እንዲገጥማቸው ምኞቴ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አምባሳደር በላይነሽ ዘቫዲያ በአሁኑ ጊዜ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የብሩንዲና የሩዋንዳ የእስራኤል አምባሳደር ናቸው፡፡ ሹመታቸውን አግኝተው ኢትዮጵያ ከመጡም ጥቂት ወራት ተቆጥረዋል፡፡

በሌላ በኩል እስራኤል ከ42 የአፍሪካ አገሮች ጋር የዲፕሎማቲክ ግንኙነት እያላትና በአኅጉሩ ውስጥ በበርካታ የልማትና የዕድገት ሥራ ላይ ተሰማርታ አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ላይ መሆኗ እየታወቀ፣ በአፍሪካ ኅብረት የታዛቢነት መድረክ አለማግኘቷ በእጅጉ እንዳሳዘናቸው አምባሳደሯ ተናግረዋል፡፡

አምባሳደር በላይነሽ እንደገለጹት፣ ኅብረቱ እስራኤልን በሚመለከት ወይም በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ባሉት ጉዳዮች ላይ ውይይት በሚያደርግበት ወቅት የፍልስጤም ተወካይ ሲገኝ፣ ለእስራኤል ግን ይህ ዓይነቱ ዕድል መነፈጉ አግባብ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹እኛ በሌለንበት ወይም እንድንሳተፍ ባልተጋበዝንበት ጉባዔ ላይ ስለእኛ ተነጋግሮ ውሳኔ ማሳለፍ ትክክለኛ አካሄድ አይደለም፤›› ያሉት አምባሳደር በላይነሽ፣ እስራኤል በአውሮፓ ኅብረትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ ድምጿን ከፍ አድርጋ የምታሰማበት መድረክ እንዳላት ሊታወቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ላይ ግን የፍልስጤሙ ተወካይ ሲገኝ እስራኤል መነፈጓ ኅብረቱ ለአንድ ወገን ያደላ አስመስሎታል ብለዋል፡፡

የእስራኤል መገኘት አስፈላጊ በሆነበት በኅብረቱ ጉባዔ ላይ እንዳትሳተፍ ሊያደርጋችሁ የቻለበት ምክንያት ምን ይመስልዎታል? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ “ምክንያቱን ባውቀው በጣም ደስ ይለኛል፤ እኔ እንደሚመስለኝ ከሆነ ግን ከእኛ ጋር ግንኙነት የሌላቸው የኅብረቱ አባል አገሮች የፈጠሩት ጫና ሳይሆን አይቀርም፤” ሲሉ አምባሳደር በላይነሽ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  

No comments:

Post a Comment