Monday, December 10, 2012

ፕሬዚዳንት ሞርሲ መከላከያ ሰራዊቱ ህግ እንዲያስከብር ጠየቁ


ታህሳስ ፩(አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በግብጽ የተጀመረው ተቃውሞ የፕሬዚዳንቱን ስልጣን አደጋ ውስጥ እየከተተው መምጣቱን ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ የጤር ሀይሉ ህግ እንዲያስከብር፣ የመንግስት ተቋማትን እንዲጠብቅና አጥፊዎችን እንዲያስር ስልጣን ሰጥተዋል።
ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ሞርሲ በቅርቡ ከፍተኛ ስልጣን የሚሰጣቸውን ህግ በመሰረዝ የህዝቡን ቁጣ ለማብረድ የሞከሩ ቢሆንም ፣ የህዝቡ ቁጣ ግን አሁንም ሊበርድ አልቻለም።  ተቃዋሚዎች ለአዲሱ ህገመንግስት ድምጽ ለመስጠት የፊታችን ቅዳሜ የተያዘውን ቀጠሮ እንዲሰረዝ ቢጠይቁም፣ ፕሬዚዳንቱ ግን ፈቃደኛ አልሆኑም።
ተቃዋሚዎች ማክሰኞ የተቃውሞ ሰልፎች እንደሚደረጉ አሳውቀዋል። የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎችም መሪያቸው ለወሰዱት እርምጃ ድጋፋቸውን ለማሳየት በተመሳሳይ ቀን ሰልፍ ጠርተዋል። በተቃዋሚዎች እና በደጋፊዎች መካከል ግጭት ይፈጠራል ተብሎ የተፈራ ሲሆን፣ መከላከያ ሰራዊቱም ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል አየተነገረ ነው።
ፕሬዚዳንቱ ለመከላከያ ሰራዊቱ የሰጡት ትእዛዝ ግብጽ ወደ ወታደራዊ አገዛዝ ተመልሳ እንዳትገባ ስጋት ፈጥሯል።
ቃዋሚዎች የተቃውሞ ማእከላቸውን በፕሬዚዳንቱ ቤተመንግስት አቅራቢያ በማድረጋቸው መከላከያ ሰራዊቱ ሀይሉን ወደ ስፋረው እያንቀሳቀሰ መሆኑን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
ፕሬዚዳንት ሞርሲ አብዮቱን ከሙባራክ ዘመን ፖለቲከኞች ለመታደግ የወሰዱት እርምጃ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢናገሩም ተቃዋሚዎች ግን የሚቀበሉት አልሆነም። ተቃዋሚዎች የፕሬዘዳንቱ እርምጃ አዲስ አምባገነን መንግስት እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው በማለት ይቃዋማሉ።

No comments:

Post a Comment