ህዳር ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከቀድሞው መንግስት ጋር በተደረገው ጦርነት የወዳደቁ የታንክና ሌሎች ተሽከርካሪ ብረቶችን በማጓጓዝ ላይ የነበረ ተሽከርካሪ ያልፍበት የነበረው ድልድይ በመሰበሩ አንድ አርሶ አደር ሲሞት ሾፌሩና ረዳቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በሰዎች ለሰዎች በተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በብዙ ሚሊየን ብር ተገንብቶ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ዘመናዊ ባለብረት ድልድይ፣ ከሚዳ ወረሞ ወረዳ መራኛ ከተማ ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ ከፍተኛ ክብደት ያለውን ብረት ጭኖ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ የነበረው ባለተሳቢ ከባድ መኪና ወንጪት የተባለ ድልድይ አቋርጦ ሲጓዝ ከጭነቱ ክብደት የተነሳ ነው ድልድዩ ሊሰበር የቻለው፡፡
ድልድዩ ከአዲስ አበባ፣ ሙከ ጡሪ ፣ እንሳሮ ዋዩ ፣ መርሃ ቤቴ ፣ ሚዳ ፣ ጃማ እና ወረኢሉ ወረዳዎች እንዲሁም ወደ ደሴ ከተማ የሚጓጓዙ ብዙ ተሸከርካሪዎችን በቀን ያስተናግድ ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ “የህዳሴው ኮንስትራክሽን እቃዎች አቅርቦት ኃ/የተ/የግል ማህበር” የተባለ ድርጅት ኢህአዴግ ከቀድሞው መንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ በነበረበት ጊዜ ተመትተው ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ታንኮችን፣ ኦራል መኪኖችንና የተለያዩ ብረታብረቶችን ከወረዳው በማሰባሰብና በመጫን ወደ አዲስ አበባ መውሰዱን ነዋሪዎች ተቃውመዋል።
የማህበሩ አባላት ከህዳር 15 እስከ ህዳር 22/2005 ዓ.ም የተለያዮ አቅም ያላቸውና ብዛት ያላቸው ብረት መቁረጫ ኦክስጅን በመጠቀም ብረት የመቆራረጥ ስራ ሲሰሩ ከቆዩ በሁዋላ ፣ ከ10 በላይ በሚሆኑ ባለ ተሳቢ ከባድ መኪኖች ጭነው ወስደዋል።
“ለህዳሴው ኮንስትራክሽን እቃዎች አቅርቦት ኃ/የተ/የግል ማህበር” ብረታብረቶችን በሚያነሳበት ጊዜ የአካባቢው ነዋሪዎች ማህበሩ ህገወጥ ነው፣ ህጋዊ የሆነ ደብዳቤም አልያዘም በማለት ተቃውሞ አንስተዋል። ይሁን እንጅ ማህበሩ የወዳደቁ ብረቶችን እንዲያሰባስብ ከመከላከያ ኢንጂነሪንግ ፈቃድ እንደተሰጠው በመግለጽ እቃዎችን አንስቷል።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ዘይኑ አሊ ማህበሩ ከመከላከያ ኢንጂነሪንግ የተላከ መሆኑን እንደገለጸላቸው ለኢሳት ተናግረዋል። የአካባቢውን ሰዎች ለማረጋጋትም 5 ፖሊሶችን ወደ አዲስ አበባ ከተጓዙት መኪኖች ጋር አብረው መላካቸውንና እቃዎች የሚራገፉበትን ትክክለኛ ቦታ አጥንተው እንደሚመጡ ማዘዛቸውን ተናግረዋል። የወረዳው የፖሊስ አዛዠ ኢንስፔክተር አንዳርጌ ዛሬ እንደገለጹት ደግሞ የተላኩት ፖሊሶች አዲስ አበባ ደርሰው እቃዎችን ለማራገፍ ወደ ሞጆ እንደሚጓዙ ገልጸዋል።
ከመኪኖቹ ጋር ከተጓዙት መካከል መቶ አለቃ ሰለሞን ድረስ ለኢሳት እንደገለጸው አንድ መኪና ወደ ሞጆ ሲሄድ ሌሎች መኪኖች በክፍያ ውዝግብ ምክንያት አዲስ አበባ መከላከያ መሀንዲስ ፊት ለፊት ቆመዋል።
“ለህዳሴው ኮንስትራክሽን እቃዎች አቅርቦት ኃ/የተ/የግል ማህበር” ከመከላከያ ሰራዊት በተቀነሱ አብዛኞቹ የህወሀት አባላት በሆኑ ወታደሮች የተመሰረተ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ በመላ አገሪቱ የወዳደቁ ታንኮችን፣ ተሽከርካሪዎችንና ብረታብረቶችን በማሰባሰብ አዲስ ለተቋቋመው መከላከያ ኢጂነሪንግ ያቀርባል።
No comments:
Post a Comment