ወታደር ይነግዳል እንዴ ወገን? ኢይይይይ የኔ ነገር እረሳሁት ማለት ነው አሳምሮ ይነግድ። እንዴ ስንቶቹ ናቸው ከተቀደደ የሗላ ኪስ ባንድ ጊዜ ባለ 5 እና 6 ወለል ፎቅ ባለቤት ሆነው የኪራይ ንግድ እያጧጧፉ የሚገኙት። ስንቶቹ ናቸው በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ከተሞች ብዛት ያለው የቦታ ካርታ እየወሰዱ እሱን በመቸብቸብ ባለ ሚሊዮን ጄኔራሎች የሆኑት። የሙገር ሲምንቶን አይር ባየር በማሻሻጥ ስንቶቹ ወታደሮች ባንዲት ጀምበር ባለሚሊዮን እንደሆኑና ሙገር ሲምኒቶ ፋብሪካን ድራሹን እንዳጠፉት ከእኛ ወዲያ ማን ምስክር አለ። ስኳር ፋብሪካዎቻችንም ቢሆኑ እንዲህ አይነቱን የወታደሮች አላግባብ ሃብት ማካበት ከማገዝ የጸዱ አይደሉም። እርግጥ ነው ወታደሮቻችንማ አሳምረው ይነግዳሉ፣ ታክስ የማይከፍሉ
ከመሆናቸውና በሕዝብ ሃብት በነጻ ከመጠቀማቸው አንጻር ሰታዩ ደግሞ ይዘርፋሉሉሉሉ ቢባል ይቀላል። ከዚህ ይልቅ እኔን በጣም የደነቀኝ ወታደሮች ከመዋዕለ ንዋይ ፍሰት (ኢንቨስትመንት) ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ስራ ሊሰሩ ነው ዋሽንግተን የገቡት መባሉ ነው።
እንዴ ጎበዝ ወታደርነት እኮ ሳይንስ ነው። ውጤታማ የሚያደርግ የራሱ የሆነ የተቀላጠፈና ቀላል ወጭ ወይም መስዋትነት የሚጠይቅ መንገድ ያለው ኩነት። እና ከእንዲህ ያለው ሳይንስ አውጥቶ ወታደሮችን ወደ ኢንቨስትመንት ምን ዶላቸው? እንዴው ነገርን ነገር ያነሳዋል ነውና ከዚህ በፊት የተዘገበ አንድ ዜና ትዝ አለኝ። ወታደራዊ ሳይንስንና የወያኔን ወታደር ግንኙነት የሚቃኝ ነው ነገርየው። ጉዳዩ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የተፈጸመ ነው። በጊዜው የነበረውንና ፍጹም ወታደራዊ ሳይንስ ያልነካካውን የኢትዮጵያና የኤርትራ እልህ የተሞላበት ጦርነት አንድ የውጭ ጋዜጠኛ የታዘበውና የዘገበው ባ16ኛው ክፍለ ዘመን ከተደረጉት ጦርነቶች እንዳንዱ አድርጎ ነበር። ልክ በቡድን እንደሚፋጁት የዱር እንሰሳት። ከዚህ አንጻር ሲመዘኑ ደግሞ የወያኔ ወታደሮች በማያውቁት የኢንቨስትመንት መስክ ይቅርና አለንበት በሚሉት ወታደራዊ ክፍልም ቢሆን በስም እንጅ በተግባር እንደጫካዎቹ አውሬዎች መሆናቸው ማየሉ ነው ክፋቱ።
የሆነስ ሆነና ማን ወይስ እነማን ናቸው ጉዳዩን የፈጸሙት አትሉም? ነገሩ ወዲህ ነው፤ የመከላከያ ሚንስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳ እና ጄኔራል ሳሞራ የኑስ፤ ውይይይ ይህ ጄኔራል ምነው ስሙ በያቅጣጫው በረከተሳ አባዝተው በተኑት እንዴ? ወታደራዊ ክህሎት እንዳላቸው አይታወቅም እንጅ ቢኖራቸው እንኳ ያ ክህሎት ለወታደራዊ ሳይንስ ብቻ ነው። በማህበራዊ ሳይንስ፣ ባስተዳደርና ፋይናንስ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ወይም በሌላ መስክ ክህሎት ሊሆን አይችልም።
በእርግጥ በወያኔ አሰራር ሁሉም ቀመር የለውም ምክንያቱም ወያኔዎች ሁሉንም መሆን ይችላሉና። ጄኔራሉ ጄኔራልነቱን ጥሎ የሕዝብ አስተዳደር ላይ ሊመደብ ይችላል ወይም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሃላፊ ሊሆን ይችላል ካልሆነም የቴሌኮሚኒኬሽን፣ የውሃና ፍሳሽ አልያም እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለውን አትራፊ ድርጅት ሊገድል ይችላል። እጅግ ሲከፋ ደግሞ እንደ ዓይነ ስውር መሪ ከሗላ ሆኖ ዩኒቨርሲቲዎችን ሊያስተዳድር ይችላል። የሰሞኑ የጄኔራሎች የአሜሪካ ጉብኝትም እንግዲህ ወታደሩ ሁሉን ማድረግ እንደማይሳነውና እያደረገም እንደሆነ ለማሳየት የተደረገ
አይመስላችሁም?
ከዚህ በመነሳት፤ ያየነውና የሰማነው እንዲህ አይነት ጉዳይ የሚያስጨንቀንና ጥያቄ የሚሆንብን፤ ከእንዲህ አይነት ስርአትና አሰራር ሊገኝ የሚችለው ትርፍ ምን ሊሆን እንደሚችል ስናስብ ነው። ላለፉት 21 ዓመታት ከሀገራችን ዓመታዊ ገቢ በተጨማሪ ወያኔ በቢሊዮን የሚቆጠር እርዳታ ዶላር ቢያገኝም የሚበዛው ከጥቂቶች መጠቀሚያነት አላለፈም። ሕዝባችን ግን ዛሬም ድረስ የርሃብ ምሳሌ እንደሆነ አለ። ከርሃብና ስደት ከድህነትና ጉስቁልና በቀር ባለፉት የወያኔ አገዛዝ ዘመኖች ሌላ እድገት አልታየም። ድሮስ ወታደር በሚያስተዳድርበት ሀገር ከዚህ ሌላ ምን ሊጠበቅ ይችላል። ሀገራችንንም ሆነ ሕዝባችንን ከእንዲህ ያለው ውርደት ለመታደግ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሕዝባዊ አስተዳደር ለመተካት የሁላችንም ትብብር ወሳኝ ነው። ለዚህ ደግሞ ቀጠሮ አያስፈልገውም። አበቃሁ።
No comments:
Post a Comment