Monday, December 3, 2012

በጥንቁር አንበሳ የካንሰር ተጠቂው ቁጥር ከሆስፒታሉ አቅም በላይ ሆኗል ተባለ


ኢሳት ዜና:-በካንሰር በሽታ ተጠቅተው ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሄዱ ህሙማን ለኢሳት እንደገለጹት ሆስፒታሉ ለካንሰር ህመምተኞች ያዘጋጀው አልጋ እና ህክምና የሚሰጡት ባለሙያዎች ቁጥር ከበሽተኛው ቁጥር ጋር ሊጣጣም ባለማቻሉ በሽተኞች ተገቢውን ህክምና ለማግኘት አልቻሉም። በጥቁር አንበሳ ለካንሰር በሽተኞች ተብሎ የተዘጋጀው አልጋ ቁጥር አነስተኛ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ በየአመቱ ከ200 ሺ በላይ አዳዲስ የካንሰር ተጠቂዎች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። የጥቁር አንበሳ የመረጃ ድረገጽ  እንደሚናገረው ሆስፒታሉ በአመት ከ1 ሺ 500 ያልበለጡ ሰዎችን ብቻ ያስተናግዳል። አብዛኛቹ በሽተኞች በአልጋ እጦት ውጭ ላይ ሳይቀር እንደሚተኙ በሽተኞች ገልጸዋል። ህክምናውን የሚሰጡት ስፔሻሊስቶች ቁጥራቸው ከ6 ያልበለጠ መሆኑም የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች በጊዜው ህክምና ማግኘት ባለመቻላቸው በሽታው ጸንቶባቸው ለሞት ይዳረጋሉ።
ብቸኛ የካንሰር ህክምና መስጫ ጣቢያ የሆነው ጥንቁር አንበሳ ሆስፒታል ካሉት 600 አልጋዎች ውስጥ ለካንሰር በሽተኞች የመደበው 18 ብቻ ነው።  አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በካንሰር ቢጠቃም ወደ ህክምና ጣቢያ በመሄድ ሪፖርት የሚያደርገው ሰው ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነው። በዚህም የተነሳ የካንሰር ተጠቂው ቁጥር ከተጠቀሰው አሀዝም ሊበልጥ እንደሚችል የሆስፒታሉ የመረጃ ድረገጽ ያሳያል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታዩት የካንሰር በሽታ አይነቶች መካከል የማህጸን፣ የጡት፣ የራስና የአንገት፣ ዋናዎቹ ናቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው የካንሰር በሽተኞች ቁጥር መጨመር ትክክለኛ ምክንያቱ እስካሁን አልታወቀም። አንዳንድ ወገኖች በዘመናዊ መንገድ ከሚመረተው ምግብ ጋር የተያያዘ ነው ቢሉም ፣ ትክክለኛ ምክንያቱ ግን እስካሁን በጥናት አልተረጋገጠም።

No comments:

Post a Comment