Monday, December 3, 2012

በኬኒያ የስደት “ኬዝ” ጋገራ


በኬኒያ የስደት “ኬዝ” ጋገራ

ሰላም ወዳጄ እንዴት ሰነባበቱልኝ…!?
ይቺ ጨወታ ለአዲሳባዋ ፍትህ (አዲስ ታይምስ) ተልካ ነበር። ታድያ እርስዎስ ለምን ታመልጥዎታለች!?
ዛሬም ወደ ኬኒያ ይዤዎት ልሄድ ነው። “አረ አንከራተትከን!” ብለው ቅር እንዳይሰኙብኝ ጥሩ ጥሩ ጨዋታዎች ስላሉ እንዳያመልጥዎ ብዬ ነው።
ኬኒያ ዘልቀን ከመግባታችን በፊት ስለ ሀገራችን ጉዳይ አንድ አስተያየት ለመስጠት ተነሳሽነቱ አለኝ። እኔ የምለው የአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ሊፈርስ ነው የሚለው ነገር የምር ነው ማለት ነው። መንግስታችን መቼም ማፍረስ ብርቁ አይደለም። እውነቴን ነው የምለው ላለፉት ከሃያ የሚበልጡ አመታት በሳቅ ሲያፈርሰን አይደል እንዴ የከረመው…!? አሁን ደግሞ ሀውልታችንን ሊያፈርስው መሆኑን ስንሰማ ባለፈው ጊዜ ልምዱ ነው ወይስ አዲስ ስልጠና ወስዶ ነው ብዬ ጠይቄያለሁ!
ሎሬት “ኦቦ” ፀጋዬ ገብረ መድን ጉዱን አላየ ያኔ በርሱ ጉርምስና ዘመን አንድ ጀብራሬ ሀውልቱ ጥግ ሽንቱን እየሸና “አንተ ድንጋይ እሸናብሃልሁ… ጓደኞችህ የተባሉትን እሺ ብለው በማርቸዲስ ሲንፈላሰሱ አንተ ይኸው እምቢ ብለህ ድንጋይ ሆነህ ቀረህ! እሸናብሃለሁ” ሲለው ከጀብራሬው ጋር “ድንጋይ አይደለም አትሸናበትም” እያለ እንዳልተፋለመ፤ አሁን የባሰባቸው ጀብራሬዎች ሀውልቱን ሊያፈርሱት መሆኑን ቢሰማ ቢኖርም በብስጭት መሞቱ አይቀርም ነበር። አንድ የፌስ ቡክ ወዳጃችን “ፀጋዬ ይቺን ሰዓት” ስትል ሸጋ ግጥም ገጥማ ተመልግቻለሁ… እኔም አቅም አጥቼ እንጂ ይሄንን ሳይ ግጥም ብቻ ሳይሆን ቡጢም ብጋጠም ደስታዬ ነበር… ግን ፈራሁ…! እሸሸግበት ጥግ አጣሁ! እፀናበት ልብ አጣሁ… “ባከሽ እመብርሃን ይብቃሽ፣ ባክሽ ምስለ ፍቁር ወልዳ… ፅናት ስጪኝ እንድካፈል የእናቴን የኢትዮጵያን ፍዳ፣ ከነከሳት መርዝ እንድቀምስ ከነደደችበት እቶን የእርሷን ሞት እኔ እንድሞታት፣ ገላዋ ገላዬ እንዲሆን።… አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ እፀናበት ልብ አጣሁ።…” ብለው ለሀገራቸው የተሰዉ አባት ሀውልት ሲፈርስ ማየት እውነትም ግጥም ብቻ ሳይሆን ቡጢም ያጋጥማል….!
ኢህአዴግ ግን የሚገርመኝ መመስገን ለምን እንደማይፈለግ “ጎሽ አበጃችሁ” መባልን ለምን እንደሚፀየፍ ነው። የባቡር ግንባታ ስራ መጀመር እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነገር ሆኖ ሳለ የማይነኩትን ከመንካት ትንሽ ዘወር አድርጎ ድምፁን ሳያሰማ መስራት ሲችል ግረግር መፍጠር በጣም ያስደስተዋል። ድሮስ በግርግር የገባ ምን መላ አለው እንዳይሉ… ካሉም ይበሉ።
የኔ ነገር ኬኒያን ደጅ አቁሜ የሀገር ወሬ ላይ ተጠመድኩኝ አይደል ይቅርታ ኬኒያዬ… በነገራችን ላይ ኬኒያ በከተማዋ ውስጥ ዘመናዊ ባቡር መጠቀም እንደጀመረች መቼለታ በኢቲቪ ሰምቻለሁ። እርስዎም ወይ ከእኔ ወይ ከኢቲቪ ሳይሰሙት አይቀሩም… ለባቡሩ ስትል ሀውልት ማፍረሷን ግን አልሰማሁም…
ሌላ በነገራችን ላይ ከአቡኑ ሀውልት ጋር የተያያዘ የዚሁ ቀጣይ የሚመስል ጨዋታ በኢሳት ድረ ገፅ ላይ ታገኙታላችሁ።
እንቀጥል… በኬኒያ የስደት “ኬዝ”…
“ኬዝ” ይህንን ቃል በዚህ መልኩ ለመጀመሪያ ግዜ  የተዋወቅበሁት “ምን አለኝ ሀገሬ” ብዬ ስደት ከወጣሁ በኋላ ነው። ቆይ ቆይ… እዚች ጋ አንዲት ጨዋታ መጣች… አንድ ወዳጃችን ነው። በሀገሩ ጉዳይ ምርር ብሎት መታወቂያው ላይ ዜግነት ኢትዮጵያዊ ተብሎ ተፅፎ ሳለ እንደ ሁለተኛ ዜጋ መታየቱን እያማረረ ወደ ቤቱ ገባ። ቤቱ ሲገባ የደላው ቴሌቪዥን የአንድ መምህርን ሙዚቃ ከጭፈራ ጋር አዋህዶ እያቀረበ ነው። ጌቴ አንለይ ይባላል ዘፋኙ። (በነገራችን ላይ ጌቴ ድሮ መምህር ነበር። ከዛ ዶክተር ፈቃደ አዘዘ አንድ ግጥም ፃፉ። ግጥሙ እንዲህ ይላል። “ሩጥልኝ ልጄ ዝፈንልኝ ልጄ መማር ለኔም አልበጄ!” አሉ። ይመስለኛል ይህንን ግጥም ጌቴ አነበበው እናም መምህርነቱን ትቶ ሙዚቀኛ ሆነ… “መሰለኝ” ካሉ የፈለጉትን ማውራት ይቻላል። መሰለኝ ነው ያልኩት!)
እናልዎ ይህ ወዳጃችን የጌቴ አንለይን “ምን አለኝ ሀገሬ!” ሙዚቃ ሲሰማ፤ ቀን በዋለበት የደረሰበት በደል፣ ሁሌም እንደ ሁለተኛ ዜጋ የመቆጠሩ ነገር ክንክን አድርጎት “ለ”ን አጥብቆ “ምን አለኝ ሀገሬ… ምን አለኝ ሀገሬ…?” እያለ መዝፈን ጀመረ። እንዳይፈርዱበት ወዳጄ ሰዎች በሀገራቸው ጉዳይ እጅግ ተስፋ ሲቆርጡ ብዙ ጥያቄ ይጠይቃሉና አይፍረዱ። በዛን ሰሞን ወዳጃችን ዳዊት ከበደ እና መስፍን ነጋሽ “እውነት ግን ይሄ ሀገር የማነው?” ብለው እንደጠየቁት ማለት ነው። እነ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ እነ ሚሚ ስብሐቱ፣ እነ ጋሽ በረከት ሰሞን ለሁሉም የምትበቃዋን ሀገር እንደ ገብጋባ ህፃን ምግብ በልቶም እንደማያውቅ፤ ሀገሪቷን በሙሉ ዝግን አድርገው ይዘው፤ ምን ዝግን አድርገው ብቻ… በሁለት ጉንጫቸው ጎስጉሰዋት (በርግጥ ይሄም ተጋኗል!) ብቻ ግን በጥቅሉ “ሀገሪቱ የኛ ብቻ ናት” ብለው ቢያስቸግሩ ግዜ ነው፤ መስፍኔ እና ዴቭ “እውነት ይቺ ሀገር የማናት?” ብለው መጠየቃቸው። በነገራችን ላይ መልሱ “ሀ” ነው። “ሀ” ምን መሰልዎ? “ሀገሩ የሁላችንም ነው። የእነሱም የእኛም!” ይህንን መለስ በተሰደድኩ በሳምንቱ ተመስገን ደሳለኝ ነግሮኝ ነበር። ያኔም በሆዴ “ቀድመህ አትናገርም ነበር” ስል አጉረምርሜያለሁ… እዚችግ ሳቅ ይግባልኝ…
ይቅርታ ወዳጄ ዋና ጨዋታዬን አልረሳሁትም። ድጋሚ አዲስ መስመር ላይ እንገናኝ። እና ኬኒያችን ሹልክ ብለን እንገባለን።
በኬኒያ “ኬዝ” እንጀራ ነው። በርካታ የሀገሬ ሰው “ምን አለኝ ሀገሬ? ምን ቀረኝ ሀገሬ?” ብሎ ይሰደዳል። በአስቸጋሪ በርሃ ውስጥ፣ ህይወቱን ለአደጋ አጋልጦ ይወጣል። አሁን ስለ ስቃዩ የምናወራበት ገፅ ላይ አይደለንም። እና ውጣ ውረዱን አልፎ እዚህ ደርሷል አሉ፤ “አንኳኩ ይከፈትላችኋል ስትገቡ ሌላ በር ይጠብቃችኋል!” እንዳለው በውቀቱ ስዩም፤ ያንን ሁሉ አልፎ እዚህ ደግሞ ሌላ ውጣ ውረድ ይጠብቀዋል። ወደ ሌላ ሀገር ለመዛወርም ሆነ በተሰደደበት ሀገር ላይ ተረጋግቶ ለመቀመጥ አንደ ወሳኝ ነገር አለ “ኬዝ” ይባላል። ጥገኝነት የመጠየቂያ አሳማኝ ምክንያት!
እንግዲህ አሁን የምናወራው “እዛ ቁጭ ብዬ ርሃብ ከምሞት ወጥቼ የመጣው ይምጣ!” ብሎ ስለተሰደደው “የኢኮኖሚ ስደተኛ” ነው ማለት ነው። ልብ አድርጉልኝ! ስደተኞችን ተቀብሎ የሚያስተናግደው ድርጅት ደግሞ “የኢኮኖሚ ስደተኛ” ከሆኑ ወደተሻለ ሀገር ለማዛወር ፈቃደኛ አይደለም። እንኳንስ ወደሌላ ሀገር ሊያሸጋግር ይቅርና በተሰደደበት ሀገርም ለመኖር የሚያስችል እውቅና አይሰጥም። እና ምን ይሻላል? የሚሻለውማ “ኬዝን” ማሳመር ነው። “ኬዝ” ከየት ይመጣል? ካሉኝ… አያስቡ… ቀልቦን አሰባስበው ይከተሉኝማ…
“ኬዝ” ልክ እንደማንኛውም ሸቀጥ ይገዛል፣ ተገዝቶም ይለቀማል፣ ተለቅሞም ይበጠራል፣ ተበጥሮም ይፈጫል፣ ተፈጭቶም ይቦካል፣ ተቦክቶም ይጋገራል! ይህንን የሚያከናውኑ ደግሞ ጥሩ ጥሩ “ኬዝ” ጋጋሪ ባለሞያዎች አሉ። ስለ ባለሞያዎቹ ሌላ ጊዜ በስፋት እናወራለን። ለአሁን ግን ከአንዳንድ ባለኬዞች ጋር የተጨዋወትኩትን እንካችሁ
አንድ
ማርዬ ትባላለች። የመጣችው ከጎንደር ነው።፡ቆንጆ ናት። ንግግሯ ላይ የዋህነቷ ተንኮል አለማወቋ፣ በጥቅሉ ጨዋነቷ ይነበባል። ዘመዶቿ ካናዳ ነዋሪ ናቸው። ታድያ እሷስ ለምን ይቅርባት? ልትሄድ ሻንጣዋን ሸክፋ መሸጋገሪያው ሀገር ላይ ደርሳለች። አገኘኋት… “ከሀገርሽ ለምን ወጣሽ?” አልኳት። “ዋ…የኬዜን ልንገርህ ወይስ የእውነቱን…?” ብላ ሳቀች። በነገራችን “ዋ!” የምትለውን የአግርሞት ቃል ትግሬዎች ይሏታል። ጎጃሜዎች ይሏታል። ጎንደሬዎችም አይምሯትም። ልብ ብለን ብንመረምር የተጣመርንበት ብዙ ነገር አለ። እስቲ… “ኬዝሽ” ምንድነው? አልኳት። “አረ ተወኝ! የኔስ ይቅር ይበለኝ…!” ብትለኝ ጭራሽ አጓጓችኝ። እስቲ ንገሪኝ… “ቄሱን አባቴን… አርበኛ ግንባር ተዋጊ ነው ብዬ…” እሺ…
በጎንደር አካባቢ በተለይም በታች አርማጭሆ አርበኛ ግንባር እንደሚንቀሳቀስ እኔም አውቃለሁኝ። ግንባሩ ከኢህአዴግ ጋር ትግል ከገጠመ ቆይቷል።
ታድያ የጎንደሯ ማርዬ፤ በስደት ያረፈችበት ኬኒያ ወደ ዘመዶቿ እንዲቀላቅላት “ወደ ጎንደር መመለስ አልችልም” ብላ ስትናገር አበቷ የአርበኛ ግንባር አባል እንደነበሩ፣ ከዛም በአንዱ ውጊያ እንደተማረኩ፣ ከዛም መንግስት የት እንዳደረሳቸው እንደማታውቅ፣ ከዛም አልፎ ጨካኙ መንግስት፣ እርኩሱ መንግስት እነርሱን፤ ልጆቻቸውን ማደን ሲጀምር እንደወጣች የሚያስረዳ “ኬዝ” ተጋግሮላታል።
ማርዬ ይቺን በደንብ አጥንታ ኢንተርቪው ያደረገች ጊዜ ስትናገር ስቅስቅ ብላ  እያለቀሰች እንደነበር ነገረችኝ። ምን ሆነሽ አለቀስሽ? ብላት “እንጃ አባቴን… ሀጥያቴ ይሆናላ! የውሸቴ ብዛት…!” አለችኝ። ማርዬን ስደተኞችን የሚቀበለው ድርጅትም ማልቀሷን ሲያይ ሆዱ ተንቦጫቦጨበት ከዛም አምኖ ተቀብላት። እናም በዛ ሰሞኑ ካናዳ ልትሄድ ጥቂት ቀርቷት ነበር። ካናዳ ስትገባ መጀመሪያ የምታደረገው ነገር ምን መሰልዎ… “ቄሱን አባቴን ጦረኛ በማለቴ ንስሀ እገባለሁ” ብላኛለች።
ሁለት
ከሀብቶም ጋር የተዋወቅነው አንድ “ኬዝ ጋጋሪ” ወዳጄ ጋር መጥቶ ነበር። ሀብቶም ገብረ ክርስቶስ ገብረ ማርያም ይባላል። “ኢትዮጵያ ውስጥ ከመኖር ወደ ሌላ ሀገር እየሄዱ መሞት ይሻላል።”  ይላል። የሀገር ቤት ኑሮ ሮሮ ሆኗል የሚለው ሀብቶም። ከመሀል አዲሳባ ነው ውልቅ ብሎ የወጣው። ስራ አጥነቱ አሰቃየኝ ከዛ በዚህ በኩል “ላጥ ማለት” ይሻላል ብዬ መጣሁ ብሎኛል።
ሀብቶም እዚህ እንደገባ በርካታ ኦሮምኛ ተናጋሪ ወዳጆች ነበሩት። ታድያ እነዚህ ኦሮሞ እና ኦሮምኛ ተናጋሪ ወዳጆቹ በሙሉ ኬዛቸውን የሰሩት “ኦነግ” ነን ብለው ነበር። ታድያ  እርሱስ ለምን ከጓደኞቹ ይለያል “ኦነግ” ነኝ ብሎ “ኬዝ” አስጋገረ። ይህንን “ኬዙን” ያየለት ወዳጄ የሀብቶም “ኦነግ” መባል አስደነቀው። ከዛም ይሔ ኬዝ መታደስ አለበት ብሎ ይህው ጥገና ያዘ። ሀብቶም በጓደኞቼ “ኦነግ” ነኝ ቢልም ድርጅቱ በሚያደርገው ማውጣጫ “ሪጀክት” የመባል እድሉ ሰፊ ነው። ፈረንጆቹ ስምህን ሁሉ አይተው ከየት አካባቢ እንደመጣህ መገመት ጀምረዋል ብሎኛል የ”ኬዝ” ባለሞያው ወዳጄ።
ሶስት
በልዩ እንደ አብዛኛው ስደተኛ “የኢኮኖሚ ስደኛ” ናት! “ቢያልፍልኝ ብዬ ነው ስወጣ ከሀገሬ…” ብላ የተሰደደች። ነገር ግን እዚህ ሀገር ለመኖር ወይም በወጉ ወደሌላ የተሻለ ሀገር ለመሸኘት ጥሩ አሳማኝ “ኬዝ” ያስፈልጋታል። ለኬዝ ጋጋሪዎች የሚከፈለውን እስከ መቶ ዶላር የሚደርስ ክፍያ መክፈል አቅም የላትም። ስለዚህ ራሷ ማሰብ አለባት ማለት ነው። በአንድ ወቅት ከቶጎዎች ጋር ኖራ የምታውቀው በልዩ አንድ ዘዴ መጣላት። ያኔ አብረዋት የነበሩት ቶጎዎች ከሀገራቸው የተሰደዱት “ቡዳ ናችሁ” ብሎ ማህበረሰቡ ስላገለላቸው ነበር። “…አሃ” አለች በልዩ ኬዟንም ጋገረችው። መጀመሪያ ስሟን ቀየረች፤ “የመጣሁት ከቶጎ ነው።” አለች። “ወደ ሀገርሽ መመለስ የማትችይበት ምክንያት ምንድነው?” አሏት። ፈቃጅ፤ ከልካዮቹ። ፈረንጆቹ። እሷም “ቡዳ ነኝ!” አለቻቸው። “ስለዚህ ያስወጣኝ ማህበረሰብ ዘንድ ድጋሚ ብቀላቀል ይገሉኛል። አለች።
አይደነቁ ወዳጄ በስደት ሀገር ተደላድሎ ለመቀመጥ ወይም ወደሌላ የሚደላ ሀገር ለመዛወር በርካቶች ያልሆኑትን ነን ብለው ሲናገሩ መስማት እዚህ የተለመደ ነው። አለበለዛ የስደተኞች ጉዳይን በሚመለከቱት “ሪጀክት” መባል ይመጣል። አንዳንዶቹ “ኬዞች” እጅግ በጣም ከሞራል በታች ናቸው…
አራት አምስት ስድስት…
በአንድ ወቅት ከሱማሌ የሚሰደዱ ዜጎች “ሂጃባቸውን” ፈተው “ክርስቲያን ስለሆንኩ ከሀገር አባረሩኝ” የሚል “ኬዝ” ይሰሩ ነበር። አሁን አሁን ደግሞ ከኤርትራ የሚሰደዱ ብዙዎቹ “ጴንጤ” ስለሆንኩ ወይም “ጆቭሃ” ስለሆንኩ ከሀገር ተናረርኩ ብሎ ማለት አሪፍ ኬዝ እየሆነ ነው። ምክንያቱም ኢሳያስ ነፍሴ በተለይ ጴንጤ እና ጆብሀዎችን ጠምደው ይዘዋቸዋል እና ነው።
በጣም ካስገረሙኝ ኬዞች ውስጥ “ግበረ ሰዶማዊ” ስለሆንኩ ከሀገር አስወጡኝ ተመልሼ ብሄድም ይገሉኛል። ብሎ የተሰራው “ኬዝ” ነው። ልብ አድርጉ አንድ ሰው የሌለበትን ያልሆነውን በራሱ ላይ ለጥፎ “ብቻ ወደ ሀገሬ አትመልሱኝ!” የሚለው ሀገሩ ምን ያህል አላስኖር ብትለው ነው? አቤቱ የምንዘምርላት ብቻ ሳይሆን የምንኖርባት አገር ስጠን ብሎ መፀለይ ይሄኔ ነው።
እስቲ ወዳጄ ለዛሬ በዚሁ ይብቃን እና ለሚቀጥለው ሞራላችንን አስባስበን እና ቤት ያፈራውን እንድናወጋ ያድርገን!
አማን ያሰንብተን!

No comments:

Post a Comment