Wednesday, December 12, 2012

በዩኒቨርስቲዎችና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ኢህአዴግ ስልጠና ሊሰጥ ነው


ታህሳስ ፫(ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢሳት የኢህአዴግ ምንጮች እንደገለጡት በመጪው ሳምንት በሚጀመረው በዚህ የስልጠና መርሀግብር የሁለተኛ ደረጃ ፣ የመሰናዶ፣ የኮሌጅ እና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ይሳተፋሉ። በመርሀ ግብሩ መሰረት ከነዚሁ የትምህርት ተቋማት የሚመረጡ ቁልፍ ተማሪዎች በቅድሚያ ስልጠና ከተሰጣቸው በሁዋላ፣ እነዚሁ ሰልጣኞች ተመልሰው በመሄድ ለተቀረው ተማሪ ስልጠና ይሰጣሉ።
ስልጠናው የሚቆየው ለአንድ ሳምንት ሲሆን፣ የሚሰለጥኑበት ሁኔታም በአብዛኛው ኢህአዴግ ባለፉት 8 አመታት ስላስገኛው ድሎች፣ ስለርእዮተ አለምና ስለእስልምና አክራሪነት ይሆናል። ስልጠናውን በፕላዝማ ቴሌቪዥን ለማካሄድ እቅድ መኖሩም የታወቀ ሲሆን፣ የመጨረሻ ውሳኔ እንዳልተሰጠበት ታውቋል።
አጠቃላይ እንቅስቃሴው በመጪው የካቲት ወር የሚካሄደውን የወረዳ ምርጫ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። መንግስት የዘረጋውን የአንድ ለአምስት አደረጃጃት በስፋት ወደ ነዋሪው ለማዳረስስ እየሰራ ነው።
በተለያዩ መስሪያ ቤቶች የሚገኙ ሰራተኞች በአንድ ለአምስት አደረጃጀት በመወጠራቸው ሌሎች ጉዳዮችን እንዳያስቡ እየተደረጉ መሆኑን ነው ሰራተኖች የሚናገሩት። ሰራተኞቹ በእየለቱ ከቀኑ 10 ሰአት ጀምረው ስለመስሪያቤታቸው የስራ እንቅስቃሴ ለአንድ ለአምስት ሰብሳቢው ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሰብሳቢውም እንዲሁ ለበላይ አለቃው መረጃዎችን በማስተላለፍ ገዢው ፓርቲ አጠቃላይ ፖለቲካ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር እንዲያመቸው ማድረጉን ሰራተኞች ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment