Monday, December 10, 2012

በቅርቡ በሁለት ልጆቿ አባት በ18 ጥይት ተደብድባ የሞተቸው ወ/ሮ ፍሬህይወት ታደሰ በወቅቱ ከፍሬህይወት ጋር አብረው በመኪና ውስጥ የነበሩትና በሶስት ጥይት የቆሰሉት እናቷ ወ/ሮ ተናኘ ሀ/ማርያም ከቁምነገር መፅሄት ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ


ቁምነገር፡- ፍሬህይወት በትዳር የነበራት ህይወት ምን ይመስል ነበር? 
ወ/ሮ ተናኜ፡- ፍሬህይወት በትዳር በሰላም የኖረችው ለአንድ ዓመት ብቻ ነው፡፡ ቀሪው 4ዓመት በመከራ ውስጥ ነበር የኖረችው ለማለት እችላለሁ፡፡ ነፍሷ አልወጣም እንጂ በጭንቅ ውስጥ ነበረች ያለችው፡፡

ቁምነገር፡- እንዴት?
ወ/ሮ ተናኜ፡- እየደበደባት፣ ፀጉሯን እየነጨ፣በረኪና ጠጪ እያለ ነበር የኖረችው፡፡ ለምሳሌ አንድ ጊዜ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ የፍሬህይወት ታናሽ ወንድም ማታ ቤታቸው ውስጥ ነበር፡፡ ታላቅ ወንድሜ የሚለው ሰውም ሊጠይቀኝ መጥቷል ይል ነበር፡፡ ከዛሌሊት ተነስቶ ሲደበድባት ወንድሟ እኛ ጋር ደውሎ ድረሱላት ይለናል፡፡ የለበስነውን ነገር አናውቅም፡፡ በለሊት ከአባቷ ጋር ተያይዘን ኮንትራት ታክሲይዘን እንሄዳለን፡፡ ግን እንዴት ብለን በር አስከፍተን እንግባ፡፡ በር ላይ ቆመን ሳለን ወንድም የተባለው ሰው መጣ፡፡ ከዚያ ‹‹ ወንድሜ ምን ድን ነው ችግሩ ጥፋቱስ የማን ነው?›› ብዬ ስጠይቀው ‹‹ልጅዎ ጋር ምንም ችግር የለም፤ ጥፋቱ ሁሉ የሱ ነው፡፡ የሚችሉ ከሆነ ልጅዎን ያድኑ›› ነበር ያለኝ፡፡ ከዛ ተያይዘን ወደቤት ውስጥ ስንገባ የሷ ፊት ቀልቶ ተቀምጣለች፡፡ እሱ ውስኪ በጠርሙስ ይዞ ተቀምጧል፤ ምንድን ነው ልጄ? ስለው‹‹ ምን ልትሰሩ መጣችሁ›› ነበር ያለን፡፡ ለምንድን ነው እንደዚህ የምትለው ስለው ወደ ሌላ ክፍል ገባ ትንሽ ቆይቶ ተመልሶ መጣ፡፡ ከዛ መዛት ጀመረ፡፡ ሁኔታው አላምር ሲለኝ ይዘናት እንሂድ አልኩት፡፡ ግን በሌሊት መጥተው ሚስቴን ይዘውብኝ ሄዱ ብሎ ለወሬ እንዲመቸው ሊያደርግ ይችላል ብዬ የለም ጠዋት ሲነጋ ችግሩን እንነጋገራለን ብዬ እዚሁነው እኔ የማድረው ብዬ መኝታ ቤት አስገብቻት በሩን ቆልፈን ተኛን፡፡ እሱ እዛው ውስኪውን ይዞሳሎን ተኝቶ 11 ሰዓት ሲሆን ተነስቶ ወጣ፡፡ እንደዚህ እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን እየፈፀመባት ነበር ዓመታት ያለፉት፡፡

ቁምነገር፡- ችግሮች ሲፈጠሩ በሽማግሌዎች በኩል ለመፍታት አልተሞከረም?
ወ/ሮ ተናኜ፡- የቀረ ነገር እኮ የለም፤ የቅርብ ሚዜዎች ሳይቀሩ የተከበሩ ትላልቅ የቤተክርስቲያን ሰዎች ሳይቀሩ ጉዳዩን ያላዩ ሰዎች የሉም፡፡ ሰውየው ምላሱ አይቻልም፤ የማይለው ነገር የለም፡፡ ዛሬ ተፈታ የተባለ ችግር ነገ እንደገና ይመጣል፤ ሰው ከቁብ የሚቆጥር ሰው አይደለም፤ በየጊዜው ይጠጣል፣ያጨሳል፤ ሌላው ቀርቶ ያድራል ያልቻለችው ነገር አልነበረም ፡፡

ቁምነገር፡- የቅርብ በሚባል በሱ ዘመዶች በኩልስ ችግሩን ለመፍታት አልሞከራችሁም?
ወ/ሮ ተናኜ፡- ምን ዘመድ አለው፤ እኛ የትስ እናውቃቸዋለን? ከሠርጉ በኋላ ለመልስም ሆነ ለቅልቅል ጊዜ ይዟቸው የሚመጣው ጓደኞቹንና ሚዜዎቹን ነው፡፡ መሰረቱንም ቤተሰቡንም አስተዋውቆን አያውቀም፡፡ ያው የሴት ልጅ ነገር ትውውቃቸው በውጪ ነው፡፡ ዘመዶችህ ቤተሰቦችህ እነማን ናቸው የሚል ጥያቄ አላቀረበችለትም፡፡ በውጪ ተዋውቀው ሽማግሌ ተላከ አባቷ አልቀበልም አለ ፡፡

ቁምነገር፡-ለምን?
ወ/ሮ ተናኜ ፡- የመጡት ሰዎች የራሱ ስራ አለው፣ ትልቅ ሰው ነው፣ ቤቱም እዚህ ራስ አምባ ሆቴል አጠገብ ነው ምናምን አሉ፡፡ አባቷ ግን ልጄን አልሰጥም አለ፡፡ ምክንያቱም ፍሬህይወት ገና ልጅነች ለትዳር ሳይሆን ለትምህርቷ ነው ቅድሚያ መስጠት ያለባት፤ ካገባች ትወልዳለች፣ ከወለደች ደግሞ ትምህርቷን ለመማር አትችልም፤ ትምህርቷን ትጨርስና ይደርሳል ነው ያለው፡፡ ሽማግሌዎች ለ12 ጊዜ ያህል ቀጠሮ ስጡን እያሉ ተመላልሰዋል፡፡ ፍሬህይወት ያን ጊዜ ገና 22 ዓመቷ ነው፡፡ እሱ ግን የሚተኛ ሰው ስላልነበር የሚያሸንፉንን  ሽማግሌ የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ማህበርተኛችን ትልቅ ካህን ይዞ መጥቶ እንዲገስፁንና እንዲቆጡን አስደርጎ በስተመጨረሻ ተሸነፍንለት፡፡ አባቷ እንኳ የዛን ጊዜ ሁሉ እንቢ ብሎ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ምናልባት ይህን ያህል ጊዜ ሽማግሌዎች የተመላለሱት ልጄ ፀንሳ ይሆን እንዴ ብዬ በማሰብ ማታ ስትመጣ ጠብቄ አጥብቄ ጠየቅኳት፡፡ እሷ ግን ፈፅሞ እንደዚህ አይነት ነገር ነበር የለም ያለችው፡፡ ከዛ አባትየው ባይስማማም ቀን ተቆርጦ ያሁሉ እናንተ ባለፈውጊዜ የዘረዘራችሁት ሠርግ ተደገሰ፡፡ በመጨረሻም ሁኔታው አላምር ሲላት ወደ ፍርድ ቤት ሄደች ፡፡

ቁምነገር፡- ፍቺ?
ወ/ሮ ተናኜ፡- አዎ የሱ ሽማግሌዎች ሳይቀሩ እኛ በዚህ ጉዳይ ውስጥ ከዚህ በኋላ አንገባም ብለው እስከማለት ደርሰዋል፡፡ በትዳሩ ላይ እንዴት እንደሚወሰልት ፣የት ሆቴል ከማን ጋር መቼ እንዳደረ ሁሉ ጠይቃ መረጃ ይዛበታለች፤ ድምፁን ሁሉ በስልክ ቀድታዋለች፤ እሱ እራሱ ድርጊቱን ከማፈር ይልቅ በግልፅ ተናግሮታል፡፡

ቁምነገር፡-ምን ብሎ?
ወ/ሮ ተናኜ፡- ያው እንደሚታወቀው የብሎኬት ማምረቻ አለው፡፡ በተያያዘ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ጨረታ አሸንፌ ግን ብሩን ሊለቁልኝ አልቻሉም፡፡ እዚህ ያሉት ሰዎች ጉቦ ካልሰጠኸን ብለው እንቢ ስላልኳቸው ገንዘቤን ሊያስቀሩብኝ ሲሉ ገንዘቤን ለማግኘት ስል እዛ የምትሰራና ልታስለቅቅልኝ የምትችል ልጅ ይዤ በተደጋጋሚ በማደር ላስለቅቅ ቻልኩ ብሎ የተናገረ ሰው ነው ፡፡ ይሄ እኮ የሚገርም አይደለም፡፡ ኮንዶም፣ የሴቶች ልብሶች ምን የቀረ ነገር አለ መኪናው ውስጥ አግኝታበታለች፡፡ ለሽማግሌዎች እነዚህን ሁሉ ነገሮች ከተናገረች በኋላ ከዚህ በኋላ ልጆቼን በሰላም ላሳድግ ብላ ነው ወደ ፍርድ ቤት የሄደችው፡፡

ቁምነገር፡- የእሱ ምላሽ ምን ነበር?
ወ/ሮ ተናኜ፡- በተጋቡ በሁለተኛው አመት ሌሊት የደበደባት ጊዜ ቤቱ ሄደን እያለ ‹‹ውሰዷት ልጃችሁን አልፈልጋትም›› ነበር ያለው፡፡ የዛን ጊዜ እንደውም አንድ ልጅ ወልዳ ሁለተኛውን ቅሪት ነበረች፡፡ ግን ውሰዷት እያለ ነበር ሲደነፋ የነበረው፡፡ ፍርድ ቤት ለፍቺ ተከሶ ሲቀርብ ግን ፍቺውን ለማክሸፍ ያላደረገው ጥረት የለም፤ አልሆን ሲለው ደግሞ እገላለሁ እያለ ሲዝት ነው የቆየው፡፡

ቁምነገር፡- ፍቺው በፍርድ ቤት ከፀደቀ በኋላ የንብረት ክፍፍሉስ?
ወ/ሮ ተናኜ፡- ምንም የተከፋፈለችው ንብረት የለም፡፡ አልፈልግም በጤናዬ ብቻ መውጣት ነው የምፈልገው ነው ያለችው፡፡

ቁምነገር፡-ለልጆቹ ማሳደጊያስ?
ወ/ሮ ተናኜ፡- የፍርድ ቤቱን ወረቀት ላሳይህ እችላለሁ፡፡ እኔ ይቅርብኝ ለልጆች ማሳደጊያ ግንይስጠኝ በወር 50 ሺህ ብር ያገኛል ብላ በፍርድ ቤት ስታመለክት የምችለው በአንድ ልጅ 500 ብር ነው በየወሩ አንድ ሺህ ብር እሰጣለሁ ብሎ ነው የፀደቀለት፡፡ ለዚያውም ያንን አንድ ሺህ ብር በየወሩ አይሰጣትም ነበር፡፡

ቁምነገር፡- ራስ አምባ ሆቴል ጋር ያለው ቤት የእርሱ አለመሆኑ ለፀባቸው ምክንያት እንደሆነ የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ፤ ፍሬህይወት የምታውቀው ነገር ነበር?
ወ/ሮ ተናኜ፡- እኔ ይሄንን አላቅውም፡፡ ቤቱ የሱ ይሁን የሌላ ሰው ይሁን እኛ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ የእኔ ነው ብሎ ሲያወራ ብቻ ነው የምናውቀው፡፡ ሰውየው ለነገሩ የማይቀጥፈው ነገር የለም፡፡ ከዚህ በፊትም ወደዚህ ወደ ሲኤምሲ አካባቢ የሚያሰራ ህንፃ አጠገብ መኪናውን አቁሞ ፎቶ በማስነሳት እዚህ እኛ ጋር አምጥቶ በማሳየት ይህ ህንፃ የኔ ነው በቅርቡ ጨርሼው ወደ እዛ ቤት እንገባለን እያለ ይነግረን ነበር፡፡ በኋላ ግን ህንፃው የእሱ አለመሆኑን ደርሰንበታል፡፡ የተባለውም ቤት የሱ ይሁን አይሁን የምታውቀው ነገር የለም፡፡ ህዝብና መንግስት ረድተውን ካላጣሩልን በስተቀር አናውቅም፡፡

ቁምነገር፡- ከፍቺ በኋላ ፍሬህይወት ምን ትሰራነበር?
ወ/ሮ ተናኜ፡- አንድ ትንሽ የጉዞ ወኪል ድርጅት ገና በማቋቋም ላይ ነበረች፡፡ ንግድ ፈቃድ አውጥታ ቢሮ ገና እያደረጀች ነበር፡፡ ልጆቿ ከሌሎች ልጆች እንዳያንሱ በትምህርታቸውም በልብሳቸውን ለመቻል እሷ ቀን ሙሉ ፆሟን እየዋለች ነበር እራሷን ለመቻል ደፋ ቀና የምትለው፡፡

ቁምነገር፡- ቅዳሜ ቅዳሜ ልጆቹን የሚወስደው ከየት ነው?
ወ/ሮ ተናኜ፡- ከዚህ ከኛ ቤት ነው የሚወስዳቸው፡፡ ቀኑን ሙሉ አጫውቶ የሚመልሰው እዚህ ነው፡፡ እሷ ተከራይታ ነው የምትኖረው፡፡ ከተፋቱ በኋላ ልታገኘው ስለማትፈልግ ከሁለት ሰዓት በፊት በጠዋት አምጥታቸው ቶሎ ነው የምትሄደው፡፡ ማታም መጀመሪያ መምጣቱን በስልክ አረጋግጣ ነበር መጥታ የምትወስዳቸው፡፡

ቁምነገር፡- በስልክ አይገናኙም ነበር?
ወ/ሮ ተናኜ፡- ፈፅሞ አይገናኙም፤ ከፍቺ በኋላ አንድ አመት ከስድስት ወር ስልኩንም አንስታ አታውቅም፤ አታናግረውም፡፡ ልጆቿን ግን ፍርድቤት በወሰነው መሰረት ወስዷቸው ይመልስ ነበር፡፡

ቁምነገር፡- ከግድያው ቀን በፊት የግድያ ዛቻ በደብዳቤ ፅፎ ልኮ እንደነበር ሰምቻለሁ፤ ምንድንነው?
ወ/ሮ ተናኜ፡- በቃሉ በተደጋጋሚ ሲዝት ነበር፡፡ እንደውም የእሷን ታናሽ ወንድም እዚህ አፍሪካ ዳቦ ቤት ጋር ደውሎ ጠርቶት አንድ ጥይት ይበቃታል ንገራት ብሎት ነበር፡፡ ይህንን ስንሰማ ምስክሮች ይዘን በመሄድ ፖሊስ ጣቢያ አመልክተን ነበር፡፡ያው ምን እንደተባለ አናውቅም ተለቀቀ፡፡ ከግድያው አንድ ሳምንት በፊት ደግሞ ልጆቹን ወስዶ አጫውቶ ሲመልሳቸው የአንድ ዓመት ወንዱ ልጅ ኪስ ውስጥ ደብዳቤ ፅፎ አስቀምጦ ነበር፡፡ ያንን ወረቀት ያገኘነው ከቀብር በኋላ ቤት ውስጥ ያሉትን ልብሶች ለማጠብ ስናገላብጥ ነው፡፡ እሷም የዛን ዕለት የልጆቿን ልብስ ኪስ በደንብ ስላልፈተሸች ነው እንጂ ዛቻውን ልኮላትነበር፡፡

ቁምነገር፡-ደብዳቤው ምንድን ነበር የሚለው?ወ/ሮ ተናኜ፡- በቀደም ዕለት ‹‹ልጆቹን ከትምህርት ቤት ልትወስጂ የሄድሽ ጊዜ ግንባርሽን ብዬ ልደፋሽ ነበር ግን፤ ከዛ የተሻለ ሌላ መንገድ ስላለ ጠብቂ ነው››የሚለው፡፡ (ለቅሶ) የገደላት ዕለትም ለጓደኛው ፃፈ የተባለ ደብዳቤው ከኪሱ ውስጥ መገኘቱን ፖሊስ ተናግሯል፡፡ እዚህ ላይ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የምጠይቀው ነገር በእግዚአብሔር ስም ይህቺን የ29 ዓመት የልጆች እናት በክላሽንኮፍ ጠመንጃ በአደባባይ በጠራራ ፀሐይ መንግስትና ህዝብ ባለበት ሀገር በግፍ በገደላት ሰው ላይ ፍትህ እንዲሰጥ ነው፡፡ ሴት ልጅ እናት ነች፣ እህት ነች ፣ ሀገር ነች፡፡ስለዚህ ህዝቡ ለመንግስት ጩሀቴን እንዲያሰማልኝ በየሀይማኖቱ ስም ነው የምማፀነው፡፡(ለቅሶ)

ቁምነገር፡- አሉ የተባሉ ንብረቶችም ለማሳገድ ምን እያደረጋችሁ ነው?
ወ/ሮ ተናኜ ፡- እውነት ለመናገር በዚህ በኩል ምን ማድረግ እንዳለብንና የት መሄድ እነዳለብን ገና አላውቅንም፤ ሀዘን ላይነው የከረምነው፤ ብሎኬት ማምረቻ የተባለውንም ወደ 20 ክፍሎች ያሉት ቤት፤ መኪናዎችም አሉ የተባሉት ለልጆቿ ማሳደጊያ ሊሆን ስለሚችል በህግ አግባብ በኩል ምን ማድረግ እንዳለብን ሙያው ያላቸው ወገኖች ቢረዱንን እንዲተባበሩን በሴት ልጆቻቸው አምላክ በእህቶቻቸውና በእናቶቻቸው ስም እለምናለው፡፡ ማንም የሚወዳት ሴት ልጅ ያለው ሁሉ ይተባበረን ነው የምለው ፡፡

ቁምነገር፡- በእርሶ በኩል ግን ለእንደዚህ አይነት ግድያ የሚያበቃ የከረረ ፀብ ወይም ምክንያት ብለው የሚገምቱት ነገርምንድን ነው?
ወ/ሮ ተናኜ፡- ምቀኝነት ነው፤ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡ ከሱ ከተለያየች በኋላ የሱ ሀሳብ ከነልጆቿ ሲርባት ተመልሳ ከእግሬ ላይ ወድቃ ቤት ትገባለች ነበር፡፡ ቢያይ አልሆነም፤ አሁን ራሷን ለመቻል ትንሽ ሱቅ ብጤ የትኬት ቢሮ ለመክፈት ደፋ ቀና ስትል ለምን እራሷን ለመቻል ትሮጣለች ነው፤ የትኬት ቢሮዋ እኮ ደግሞ ብታያት ገና ምንም ነገር ስራ ያልተጀመረበት ነው፤ የአየር መንገድ ትኬት የሚሸጥ ሰው በደንብ ስራን ያውቀዋል፤ ከተገኘም ከአንድ ትኬት ስለሚገኘው ብር ለዚያውም ትኬት የሚገዛ ሰው ከመጣ ነው፤ ለምን ይሄንን ከፈተች ነው የሱ ሃሳብ፤ ከዚህ ውጪ ይሄ ነው የሚለው ምክንያት አይታየኝም ፡፡ ምክንያቱም ከተፋታች በኋላ እንኳን አምስት ሳንቲም አልጠየቀችውም፡፡ ለልጆቿ በየወሩ ተቆራጭ መስጠት ያለበትን ብር ሲያስቀር እንኳን ለምን አትለውም፡፡ አሁን ልጆቿን ለማሳደግ ቀና ደፋ ስትል ቅናት አላስቀምጥአለው፡፡ የሱ ሃሳብማ ድሃ ሆና እንድትኖር ነው፡፡

ቁምነገር፡- እርስዎስ ጤናዎት እንዴት ነው?
ወ/ሮ ተናኜ፡- ደህና ነኝ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ተርፌያለሁ ልጄን ግን ገደላት፡፡

ቁምነገር፡- ከእርሶ ሌላ የተጎዳ ሰው ነበር?
ወ/ሮ ተናኜ፡- አዎ ሁለት መንገደኞች በጥይት ተመትተዋል፡፡ እንደውም አንዱ ሰውዬ በጣም ተጎድተዋል ተብሏል፡፡ መንገድላይ የነበረ የ10 ዓመት ልጅም ተመትቷል፡፡

ቁምነገር፡- በመጨረሻ የሚገልፁት ነገር ካለ?
ወ/ሮ ተናኜ፡- በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ላይ ቅሬታ አለን፡፡ እኛ በልጃችን ሞት ሳቢያ ሀዘኑ የእግር እሳት ሆኖብን ሳለ ሃሰተኛመረጃ ለህብረሰቡ ያሰራጩብን ጋዜጦችና መፅሔቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሪፖርተር ጋዜጣ፣ ቆንጆ መፅሔት ንብረት ተካፍላለች ከሱ በኋላ ልጅ ወልዳለች እያሉ ያቀረቡት ዘገባ መላ ቤተሰቡን አሳዝኗል፡፡ መረጃውን መጥተው ጠይቀው አረጋግጠው መዘገብ ሲገባቸው ያልሆነ አሉባልታ ይዘው በመውጣት ህብረተሰቡን ማደናገራችን ትክክል አይደለም፡፡ እኛ ልጃችንን አንድ ጊዜ በግፍ ተነጥቀናል፤ ዳግመኛ ታሪኳ መበላሸት የለበትም፤ ብለን እንዲያርሙ ስንጠይቃቸው የሚያርሙበት መንገድ የሚያሳዝንነው፡፡ ሴት ልጅ እንደ ወንድ ልጅ አይደለችም፡፡ ወንድ በድብቅ ወልዶ ልጅ ሊያመጣ ይችላል፤ ሴት ልጅ ግን ሰው ሳያያት ልታረግዝነና ልትወልድ አትችልም፡፡ ከሆነም ወለደች የሚሉትን አምጥተው ቢያሳዩን ጥሩ ነው ፡ ፡ አልሆነም እንጂ ከዚያ ውጪ ከተፋታች በኋላ ብትወልድስ ችግሩ ምንድን ነው፡፡ ስለዚህ ሚዲያዎችን እባካችሁ ስለ ሴት ልጅ ብላችሁ እውነታን አታዛቡ ጠይቃችሁ ፃፉ ነው የምለው፡፡ በማንኛውም መልኩ የልጃችንን ሀዘን ሊካፈሉንና በህግም በኩል ሊረዱን የሚፈልጉ ሁሉ በ0911693061 ሊያገኙኝ ይችላሉ፡፡
ቁምነገር፡- አመሰግናለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment