ከኢህአዴግ የሽግግር መንግስት በኋላ እስከ 1994 ዓ.ም ድረስ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለገሉት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በሥልጣን ዘመናቸው ለማከናወን አስበው ካልተሳኩላቸው የቤተ-መንግስት እቅዶች መካከል አንዱን አጫውተውኛል። ዶ/ር ነጋሶ ርዕሠ-ብሄር ሆነው ወደ ብሄራዊ (ኢዮቤልዮ) ቤተመንግስት ከገቡ በኋላ የቤተመንግስቱን የተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው ተመለከቱ፡፡ ብዙ ለዓይን የሚስቡና ለጐብኚዎች አይን ማረፊያ የሚሆኑ ነገሮችን ያስተዋሉት ፕሬዚዳንቱ፤ አንድ ሃሳብ ብልጭ ይልላቸዋል። ቤተመንግስቱን በሰለጠኑት አገራት የጥራት ደረጃ ለማሰራት ነበር ያሰቡት፡፡ ይሄንን ዕውን ለማድረግም የሌላው ዓለም ቤተ-መንግስቶች ምን አይነት አሠራርና አካሄድ እንዳላቸው ያጠኑላቸው ዘንድ በወቅቱ የቤተ መንግስቱ አስተዳዳሪ የነበሩትን ጀነራል ፍሬ ሠንበት ወደ እንግሊዝና አሜሪካ ላኩ፡፡ ጀነራሉ ባመጡት መረጃ መሠረት፤ የአሜሪካው ኋይት ሀውስም ሆነ የእንግሊዙ ቤኪንግሀም በቱሪስቶች ይጐበኛል፡፡
ኋይት ሀውስ ፕሬዚዳንት ኦባማ ስራቸውን እያከናወኑም ቢሆን አልፎ አልፎ ክፍት እየሆነ በውስጡ ያሉ ቅርሶችና ታሪኮች እንደሚጐበኙ፣ የንግስት ኤልሳቤት መቀመጫ የሆነው የእንግሊዙ ቤኪንግሀምም ለጐብኚዎች ክፍት እየተደረገ የአገሩ ህዝብ መሪዎቹ የሚኖሩበትን ቤተ-መንግስት፣ ቅርሶች፣ የቀደሙ መሪዎችን ታሪክ ይጐበኛል፡፡ ስለሀገሩም በቂ ግንዛቤ ያገኛል። ይህን የሠሙት ዶ/ር ነጋሶ፤ “በዚህ አይነትማ የሀገሬ ቤተመንግስት ብዙ ሊጐበኙ የሚችሉ ነገሮች ሞልተውታል” በማለት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መምከር ይጀምራሉ፡፡ (ልብ በሉ! በወቅቱ ዶ/ር ነጋሶ የሚኖሩበት ቤተመንግስት ጣሪያ ያፈስ ነበር።) “ጀነራል ፍሬ ሠንበትን ልኬ ባስጠናሁት መሠረት የእኛንም ቤተመንግስት ለቱሪስት ክፍት ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀመርኩ” ይላሉ ዶ/ር ነጋሶ፡፡
በተለይ አሁን ፕሬዚዳንት ወ/ጊዮርጊስ የሚኖሩበት ብሄራዊ ቤተመንግስት ከንግስት ዘውዲቱ፣ ከልጅ እያሱና ከሀይለ ስላሴ እስከ መንግስቱ ኃ/ማሪያም የአገዛዝ ዘመን ድረስ ያሉ በርካታ ቅርሶችን የያዘ በመሆኑ ለሙዚየምነት ከበቂ በላይ ነው፡፡ የኃይለስላሴ እና ሌሎች የልዑላን ቤተሠቦች ያገኟቸው ሽልማቶች፣ የጦር ሜዳ መሣሪያዎች፣ አልባሣት፣ የቤት እቃዎችና መሠል በርካታ ቅርሶች በቤተመንግስቱ ውስጥ ቢኖሩም የሀገሬው ህዝብ ግን ሊያያቸው ቀርቶ ከነመኖራቸው ማወቁንም ይጠራጠራሉ – ዶ/ር ነጋሶ፡፡ “ሌላውን ተይው ኃይለ ስላሴ ሊታሠሩ ሲያዙ ከአልጋ ላይ የወረዱበት ነጠላ ጫማና ፒጃማ ሳይቀር በቤተመንግስት ይገኛል” የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ መታጠቢያ ቤት ሲገባ የጢም መላጫቸው፣ ሳሙና፣ ፎጣና ሌሎች ነገሮች እንደሚገኙም ነው ያጫወቱኝ። ዶ/ር ነጋሶ እንደሚሉት፤ ይህንን ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሊያየው ይገባል፡፡ “እኛ አገር ስለ ቱሪዝም ሲወራ ቶሎ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው የፈረንጅ ጐብኚ ነው፡፡ ሀገሬው ሊጐበኛቸው የሚገቡ በርካታ ቅርሶች እንዳሉን ግን እንዘነጋዋለን” ይላሉ፡፡ የሆኖ ሆኖ እቅድ ወጣ፡፡
እቅዱም በብሔራዊም ሆነ በታላቁም ቤተ መንግስት ያሉ ቅርሶችን ለህዝብ ክፍት አድርጐ ለማሣየት፣ በታላቁ ቤተ መንግስት ግቢ ውስጥ አንድ ሙዚየም መገንባት ነው፡፡ ይህን እዉን ለማድረግ ከብሔራዊ ቤተ መንግስት ተነስቶ በሒልተንና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፊት ለፊት በሚገኘውና ሼክ መሀመድ አሊ አላሙዲን ባሠሩት “አፍሪካ ፓርክ” አናት ላይ በድልድይ መልክ አልፎ ታላቁ ቤተ-መንግስት ድረስ የሚሄድ መንገድ መገንባትና ለጐብኚ ክፍት ማድረግ ነበር። የመንገዱ ዋና አላማ ብሄራዊ ቤተመንግስቱ ውስጥ ያሉትን ቅርሶች የሚጐበኙ ሠዎች፤ ከዚያ ወጥተው ላይኛው (ታላቁ) ቤተመንግስት ሙዚየም ለመግባት እንዳይቸገሩ ለማድረግ እንደነበር ዶ/ር ነጋሶ ይናገራሉ፡፡ በታላቁ ቤተ መንግስት ውስጥ አዲስ ከሚገነባው ሙዚየም በተጨማሪም የአፄ ምኒሊክ ቤተ መንግስት ስለሚገኝ እግረ-መንገዱን መጐብኘት ይችላል የሚል ሀሣብ መካተቱን የሚናገሩት ዶ/ር ነጋሶ፤ ይህም የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ወጣቱ ስለሀገሩ እያወቀና እየተገነዘበ እንዲሄድ በማሰብ ዝግጅት መጀመሩን ያስታውሳሉ፡፡
የሙዚየም ዕቅዱን እውን ለማድረግ ዲዛይን ሁሉ ተዘጋጀ፡፡ በጀትም ተመደበ፡፡ ወደ ስራ ሊገባ በዝግጅት ላይ እንዳለ የ1993 ዓ.ም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መጣና በነጋሶ የሞቀ እቅድ ላይ ውሀ ቸለሠበት፡፡ ሁሉም ትኩረቱን ወደ ጦርነቱ ከማድረጉም በተጨማሪ “የሙዚየሙን ጉዳይ እውን የምናደርግበት ገንዘብ የለንም” ተባሉ፡፡ ይህን የመሠለ የነጋሶ ድንቅ ዕቅድም በሀሣብ ብቻ መቅረቱን ያስታውሳሉ – ዶ/ር ነጋሶ። ይህንን ነግረውኝ ሲጨርሱ ትዝ ያለኝ የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” የተሰኘ መፅሃፍ ነው፡፡ እኔም መክሸፍ እንደ ነጋሶ ሃሳብ” አልኩኝ ለራሴ፡፡ ዶ/ር ነጋሶ የሙዚየሙ ጉዳይ እንዲሣካ ከፍተኛ ፍላጐት እንደነበራቸው ይናገራሉ፡፡ ሙዚየሙን ለማስገንባት የቦታ ጥያቄ እንዳይነሳ በመፍራት “ፕሬዚዳንቱ በህገ-መንግስቱ እንደተቀመጠው ብዙ የአስተዳደር ስራ ላይ አልተቀመጠም፤ ለመኖሪያ የሚያገለግል አነስተኛ ቤትና ትንሽ ፅ/ቤት ብቻ ይበቃዋል፤ ሌላው ለጉብኝት ክፍት ይሁን” የሚል ሀሣብ አቅርበው እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ አልተሳካም፡፡ የክሽፈት ታሪካችንን አያችሁልኝ!!
No comments:
Post a Comment