Monday, May 13, 2013

“የጠቅላይ ኦዲተር ባለስልጣን በየዓመቱ የሚያቀርበው ሪፖርት አስገራሚና አሳዛኝ ቢሆንም የዘንድሮው ግን አስደንጋጭ ነው



ከሳምንት በፊት የፌደራሉ ጠቅላይ ኦዲተር ያቀረበው አስገራሚ ሪፖርት ያንገበገባቸው ወገኖች “ምን እየተደረገ ነው? መንግስት አለ ወይ?” በማለት ጥያቄ አቅርበው እንደነበር የሚያስታውሱ “የጠቅላይ ኦዲተር ባለስልጣን በየዓመቱ የሚያቀርበው ሪፖርት አስገራሚና አሳዛኝ ቢሆንም የዘንድሮው ግን አስደንጋጭ ነው” የሚሉት አስተያየት ሰጪ፣ ሪፖርተርና ሰንደቅ ጋዜጣ ያቀረቡትን ዜና በዋቢነት ያቀርባሉ።
. 1.4ቢሊዮን ብር ያልተወራረደ ሒሳብ አለ
. 313.6 ሚሊዮን ብር ዕዳ ሳይመልሱ የተሸጡ ድርጅቶች አሉ
. 897.5 ሚሊዮን ብር ሕጋዊ ያልሆነ ክፍያና ወጪ ተደርጓል
. ያልተወራረደው 1.4 ቢሊዮን ብር በ57 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የታየ ነው
. 15 ድርጅቶች ወይም መሥሪያ ቤቶች ከልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ምንጮች ገቢ የሚሰበስቡ ቢሆኑም፣ የገቢ ሪፖርት የማያደርጉ በመሆኑ ኦዲት ማድረግ አልተቻለም
. በ13 ናሙና መሥሪያ ቤቶች የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ 132.364 ሚሊዮን ብር በወጪ ተመዝግቧል
. 22 መሥሪያ ቤቶች 13.8 ሚሊዮን ብር ማስረጃ የሌለው ወጪ አድርገዋል
. 30 መሥሪያ ቤቶች ደንብና መመርያ በመጣስ 353.568 ብር የሚያወጣ ግዥ ፈጽመዋል
. በውሎ አበልና በትርፍ ሰዓት ተመን 11 መሥሪያ ቤቶች 1.4 ሚሊዮን ብር አባክነዋል
. በኤርፖርት ተርሚናል የተሰማራ አንድ የግል ድርጅት ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ ለመቀበል ፈቃድ ሳይኖረው ከአሥር ዓመታት በላይ እየሠራ እንደሚገኝና ተቆጣጣሪ አካላት ያደረጉት ምንም ነገር የለም
. 134.7 ሚሊዮን ብር ብድር ያልመለሱ የመንግሥት ድርጅቶች መኖራቸውን
. የመንግሥት ትርፍ ድርሻ የሆነ 18.549 ሚሊዮን ብር ሳይከፍሉ የተሸጡ ድርጅቶች እንዳሉ
. 44.254 ሚሊዮን ብድር ያለባቸው ድርጅቶች ሲሸጡም የገዛው አካል ለመንግሥት መከፈል የነበረበትን እዳ ያልተከፈለ መሆኑን እና ተመሳሳይ የመንግስት ብክነትና ወንጀሎችን ጠቅላይ ኦዲተር ይፋ ያደረገው ለዚሁ “የተከበረ” ለሚባለው ፓርላማ ነበር፡፡
በቀረጥ፣ በሙስናና ባለስልጣናትን የንግድ ሸሪክ በማድረግ ኢትዮጵያን እየጋለቡዋት ያሉ “ባለሃብቶችና አሽከሮቻቸው” እስካልተነኩ ድረስ ኢህአዴግ በሙስና ላይ የጀመረውን ትግል ሙሉ ሊያደርገው እንደማይችል ተገለጸ። ጅማሮው የችግሩ ቁልፍና እምብርት በሆነው ተቋም ላይ መሆኑ የሚደነቅ እንደሆነ የሚገልጹ ክፍሎች ደግሞ ድሩ ያልተበተበው የለምና የመጨረሻው አካሄድ ወዴት እንደሚያመራ ለመገመት ቢቻልም ጅምሩ ይገፋል የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
የባለስልጣናት ሚስቶችን፣ ዘመዶችና ወዳጆችን በተቋሞቻቸው ውስጥ በማይመጥኑት ሃላፊነት በመመደብ፣ ከተለያዩ የማማለያ ሽልማቶች ጋር ከፍተኛ ደሞዝ በመክፈል፣ አንዳንዴም ውጪ አገር ድረስ የህክምና ወጪ በመሸፈን ሰበብ የአገሪቱን የአመራር በትር ጨብጠው አገሪቱን እያለቡ ያሉት ወገኖች በይፋ እንደሚታወቁ የሚገልጹ ክፍሎች “አሁን ተጀመረ የተባለውና ይፋ የተደረገው የሙስና ትግል እነዚህን ክፍሎች ብብቱ ስር ይዞ የሚቀጥል ከሆነ ከቀልድ አይዘልም” ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ያስቀምጣሉ።
አትራፊ የሆኑ የህዝብና የአገር ተቋማትን ወደ ግላቸው ያለ ክፍያ፣ ያለ ተመጣጣኝ ዋጋ፣ በተጭበረበረ ጨረታና አሰራር ወደ ግላቸው በማዞር አቶ መለስ “ተራው ህዝብ” በማለት በሚጠሩት ህዝብ ትከሻ ላይ እንዳሻቸው የሚዘሉትን “የሙስና አባቶችን” መታገል የማይችል የጸረ ሙስና ቀረርቶ ከተራ የፖለቲካ ልዩነት የዘለለ መነሻና መድረሻ ሊኖረው እንደማይችል እነዚሁ ወገኖች ይናገራሉ።
ሰሞኑን የመንግስት፣ የግል መሰል የድርጅት፣ የግል፣ የድረገጽ መገናኛዎች የተቀባበሉት ዜና የፌዴራሉ የጸረሙስናና የስነምግባር ኮሚሽን ይፋ ያደረገው የባለስልጣናት፣ የታዋቂ ነጋዴዎች እንዲሁም ተባባሪና የሙስናው ተዋናይ ናቸው የተባሉ አስራ ሶስት ሰዎች ስም የተጠቀሰበት እስር ነው። ይህንኑ ዜና በማድነቅ ጅምሩን የሚያበረታቱ ክፍሎች በበኩላቸው “ቢዘገይም፣ ችግሩና ንቅዘቱ እንዳለ ያደባባይ ሚስጥር ቢሆንም አሁንም አልረፈደምና ኢህአዴግ ለጀመረው የሙስና ትግል ድጋፍ መስጠት አግባብ ነው” ባይ ናቸው።
ኢህአዴግ “ገምተናል” በማለት ቃል ሳይመርጥ ራሱን ከፈረጀበት የሙስና አዘቅት አንድ ሁለት እያለ ዘመቻ መጀመሩ ሊበረታታ እንደሚገባ የሚጠቁሙ ክፍሎች “በአንድ ጀንበር ተዓምር መጠበቅ ከተራ የማንቋሸሽና ሁሌም የመቃወም አዝማሚያ ላይ የመኖር ያህል ያስቆጥራል። በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ጅማሬው ወዴት እንደሚያመራ አይታወቅምና በትዕግስት መከታተሉ የተሻለ ይሆናል” ሲሉ በቀጣይ ርምጃው እየሰፋ እንደሚሄድ ተስፋቸውን ይገልጻሉ። ዜናውን ያቀረበው ኢቲቪን ግን ይወቅሳሉ።
ኢቲቪ ዜናውን ሲያውጅ አቶ መለስን ካሉበት ሰፈር ቀስቅሶ በዋቢነት ማቅረቡ ከዜናው በላይ አስገራሚ እንደሆነ አስተያየት የተሰጠው አፍታም ሳይቆይ ነበር። አቶ መለስ “በተከበረው ፓርላማ” ፊት “ቁርጠኛ” በማለት የሾሟቸውን ባለስልጣናት “ሌቦች፣ ተስፈኞች” እያሉ ሲያበሻቅጡ በማሰማት የጸረ ሙስና ኮሚሽን “በከባድ የሙስና ወንጀል” ስላሰራቸው ባለስልጣናት የተናገረው ኢቲቪ፣ አቶ መለስ በህይወት እያሉ ለህዝብና ለወገን እንዴት ይቆረቆሩ እንደነበር አስታውሷል።
“… መንግሥት አንድ እጁን ታስሮ ነው የሚታገለው። እጁም እግሩም ያልታሰረው ተራው ህዝብ ነው። ስለዚህ ተራው ህዝብ በዚህ ትግል ውስጥ ሊሳተፍ ይገባል” በማለት ለተራው ምስኪን ኢትዮጵያዊ ሲያነቡለት የሚያሳይ ቅንጫቢ ወሬ በማሰማት የባለስልጣኖቹን መታሰር የመለስ ህልምና ትግል ውጤት ለማስመሰል የሞከረው ኢቲቪ፣ ጅማሬው ሊመሰገን የሚገባውን ተግባር እንዳደበዘዘው ነው አስተያየት ሰጪዎች ለጎልጉል የገለጹት። ዜናው አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ “… ዛሬውኑ ማስረጃ በመያዝ ለጸረሙስና ኮሚሽን አቅርቡ፣ እኔው እራሴ ተከታትዬ አስፈጽማለሁ” በማለት አቶ መለስን ተከትለው ቃል ሲገቡ አሰምቷል።ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነው የፌደራል የጸረ ሙስናና የስነ ምግባር ኮሚሽን ከብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎትና ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን ተጠርጣሪዎች ስም ይፋ አድርጓል። የኢህአዴግ አንደበት የሆኑት ዋልታ ኢንፎርሜሽንና ፋና ብሮድካስቲንግ የሁለቱን ዋና ባለስልጣናት ምስል አስደግፈው ያቀረቡት ዜና ግንቦት3 ቀን 2005 የፌዴራሉ የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን የገቢዎች ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታን እንዲሁም፣ ምክትል ዳይሬክተሩን አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስን ጨምሮ 12 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንና ኮሚሽኑ በግለሰቦቹ ላይ በቂ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ማሰባሰቡን፣ ጉዳዩ ለፍርድ ቤት እስኪቀርብ ድረስም ተጠርጣሪዎቹን በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲቆዩ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ በመግለጽ ነበር።
በቁጥጥር ስር የዋሉ 13 ሰዎች ስም ዝርዝር
1.የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታን
2.ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ
3.እሸቱ ወልደሰማያት በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር
4.አስመላሽ ወልደማሪያም የቃሊቲ ጉምሩክ ኃላፊ
5.ጥሩነህ በርታ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተወረሱ ንብረቶች አስተዳደር ቡድን መሪ
6.አምኘ ታገለ የናዝሬት ጉምሩክ ኃላፊ
7.ሙሉጌታ ጋሻው በኦሮሚያ ልዩ ዞን መሀንዲስ
8.ከተማ ከበደ የኬኬ ትሬዲንግ ባለቤት
9.ስማቸው ከበደ የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት
10.ምህረት አብ አብርሀ ባለሀብት
11.ነጋ ገብረእግዚአብሄር የነፃ ትሬዲግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤት
12.ዘሪሁን ዘውዴ ትራንዚተርና ደላላ
13.ማርሸት ተስፉ ትራንዚተርና ደላላ
የፌደራል የጸረ ሙስና ኮሚሽን በህግ አዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለያዩ ባለ ጉዳዮችና ከንግዱ ማህበረሰብ እንዲሁም፣ ከልዩ ልዩ መንግስታዊና ህዝባዊ አካላት ጥቆማዎችን ሲቀበል ቆይቷል። ጥቆማዎቹ በአንዳንድ የገቢዎችና ጉምሩክ መስሪያ ቤት ኃላፊዎችና ሰራተኞች እንዲሁም፥ በግል ንግድ በተሰማሩ ህገ ወጥ አካሄድን በሚያዘወትሩ ግለሰቦች ላይ ያተኮሩ” ነበሩ።
ኮሚሽኑ ከህዝቡ የተቀበላቸውን እነዚህን ጥቆማዎች መነሻ በማድረግም “ከብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል። በጥናቱም በቂ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ሰብስቧል” በማለት የኢህአዴግ ልሳኖች መረጃ ማሰባሰቡ በቅርብ የተጀመረ ጥናት መሆኑንን ይፋ ሲያደርጉ፤ ኢቲቪ በበኩሉ ውሳኔው አቶ መለስ በህይወት እንዳሉ አድርጎ ለማሳየት “ለረዥም ዓመት፣ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ክትትል ሲደረግበት ነበር” ብሏል።
ሙስና በስንጥር! ከዚያስ?
Melaku-Fenta-Gebrewahid-Woldegiorgis
መላኩ ፈንታና ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ (ፎቶ Fortune)
አቶ መለስ በህይወት እያሉ በግልጽ የሚያውቁትን “የመበስበስ በሽታ” በእንጭጩ ከመቅጨት ይልቅ በማስፈራሪያነት ለንግግራቸው ማድመቂያ፣ ለሃላፊነታቸው ማስቀጠያ፣ ለተቀናቃኞቻቸው አንገት ማስደፊያ አድርገውት ይጠቀሙበት እንደነበር የሚያሳይ ተግባር ተከናውኗል ብለው የሚያምኑ ወገኖች እንደሚሉት “አሁን የተወሰደው ርምጃ በፖለቲካው አውራዎች መካከል ተፈጥሯል የተባለውን ልዩነት ተገን ያደረገና ተቀናቃቀኞችን የማጥራት ከቀድሞ ጀምሮ የኖረ አሰራር ቀጣይ ምዕራፍ ነው” ሲሉ ግልጽ አቋም ለመያዝ እንደሚቸገሩ ይናገራሉ።
እነዚህ ክፍሎች እንደሚሉት አቶ ገብረዋህድ ሃቀኛ ለመምሰል ሙሽሮች ተውበው በሊሞዚን ሲሄዱ “ሊሞዚኑ በህገወጥ የስም ዝውውር ለሶስተኛ ወገን የተላለፈ ነው” በማለት ሙሽራ አስወርደው መኪናውን ያሰሩ፣ ዘይት በተወደደ ጊዜ ከንግድ ሚኒስትሩ ጋር በመሆን ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ “ነጋዴዎች ሸቀጥ እየደበቁ የሚፈጥሩት ችግር ምስኪኑን ህዝብ እየጎዳው ነው። ለዚህ ምስኪን ህዝብ ልንደርስለት ይገባል። ጉዳዩ በዚህ ከቀጠለ አላስፈላጊ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል” ብለው መናገራቸውን ያስታውሱና አንድ ትልቅ ነጥብ ያነሳሉ። የገቢዎች ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትርነት ወይም ዳይሬክተርነት ቦታ ኮታው የኦህዴድ ሆኖ ሳለ ጉምሩክና ገቢዎች ሚኒስትር ሲቀላቀሉ ኦህዴድ ቦታውን እንዲያጣ የተደረገው በቀጥታ በአቶ መለስ ትዕዛዝ እንደነበር ይጠቁማሉ።
አቶ ገብረዋህድ ከጉምሩክ የነበራቸውን ሃላፊነት በመያዝ በሚኒስትር ማዕረግ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክትር ሆነው ሲሾሙ፤ የወቅቱ የጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት የኦህዴድ ሰው እንዲነሱ ተደርጎ ነበር። ስለወቅቱ ድራማ የሚያውቁት አስተያየት ሰጪዎች፣ በወቅቱ ኦህዴድ ቅሬታውን አቶ መለስ ዘንድ ይዞ ቀርቦ ነበር። አቶ መለስ የኦህዴድን ቅሬታ ወደ ጎን በማለት አቶ ገብረዋህድ ቦታውን በመያዝ እንዲቀጥሉ መወሰናቸውን ተከትሎ ኦህዴድ ውስጥ ጉምጉምታ እንደነበር ከነዚሁ ክፍሎች ለመረዳት ተችሏል።
ቦታው አጓጊ የሆነው ኬላዎች ላይ ለመጠቃቀምና በመቀራረብ ምደባ በማካሄድ በትስስር ኮንትሮባንድ ንግድ ውስጥ ለመግባት አመቺ በመሆኑ እንደሆነ ያመለከቱት ክፍሎች “ከኬላ ጋር በተያያዘ ሁሉም ሃላፊነትና የምደባው እርከን አቶ ገብረዋህድን ስለሚመለከት፣ ምርመራው በጥብቅ ከተያዘ ወንጀሉ አቶ ሃይለማርያም እንዳሉት በሞቀ ሳሎናቸው የተቀመጡ በርካታ ሰዎችን ማዳረሱ አይቀርም”።
ይኸው ሙስናን በስንጠር የሚል ስያሜ የተሰጠው ርምጃ ተከትሎ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ባለስልጣኖች በላይ የኬኬ ሃላፊነቱ የተወሰነ የንግድ ማህበር ባለቤት አቶ ከተማ ከበደና የነጻ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ነጋ ገ/እግዚአብሄር ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል። የሁለቱ ቱጃሮች መታሰር በርካታ ነጋዴዎችን አስበርግጓል።
የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት ለሆቴላቸው ማስገንቢያ ከመንግሥት በብድር የወሰዱት ገንዘብ ለግንባታ ከሚፈጀው በእጥፍ የተጋነነ ግምት በመሆኑ የተበደሩትን ገንዘብ በሙሉ ለግንባታ ሥራ አላዋሉትም በሚል ከፍተኛ ቅሬታና ጥቆማ ቀርቦባቸው ነበር፡፡ በወቅቱ ስለሆቴሎች ብድር በቀረበ ጥናታዊ ጽሁፍ አብዛኛዎቹ ተበዳሪዎች ለአበዳሪ ባንኮች ኮሚሽን በመስጠት ከፕሮጀክት በላይ ብድር እንደሚወስዱ ተረጋግጦ ነበር፡፡ በዚሁ ስሌት መሠረት ከፕሮጀክት በላይ የሚወስዱትን የብድር ገንዘብ ወደ ዶላር በመቀየር በውጭ አገር ባንኮች እንደሚያቀምጡ የጸረ ሙስና ኮሚሽን ከበቂ በላይ መረጃ እንዳለው የጎልጉል ምንጮች አስታውሰዋል፡፡ የጎልጉል መረጃ አቀባዮች አንዳንድ መረጃዎችን ያሰባሰቡ ቢሆንም ከጉዳዩ ጥሬነት አንጻር ዝርዝሩን አሁን ከማቅረብ ታቅበናል።
በመጨረሻ በተገኘ ዜና የኮሎኔል ማዕረግ ያላቸው የአቶ ገብረዋህድ ባለቤትም ከፍተሻ የተረፉ ሰነዶችን ለመደበቅ ሲሞክሩ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰምቷል። የጎልጉል ምንጮች እንዳሉት ከዚሁ የሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ባለሃብቶችና ተጨማሪ ሰዎች ታስረዋል። ካገር እንዳይወጡ እየጠበቁ ያሉም አሉ።
source. facebook

No comments:

Post a Comment