Thursday, May 16, 2013

በምርጫ 97 የትዝታ ማህደር ውስጥ የልደቱ ቦታ



ከመሐመድ አሊ መሐመድ (ጋዜጠኛ)
እስኪ በትዝታ ፈረስ ሽምጥ እንጋልብና የምርጫ 97ን ሂደት እንደዋዛ እንዳስሰው፡፡ ምርጫ 97 ሲነሳ ከትውስታ ማህደራችን ጎላ ብሎ የሚወጣው የሚያዚያ 30 ትዕይንተ ህዝብ ነው፡፡ ለነገሩማ ያ ታሪካዊ ዕለት እንዴት ይረሳል? ወደ መስቀል አደባባይ የሚያመሩ መንገዶች ሁሉ በለውጥ መንፈስ በተሞላ የህዝብ ጎርፍ የተጥለቀለቁበት፣ ያለማንም ቀስቃሽ ህዝብ ለመብቱና ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ ሆ! ብሎ የወጣበት፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ብቃት ያረጋገጠበት፣ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ዓለምን ያስደመመበት ያ ታሪካዊ ዕለት እንዴት ይረሳል?
ሚያዚያ 30ን ስናስታውስ አንድ ክስተትም አብሮ ይታወሳል፡፡ “ዴሞክራሲን እናወድስ” በሚል መሪ ቃል መስቀል አደባባይና ዙሪያ ገባውን ባጨናነቀው ህዝብ መሐል አንድት ፒክ-ኣፕ መኪና ወደ አደባባዩ እምብርት ዘለቀች፡፡ በመኪናዋ ላይ በኢትዮጵያ ባንዲራ ደምቆ የለውጥ ሀዋርያነቱን የሚያውጅ ሰው ነበር፡፡ ህዝቡም ያን የለውጥ ሀዋርያ በፍቅርና በስስት ስሜት እጁን ለመንካት ይረባረብ ነበር፡፡ እሱም እጆቹን በማውለብለብ አፀፋና ምስጋናውን ይገልፅ ነበር፡፡ በወቅቱ ስለዚያ የለውጥ ሃዋርያ አንዳች አሉታዊ አስተያየት መስጠት ትልቅ ዋጋ ያስከፍል ነበር፡፡
ከምርጫው በኋላም ያ የለውጥ ሀዋርያ በድርጅቱ ጽ/ቤት ታገተ ተብሎ ህዝቡ በፆም በፀሎት ተጠመደ፡፡ በርካቶች ባገኙት ሚዲያና መንገድ ሁሉ እገታው የፈጠረባቸውን ስሜት በእንባና ሲቃ ሲገልፁ ተደመጡ፡፡ ግና በዚች ምድር ቋሚ ነገር የለምና ያ የለውጥ ሀዋርያ ተብሎ የተወደሰ ሰው ብዙም ሳይቆይ በካሀዲነት ተፈረጀ፡፡ ያ ሰው ማን እንደሆነ ግር የሚለው ሰው ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያለገደብ የተሞገሰና የተወገዘ! ግን ለምን?
ስለልደቱ አያሌው ብዙ ተብሏል፡፡ እኔ የተባለውን ሁሉ አልጋራም፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ የስልጣን ጉጉት እንዳላቸው አውቃለሁ፡፡ ቢሆንም የፖለቲካ ትግል የመጨረሻ ግቡ ሥልጣን ይዞ ዓላማን ማስፈፀም በመሆኑ የሥልጣን ጥማት እንደነውር ሊታይ የሚገባው አይመስለኝም፡፡ ነውር የሚሆነው ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ መንገድ ሥልጣን ለመያዝ ሲባል የቆሙለትን ዓላማ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡ በተለይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን በሚደረግ ትግል ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ መንገድ ሥልጣን ለመያዝ መሞከር የትግሉን ዓላማ ምን ያህል ሊጎዳው እንደሚችል መገመት አያስቸግርም፡፡
ከዚህ አንፃር አቶ ልደቱ በተለያየ ጊዜ ከሥልጣን ሽኩቻ ጋር በተያያዘ ትግሉን የሚጎዱ አፍራሽ እርምጃዎች ወስደዋል፡፡ አቶ ልደቱ በቀድሞው መዐህድ (የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት) አመራርና በወጣቶች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ሳቢያ ድርጅቱን ለቀው ሲወጡ የወሰዱት እርምጃ የድርጅቱን ገፅታ ከማጠልሸቱም በላይ በትግሉም ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት አድርሷል፡፡ በኋላም ኢዴፓ ከተቋቋመ በኋላ በፓርቲው መሥራች አባላት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት አቶ ልደቱ ተቀናቃኞቻቸውን ለማስወገድ የተከተሉት መንገድ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መቆማቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነበር፡፡ በወቅቱ የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውን የፖለቲካ ሰብዕና ለመግደል/ሽባ ለማድረግ (character assassination/paralization) በእሳቸው ላይ ሲደርስ ያወገዙትን አሉባልታ የመንዛትና ስም የማጥፋት ስልት መከተላቸው አይዘነጋም፡፡
አቶ ልደቱ የራሳቸው ምክንያት ቢኖራቸውም ፓርቲያቸው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በነበረው የትግልና የትብብር ግንኙነቶች ላይም የሚወስዷቸው አቋሞች እንደዚሁ ትግሉን የሚጎዱ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ በተለይም በ1997 ዓ.ም በተፈጠረው #ቅንጅት$ ውስጥ አቶ ልደቱ ሲያሳዩት የነበረው ልታይ ልታይ ባይነትና አጉል #ብልጣብልጥነት$ በተቃውሞው ጎራ ውስጥ በዓይነ-ቁራኛ እንዲታዩ ሳያደርጋቸው አልቀረም፡፡ ቅንጅት በ1997 ምርጫ ሂደት በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትና ድምፅ ካገኘ በኋላ ወደ ውህደት ሲያመራ የልደቱን የሥልጣን ፍላጎት ባለማርካቱ በእልህ ተነሳስተው የወሰዱት እርምጃ ታላቅ ታሪካዊ ስህተት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አቶ ልደቱ ለወሰዱት እርምጃ ምክንያት ቢኖራቸውም እርምጃውን የወሰዱበት ጊዜና መንገድ ከህዝብ እንዲነጠሉ በማድረግ ብዙ ፖለቲካዊ ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡
አቶ ልደቱ ለቅንጅት መፍረስ ምክንያት አለመሆናቸውን ለማሳመን ጥረት ቢያደርጉም በቀላሉ ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡ የእሳቸው መከራከሪያ ቅንጅትን አንድ ልደቱ የሚያፈርሰው ከሆነ ከጅምሩም ቅንጅት የሚባል ጠንካራ ኃይል አልነበረም የሚል ነው፡፡ በእርግጥም ይህ ክርክር በደምሳሳው ሲታይ እውነትነት ያለው ይመስላል፡፡ ነገር ግን አቶ ልደቱ በውህደት ስምምነቱ ላይ መሐተም ለማሳረፍ አሻፈረኝ በማለታቸው የኢህአዴግ መንግሥት ያቋቋመው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቅንጅትን የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ለመከልከል ምክንያት አግኝቷል፡፡ አቶ ልደቱና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የወሰዱት እርምጃ ቀደም ብሎ የተቀነባበረ ይሁን በድንገት የተፈጠረ ግጥምጥሞሽ ሊያስረዱን የሚችሉት አቶ ልደቱ ብቻ ናቸው፡፡
አቶ ልደቱ ቅንጅት ከፈረሰ በኋላ #ሦስተኛ አማራጭ$ በሚል ያመጡት የፖለቲካ ፈሊጥ ብዙዎችን ግራ ያጋባና እሳቸውንም ለባሰ የፖለቲካ ክስረት የዳረገ ነው፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አማካይ ቦታ/#ሦስተኛ አማራጭ$ እንደሚያስፈልግ ቢታመንም ይህን አቋም ለማራመድ በወቅቱ አቶ ልደቱ ትክክለኛው ሰው ነበሩ ለማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የ1997 ምርጫን ተከትሎ በተፈጠረው ውጥረት የቅንጅት መሪዎች ለእስር እስከተዳረጉበት ጊዜ ድረስ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል ለነበረው የተካረረ ግንኙነት አቶ ልደቱ ዋነኛው ተጠያቂ ናቸው፡፡
ስለሆነም #የጭፍን ተቃውሞ$ ፖለቲካን ለማውገዝ/ከማውገዛቸው በፊት አቋማቸውን የቀየሩበትን አሳማኝ ምክንያት ማቅረብና ቀደም ሲል ሲያራምዱት በነበረው የተካረረ አቋም ሳቢያ ለደረሰው ጥፋት ሁሉ ኃላፊነት መውሰድና ይቅርታ መጠየቅ ነበረባቸው፡፡ ይህን ሳያደርጉ ድንገት ተነስተው #ሦስተኛ አማራጭ$ በማለታቸውና የተቃውሞውን ጎራ ተጠያቂ በማድረጋቸው ህዝብ ሊያምናቸው አልቻለም፡፡ ይልቁንም ከገዥው ፓርቲ ጋር ለመሞዳሞድ እንደፈጠሩት ሥልት ተቆጥሮ በካሃዲነት አስፈርጇቸዋል፡፡ አቶ ልደቱ በተሳሳተ ስሌት በእጃቸው ውስጥ የነበረውን መልካም ዕድል ካጡ በኋላ ተስፋ ሳይቆርጡ ቢፍጨረጨሩም እንደዋዛ ያመለጣቸውን ዕድል በቀላሉ መልሰው እጃቸው ውስጥ ሊያስገቡት አልቻሉም፡፡
ይህም ሆኖ ግን አቶ ልደቱ አያሌው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሁነኛ ሥፍራ ያላቸውና የሚገባቸውም ሰው ናቸው፡፡ ወደተደራጀ የፖለቲካ ትግል ከገቡ ጀምሮ ያላቸውን ጊዜና አቅም አሟጥጠው ተጠቅመዋል፡፡ በተለይ የ97 ምርጫ ቅስቀሳ በእሳቸው ጫንቃ ላይ ያረፈ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በምርጫ ቅስቀሳው በአንድ በኩል የገዥውን ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች አንገት ሲያስደፉ በሌላ በኩል የተቃውሞውን ጎራ ደጋፊዎች አንጀት ያርሱ ነበር፡፡
አቶ ልደቱ በትግሉ ውስጥ ያላቸው ቆይታ በአንፃራዊነት አጭር ሊባል የሚችል ቢሆንም ያካበቱት ልምድና እውቀት ቀላል የማይባል ነው፡፡ በእኔ እይታ አቶ ልደቱ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ደርዝ ባለው መንገድ ለመገምገምና ለመተንተን ብቃት ካላቸው ጥቂት ኢትዮጵያውያን ተርታ የሚሰለፉ ናቸው፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው አቶ ልደቱ የተቃዋሚ መሪዎችን ቁጥር በአንድ የሚያሳድጉ ሳይሆኑ በኢትየጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትርጉም ያለው ሚና መጫወት የሚችሉ ሰው ናቸው፡፡ በእርግጥ አቶ ልደቱ የሚጫወቱት ሚና እንደየሰው አተያይ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የ1997 ምርጫን ተከትሎ አቶ ልደቱን የገጠማቸው ከህዝብ የመነጠል ፈተናና ፈተናውን በአሸናፊነት ለመወጣት ተስፋ ሳይቆርጡ ያደረጉት ጥረትም ስለሰብዕናቸው የሚነግረን ቁም ነገር አለ፡፡
አንዳንድ ሰዎች #ልደቱ ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ዳግም ላይመለስ የውድቀት ጽዋውን ተጎንጭቷል$ ሲሉ በኩራት ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን የልደቱ ከህዝብ መነጠል ለተቃውሞው ጎራ ውድቀት እንጅ በኩራት የሚገለፅ ስኬት አይደለም፡፡ የአንዳንዶቻችን በልደቱ ውድቀት መደሰት ከተራ ምቀኝነት ያለፈ ትርጉም ላይኖረው ይችላል፡፡ ልደቱ ሰው ነውና ተሳሳተ፡፡ የሚሳሳተው ደግሞ የሚሰራ እንጅ ከዳር ቆሞ የሚታዘብ አይደለም፡፡
በነገራችን ላይ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የቅንጅት መሪዎች ከእስር ከተፈቱ በኋላ የፈፀሙት ስህተት በምንም መመዘኛ ልደቱ ከፈፀመው ስህተት የሚያንስ አይደለም፡፡ ዱሮም ቢሆን ልደቱ የወሰደው እርምጃ የቅንጅትን ውድቀት አፋጠነው እንጅ ውሎ አድሮ ቅንጅትን ከመፈረካከስ የሚታደገው ኃይል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም የቅንጅት አፈጣጠርም ሆነ የሰው ኃይል ጥንቅር ረጅም ርቀት መጓዝ የሚያስችለው አልነበረም፡፡
እንደአለመታደል ሆኖ በቅንጅት ጥላ ሥር የተሰባሰቡት ሰዎች በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ መተያየት የማይፈልጉና አንዱ ሌላውን ጠልፎ ለመጣል የሚያደቡ ወይም በየጓዳ ጎድጓዳው የሚያሴሩ ስለመሆናቸው መሪዎቹ ከእስር በተፈቱ ማግሥት እውነቱ ገሀድ ሆኗል፡፡ ስለሆነም ለቅንጅት መፍረስ ልደቱን ብቻ ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ሁላችንም ድርሻ ድርሻችንን መውሰድ ይኖርብናል፡፡ እኔ የድርሻዬን ለማንሳት ዝግጁ ነኝ፡፡ ያ ታሪካዊ ሂደት “ውሾን ያነሳ ውሾ ይሁን” በሚል ብሂል ተሸፋፍኖ መቅረት ያለበት አይመስለኝም፡፡ በግልፅ ልንነጋገርበትና ልንማርበት ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለተቃውሞው ፖለቲካ መፃኢ ዕድል መነጋገር ካለብን ደግሞ #አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ$ እንዲሉ መሆን የለበትም፡፡

No comments:

Post a Comment