Monday, May 13, 2013

በባህር ዳር አንድ ግለሰብ ባልታወቀ ምክንያት 12 ሰዎችን ገደለ



bahirdarbest
አዲስ አበባ ፣ግንቦት 5 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በባህር ዳር ከተማ ልዩ ስሙ አባይ ማዶ በተባለ አከባቢ ፥ አንድ ግለሰብ  12 ሰዎችን ገደለ ፡፡
ከስፍራው የደረሰን መረጃ  ግለሰቡ  ሰክሮ እንደነበር ነው የሚያመለክተው ።
የባህር ዳር ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን መምሪያ ሀላፊ ኮማንደር ደረጀ አቻምየለህ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት ፥ ግለሰቡ በውል ባልታወቀ ምክንያት በመንገድ ላይ በከፈተው ተኩስ ከሞቱት 12 ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ሰዎች ክፉኛ ቆስለዋል ።
በሰዓቱም ግለሰቡን በቁጥጥር  ስር ለማዋል ፖሊስ ክትትል ሲያደርግ እንደነበርና  በመጨረሻም ራሱን  በወንዝ ውስጥ በመወርወር ህይወቱን እንዳጠፋ ነው ያመለከቱት ።
ድርጊቱን የፈፀመው ግለሰብ የፖሊስ አባል መሆኑን  የገለፁት  ኮማንደሩ ፥  ድርጊቱን  የፈፀመበት  ምክንያት ግለሰባዊ እንደሆነ አመልክተዋል ።
ትናንት ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ በተፈፀመው ድርጊት ከሞቱት መካከል ሴቶች ፣ ህፃናትና  አዛውንቶች ይገኙበታል ።
ከተገደሉት ግለሰቦች መካከልም የሰባቱ የቀብር ስነ ስርዓት በጋራ  ተፈፅሟል ።
በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ  የተገኙት የአማራ  ክልል  ርእሰ መስተዳድር  አቶ አያሌው ጎበዜም የክልሉ መንግስትም የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል ።
ጉዳዩን በመከታተል ዝርዝሩን ለህዝብ  ይፋ  እንደሚያደርግም ነው ያስታወቁት ።

No comments:

Post a Comment