- ተጠርጣሪዎች በድብደባና በግዳጅ ቃል እንዲሰጡ መደረጋቸውን ተናገሩ
ከሕገወጥ ነጋዴዎች፣ አስፈጻሚዎችና ከትራንዚት ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር በሕገወጥ መንገድ ከናዝሬት ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ሳይፈተሹ እንዲያልፉ በማድረግ፣ ሕገወጥ ጥቅም በማግኘትና ሀብት በማከማቸት የተጠረጠሩ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የአዳማና የሚሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጆችን ጨምሮ በጠቅላላው 54 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡
ግንቦት 5፣ 6 እና 9 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀረቡት ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ ግንቦት 12 እና 13 ቀን 2005 ዓ.ም. በአዲስ የምርመራ መዝገብ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ የወንጀል ችሎት ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረቡ 15 ተጠርጣሪዎች ተካተዋል፡፡
የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ግንቦት 12 ቀን 2005 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ፍርድ ቤት ያቀረባቸው የባለሥልጣኑ አዳማ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ያዴሳ ሚደቅሳ፣ የሚሌ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተክለአብ ዘርዓብሩክ፣ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሕግ ማስከበር ኃላፊ አቶ አምባውሰገድ አብርሃ፣ የሚሌ ቅርንጫፍ ሕግ ማስከበር ኃላፊ አቶ እሸቱ ግረፍ፣ የአዳማ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ቱጂ፣ የሞጆ ደረቅ ወደብ ትራንዚት ኢንስፔክተር አቶ መላኩ ግርማ፣ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ የላጋር ጉምሩክ መቅረጥ አስተባባሪ አቶ አስፋው ሥዩም፣ የአቃቂ ቃሊቲ የመጋዘን ቡድን ሠራተኛ አቶ ጌታነህ ግደይ፣ የቅርንጫፍ ሠራተኛ አቶ ዮሴፍ አዳዊ፣ የአልቲሜት ፕላን የግል ድርጅት ከፍተኛ ባለድርሻና አርክቴክት አቶ በእግዚአብሔር አለበል፣ አቶ ዘለቀ ልየው የበምጫ ትራንዚት ባለቤት ናቸው፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ማክሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ያቀረባቸው ተጠርጣሪዎች ደግሞ አራት ሲሆኑ፣ አቶ መልካሙ እንድርያስ የባለሥልጣኑ የናዝሬት ቅርንጫፍ ሠራተኛ፣ ወ/ሮ አልማዝ ከበደ የዋው ትራንዚት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ፣ በድለላ ሥራ የተሰማሩ አቶ ዳዊት መኮንንና አቶ ደጉ ኮቢቶ የሚባሉ ግለሰቦች መሆናቸው ታውቋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከሕገወጥ ነጋዴዎች፣ ጉዳይ አስፈጻሚዎችና ከትራንዚት ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር፣ በሕገወጥ መንገድ በናዝሬት በኩል የሚያልፉ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እንዳይፈተሹ በማድረግና በሕገወጥ መገድ ሀብት በማከማቸት ወንጀል የተጠረጠሩ መሆኑን፣ መርማሪ ቡድኑ ለተጠርጣሪዎቹና ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው ያልተጠናቀቀ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
መርማሪ ቡድኑ በአራቱ ተጠርጣሪዎች ላይ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቢጠይቅም፣ ፍርድ ቤቱ የ10 ቀናት ጊዜ በመፍቀድ ግንቦት 23 ቀን 2005 ዓ.ም. እንዲቀርቡ አዟል፡፡
በእነ አምባውሰገድ አብርሃ የምርመራ መዝገብ ግንቦት 12 ቀን 2005 ዓ.ም. ፍርድ ቤት የቀረቡት የአዳማና የሚሌ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆችን ጨምሮ 11 ተጠርጣሪዎች፣ ኃላፊነታቸውን ወደ ጐን በመተው ከሕገወጦች ጋር በመመሳጠር በናዝሬት በኩል ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች የጉምሩክ ሥርዓት ሳይፈጸምባቸው እንዲያልፉ በማድረግ፣ የተከሰሱ ሰዎችን ክስ በማቋረጥና በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ሀብት በማከማቸት ወንጀል መጠርጠራቸውን የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
የተጠርጣሪዎችን የተወሰነ ቃል መቀበሉንና የሰነድ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ መቻሉን ያስረዳው መርማሪ ቡድኑ ያልተሰበሰቡ የሰነድ ማስረጃዎች፣ የተጠርጣሪዎችን ቃልና የምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቅድለት ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከታሰሩ ጀምሮ ቤተሰብም ሆነ የሕግ አማካሪ ለማግኘት አለመቻላቸውን ለፍርድ ቤቱ አመልክተው፣ አማክረው እንዲመጡ እንዲፈቀድላቸው ሲጠይቁ መርማሪ ቡድኑም እንደማይቃወም በመግለጹ፣ ለግንቦት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. አማክረውና ተዘጋጅተው እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ከሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ጋር ተመሳሳይ በሆነ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡት የአቃቂ ቃሊቲ ጉምሩክ የሕግ ማስከበር ቡድን ኃላፊ አቶ ተመስገን ሥዩም፣ በዋና መሥሪያ ቤቱ የቅርንጫፍ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ተመስገን፣ የሞጆ ደረቅ ወደብ የዋጋ ትመና ኦፊሰር አቶ ቢኒያም ለማ፣ የሞጆ ደረቅ ወደብ ፍተሻ ሠራተኛ አቶ ስንሻው ዓለምነው፣ የሞጆ ደረቅ ወደብ የደንበኞች አጠቃላይ ቅሬታ ሰሚ አቶ ደረጀ መርጋ፣ አቶ ሥዩም ለይኩንና አቶ ኃይለ ማርያም አሰፋ የተባሉ የትራንዚት ሠራተኞች፣ ከመርማሪ ቡድኑ ጋር ክርክር አድርገው መርማሪው የጠየቀው 14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ በመፈቀዱ ለግንቦት 19 ቀን 2005 ዓ.ም. ተቀጥረዋል፡፡
በተጠረጠሩበት ወንጀል ግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም. ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም፣ ተሟልተው ባለመቅረባቸውና የምርመራ መዝገቡ የወንጀል መዝገብ መሆኑን በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ ለግንቦት 12 ቀን 2005 ዓ.ም. ተሟልተው እንዲቀርቡ ታዘው የነበሩት እነ ዳዊት ኢትዮጵያ ሰባት ተጠርጣሪዎች ነበሩ፡፡
ግንቦት 12 ቀን 2005 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ የተሰየመው ችሎት ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደው አቶ ዳዊት ኢትዮጵያ፣ አቶ ማሞ አብዲና አቶ አሸብር ተሰማ በባለሥልጣኑ በተለያዩ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሠራተኞች፣ አቶ ፍፁም ገብረ መድኅን፣ አቶ ማሞ ኪሮስ፣ አቶ አበበልኝ ተስፋዬና አቶ ኮነ ምሕረቱ ደግሞ በተለያዩ ሥራዎችና የትራንዚት ድርጅቶች ላይ የሚሠሩ ተጠርጣሪዎች ክርክር ነበር፡፡
ከአቶ አበበልኝ ተስፋዬ በስተቀር ስድስቱ ተጠርጣሪዎች ከቤተሰቦቻቸውንም ሆነ ከሕግ አማካሪዎች ጋር አለመገናኘታቸውን በማስረዳት፣ በፍርድ ቤቱ ካገኟቸው የሕግ አማካሪዎች ጋር እንዲመካከሩ ፍርድ ቤቱ አምስት ደቂቃ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀው ፍርድ ቤቱ ፈቅዶላቸዋል፡፡ ተመካክረውም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የተጠረጠሩበት ወንጀል ከሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ያዳመጡት እነ አቶ ዳዊት ኢትዮጵያ በጠበቆቻቸው አማካይነት በሰጡት ምላሽ፣ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በቢሮና በቤታቸው ብርበራ ተካሂዶ የተገኘው ማስረጃ በሙሉ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡
ወንጀሉ የተፈጸመው መቼ እንደሆነ እንዳልተገለጸላቸውና ተፈላጊው ነገር ሰነድ መሆኑን፣ እሱም በመርማሪው እጅ እንደሚገኝ በመጠቆም የዋስትና መብታቸው ተከብሮ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ የተወሰኑት ተጠርጣሪዎች ተራ ሠራተኛ መሆናቸውን በማስረዳት፣ ሌሎች ከተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ጋር የሚያገናኛቸው ጉዳይ እንደሌለ በመግለጽ በዋስ እንዲፈቱ አመልክተዋል፡፡ የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት አባል መሆናቸውንና ያለመከሰስ መብት እንዳላቸው ያመለከቱ ተጠርጣሪም ነበሩ፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ተጠርጣሪዎቹ ባቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ላይ በሰጠው ምላሽ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢፈቱ ያልሰበሰቡትን ማስረጃ ሊያጠፉባቸው የሚችሉ መሆናቸውን፣ ቃል ያልተቀበሏቸውን ምስክሮች በማባበልና በማስፈራራት ሊያጠፉባቸው እንደሚችሉ በማስረዳት፣ የዋስትና ጥያቄውን ተቃውመዋል፡፡ ያለመከሰስ መብት እንዳላቸው ያመለከቱት ተጠርጣሪን በሚመለከትም፣ የአዲስ አበባ ከተማ ማቋቋሚያ ቻርተር ያለመከሰስ መብት የሚፈቅደው ለማዕከል ተመራጮች በመሆኑ ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡
እነ አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ ግንቦት 5 ቀን 2005 ዓ.ም. ሲቀርቡ እነሱም ቀርበው ጊዜው በመምሸቱ በአዳር ለግንቦት 6 ቀን 2005 ዓ.ም. የተቀጠሩ ቢሆንም፣ ከቤተሰብም ሆነ ከሕግ አማካሪ ጋር አለመገናኘታቸውን ለፍርድ ቤት በማስረዳታቸው፣ ለግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም. ከሕግ አማካሪዎች ጋር ተመካክረው እንዲመጡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠው በእነ አቶ መሐመድ ኢሳ መዝገብ ለቀረቡ ስድስት ተጠርጣሪዎች እንደነበር ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም. መርማሪ ቡድኑ ‹‹በስህተት አላቀረብናቸውም›› በማለቱ ፍርድ ቤቱ ለሦስተኛ ጊዜ ለግንቦት 12 ቀን 2005 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ጥብቅ ትዕዛዝ በመስጠቱ ሊቀርቡ ችለዋል፡፡
ሌሎች በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል እነሱም ከመጠርጠራቸው በተጨማሪ አስተዳደራዊ ሥራን ሽፋን ያደረገና በኔትወርክ የተሠራ ወንጀል መሆኑንም መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ ጠበቆቻቸው መርማሪ ቡድኑ ያቀረበው የምርመራ ሥራ ከሳምንት በፊት ያቀረበውን መሆኑን በመጥቀስ፣ ተጠርጣሪዎቹ በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችም ሆነ በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ስለሚፈቀድላቸው ተከብሮላቸው እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡
ዋስትና የሚፈቀደው በልዩ ድንጋጌ መሆኑንና ሲተረጐምም ተጠርጣሪውን በሚጠቅም ሁኔታ በጠባቡ መሆኑን በመጥቀስ፣ የዋስትና መብት እንዲከበርላቸው በተደጋጋሚ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
የአቶ መሐመድ ኢሳ ጠበቃ ለፍርድ ቤቱ የተለየ ማመልከቻ እንዳላቸው በማመልከት፣ ደንበኛቸው ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት እስከ ስምንት ሰዓት በመርማሪዎች እየተወሰዱ ከፍተኛ ድብደባ እንደሚፈጸምባቸውና በግዳጅ ቃል እንዲሰጡ እየተገደዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኢሰብዓዊ ድርጊት መፈጸሙ አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ፣ በግዳጅ እንዲሰጥ የተደረገው ቃል ውድቅ ተደርጐ፣ ለኮሚሽኑ መርማሪዎች በድጋሚ ቃላቸውን እንዲሰጡ እንዲታዘዝላቸው ጠበቃው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ሌላው ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡት አቤቱታ ከተጠረጠሩበት ወንጀል ጋር ያልተያያዘ ነገር ግን ሁሉም የጉምሩክ ሥርዓት የተፈጸመባቸውና ወደ አገር ውስጥ መግባት ያለባቸው ዕቃዎች ሰነድ ከሌሎች ሰነዶች ጋር እንደተወሰደ ተናግረው፣ ሰነዱ ለአስመጪዎቹ እንዲሰጣቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ግን የሁሉንም የተጠርጣሪዎች አቤቱታና ማመልከቻ በመቃወም ለቀረው የምርመራ ሥራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
የግራ ቀኙን የቃል ክርክር ሲያዳምጥ የቆየው ፍርድ ቤቱ፣ የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን የጠየቀውን ተጨማሪ 14 ቀናትና ተጠርጣሪዎቹ የጠየቁትን የዋስትና መብት በሚመለከት በሰጠው ትዕዛዝ፣ በመርማሪ ቡድኑ የቀረበው የተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ውስብስብ መሆኑን ፍርድ ቤቱም እንዳመነበት በመግለጽ የ14 ቀናት ጊዜውን መፍቀዱን ገልጿል፡፡
በተጠርጣሪዎች ላይ ደርሷል ስለተባለው በግዳጅ ቃል እንዲሰጡ የማድረግና የድብደባ ድርጊት ኮሚሽኑ አጣርቶ ሪፖርት እንዲያደርግ፣ ከቤተሰብና ከሕግ አማካሪዎች ጋር ማገናኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት በመሆኑ ኮሚሽኑ እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ በመስጠት፣ ሁሉም ተጠርጣሪዎች ግንቦት 19 ቀን 2005 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በእነ መልካሙ እንድሪያስ መዝገብ የቀረቡት አራት ተጠርጣሪዎች ግን ግንቦት 23 ቀን 2005 ዓ.ም. እንዲቀርቡ አዟል፡፡
በአጠቃላይ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን በቁጥጥር ሥር አውሎ ፍርድ ቤት ያቀረባቸው ተጠርጣሪዎች፣ በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የምርመራ መዝገብ 7፣ በእነ አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ መዝገብ 12፣ በእነ መሐመድ ኢሳ መዝገብ 6፣ በእነ አቶ ዳዊት ኢትዮጵያ መዝገብ 7፣ በእነ አቶ አምባውሰገድ አብርሃ መዝገብ 11፣ በእነ አቶ ተመስገን ሥዩም መዝገብ 7 እና በእነ አቶ መልካሙ እንድሪያስ የምርመራ መዝገብ 4 በድምሩ 54 ተጠርጣሪዎች ናቸው፡
No comments:
Post a Comment