‹‹ዘ ማንዴላስ ገን›› በሚል ስያሜ የሚሠራው ዘጋቢ ፊልም በደቡብ አፍሪካው ‹‹ዲቪ8›› እና በእንግሊዝ ‹‹ቢር ኸርት ሊሚትድ›› የፊልም ኩባንያዎች ትብብር በእንግሊዝና በደቡብ አፍሪካ ቀረፃው ከተገባደደ በኋላ፣ የዚህ ፊልም ታሪክ እምብርት በሆነችው በኢትዮጵያ የመጨረሻው ቀረፃ ሊደረግ ነው፡፡
ቀረፃውን ለማከናወን የሚያስችለውን የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ የፊልሙ ፕሮዳክሽን ማኔጀርና የፕሮዲዩሰሮች ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ ከፖሊስ ኮሚሽን ባለሥልጣናት፣ ከታሪክ ምሁራን፣ ከአርቲስቶች፣ ከታዋቂ ሰዎችና ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ከፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ሐሰን ሺፋ ጋር በመሆን የደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ወታደራዊ ሥልጠና በወሰዱበት ኮልፌ በሚገኘው የፖሊስ ማሠልጠኛ ተገኝተው ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በጉብኝቱም ወቅት ማንዴላ ሥልጠና ሲያደርጉበት የነበረበትን ሜዳ፣ የሚያርፉበትን ክፍልና የቦክስ ልምምድ የሚያደርጉበትን ሥፍራ አይተዋል፡፡
ማንዴላ ያርፉበት በነበረበት ክፍል ውስጥም የቡና ማፍላት ሥርዓት መካሄዱን ‹‹ዘ ማንዴላስ ገን›› ፊልም በኢትዮጵያ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራ የሚሠራው የርዕዮት ኪነ ጥበብና ፕሮሞሽን የራዲዮ ፕሮግራም ዝግጅት ባልደረባ አቶ ቴዎድሮስ ፀጋዬ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልጸዋል፡፡ በተለይ ደቡብ አፍሪካውያንና እንግሊዛውያንን ያቀፈው ቡድን አባላት ቅዳሜ ዕለት በሒልተን ሆቴል የታሪክ ምሁራን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ አርቲስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ የባህልና የቅርስ ኤክስፐርቶችና ትምህርታቸውን በደቡብ አፍሪካ የተከታተሉ ኢትዮጵያውያን ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ውይይት አድርጓል፡፡
ማንዴላ ለወታደራዊ ሥልጠና በኢትዮጵያ ውስጥ በነበሩበት ወቅት የነበሩ፣ ታሪኩን የሚያውቁ፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውና ይህን በተመለከተ ማንኛውም ዓይነት የምስል፣ የጽሑፍና የድምፅ መረጃዎች ያሉዋቸው መንግሥታዊ አካላትና ግለሰቦች ትብብር እንዲያደርጉ የተጠየቀ ሲሆን፣ በውይይቱም ወቅት በፊልሙ ላይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እንዴት ነው መገለጽ ያለባቸው የሚለው የታሪክ ባለሙያዎችንና ሌሎች ተሳታፊዎችንም አወያይቷል፡፡
‹‹ማንዴላስ ገን›› ፊልም በኢትዮጵያ አስተባባሪና ተወካይ የሆኑት የታይኮን ሪል ስቴት ባለቤት አቶ አሰፋ ገብረ ሚካኤል በውይይቱ ወቅት፣ ‹‹በተቻለ መጠን የታሪክ ሽሚያና መፋለስ ሳይኖርበት፣ ያሉንን መረጃዎች በጥንቃቄ በመመርመርና በማጠናቀር ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ በፀረ አፓርታይድ ትግል፣ በአፍሪካ፣ በአፍሪካ አሜሪካውያንንና በአጠቃላይ በሰው ልጆች ነፃነት ትግል ታሪክ ውስጥ የነበራት አዎንታዊና ታላቅ የሆነ ታሪካዊ ሚና በሚገባ በፊልሙ ውስጥ እንዲገለጽ ትልቅ ጥንቃቄ እንደርጋለን፤›› ሲሉ ለውይይቱ ተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡
አቶ አሰፋ በአንድ ወቅት ቢቢሲ ባዘጋጀው ‹‹ዘ ብሉ ናይል›› በሚለው ጥናታዊ ፊልም ውስጥ በኢትዮጵያ በኩል አስተባባሪና ተወካይ መሆናቸውን አስታውሰው፣ በዚህ ፊልም ውስጥ የናይል ወንዝ መነሻና ከውኃው ከ85 በመቶ በላይ ድርሻ በማበርከት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካላት ኢትዮጵያ ይልቅ፣ ጉልህ ድርሻ የተሰጣት ግብፅ መሆኗን እንዳላስደሰታቸው ቅሬታቸውን በመግለጽ፣ በዚህ ወቅት ግን እንዲህ ዓይነቱ ስህተት ዳግም እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የውይይቱ መሪ የነበሩት የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ወዳጆች ማኅበር አስተባባሪ ዶክተር ብርሃኑ ግዛው፣ ‹‹የዚህ ውይይት አስፈላጊነትም እንዲህ ዓይነቱ የታሪክ ሽሚያና ኢትዮጵያችንን ለተቀረው ዓለም አኮስሶ የሚያሳይ ስህተት እንዳይኖር ከወዲሁ ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት ለማድረግ የተጀመረ ውይይት ነው፡፡ ይህ ውይይትና የሐሳብ ልውውጥ ወደፊትም ፊልሙ ተቀርፆ እስኪያበቃ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ በሒልተን ሆቴል በተካሄደው ውይይት የታሪክ ምሁራን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ አርቲስቶች፣ የፊልም ባለሙያዎች፣ ሙዚቃ አቀናባሪዎች፣ የባህል ኤክስፐርቶች፣ ታሪክ አዋቂ የሆኑ የዕድሜ ባለፀጋዎችና ሌሎችም በፊልሙ ሥራ ላይ የራሳቸውን የሆነ ሙያዊ ድርሻቸውን በመወጣት ፊልሙ በትክክል የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህል፣ ሥርዓትና ትውፊት በጠበቀና በሚያንፀባርቅ ሁኔታ እንዲሠራ ከወዲሁ ጥረት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡ ማክሰኞ ዕለትም በብሔራዊ ቴአትር ለዚሁ ፊልም ፕሮዲዩሰሮችና ማኔጀሮች፣ በኢትዮጵያ የፊልሙ አስተባባሪና ተወካይ የሆኑት አቶ አሰፋ ገብረ ሚካኤል ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የዚህ ፊልም ፕሮዲዩሰሮች ቡድን በኢትዮጵያ በተደረገለት አቀባበልና እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ ድርጅቶችና ሌሎችንም ማመስገኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፊልሙ ቀረፃ ታሪካዊ ጥናቶች ዳሰሳ የመጀመሪያ ሥራው አመርቂ መሆኑን የገለጹት የቡድኑ አባላት እንግሊዛዊው የፊልም ዳይሬክተር ጆን አርቪን፣ ፕሮዲዩሰር ክሌሬ ኢቫንስና እንዲሁም ደቡብ አፍሪካዊው ፕሮዲዩሰር ጄረሚ ናታን ይህ ፊልም እስከሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ ድረስ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡ ፊልሙ በዋሽንግተን ዲሲ በሚቀጥለው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሚገኙበት ለኔልሰን ማንዴላ ክብር በሚቆመው ሐውልት ምረቃ ላይ እንደሚቀርብ አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከማንዴላ የነፃነት ትግል ሕይወት ጋር ያላትን ቁርኝት በሚመለከት እየተሠራ ባለው ፊልም ላይ አስተባባሪ የሆነችው ወጣቷ ደቡብ አፍሪካዊት ሞሮባ ናካዌ ከሪፖርተር ጋር ባደረገችው ቆይታ እንዲህ ነበር ያለችው፡፡ ‹‹… እኔም ሆንኩ አብዛኛው ወጣት ደቡብ አፍሪካዊ ትውልድ የዛሬውን የነፃነት አየር እንድንተነፍስ፣ ለዚህ ክብርና ነፃነት ያበቁን አባቶቻችን የከፈሉትን የመስዋዕትነት ታሪክና ተጋድሎ እምብዛም አናውቅም፡፡ ስለዚህ በረዥሙ የፀረ አፓርታይድ የነፃነት ትግልና በዚያን ቀውጢ ወቅት አብረውን የቆሙ አገሮችና ሕዝቦች ታሪካቸው መነገር ስላለበት ነው ይህን ፊልም መሥራት አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው፤›› ስትል አስረድታለች፡፡
Source: Ethiopian Reporter
No comments:
Post a Comment