Thursday, May 30, 2013

መንግስት በጉምሩክ ባለስልጣናት ላይ የወሰደውን እርምጃ ወደ ሌሎች ባለስልጣናት ማዞር ፈርቷል ተባለ



ግንቦት ፳፪ (ሀያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-መንግስት በቅርቡ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሥራ ኃላፊዎችና ባለሃብቶች ላይ የወሰደውን እርምጃ ወደሌሎች በሙስና የሚጠረጠሩ ባለስልጣናት ለማስፋት ፍርሃት እየታየበት መሆኑን ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ በአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ከኢትዮምህዳር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልለስ ገልጸዋል፡፡
ዶክተሩ ግንቦት 20 ለወጣው ኢትዮምህዳር ጋዜጣ እንደተናገሩት “በሙስና ተከስሰው ወደወህኒ የወረዱት የአንድ መ/ቤት ሠራተኞችና ከእነርሱ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሐብታሞች ናቸው፡፡ የሙስናው ደረጃ በጣም የተስፋፋና የአገሪቱን አብዛኛውን ተቋማት ያዳረሰ ለመሆኑ ከኦዲት ሪፖርቱ ፍንጭ አግኝተናል፡፡ ይሁንና የክሱን ውስንነት በምናይበት ጊዜ ከጉምሩክ ውጪ ያሉ ስማቸው በሙስና የሚነሳ ተቋማትን ለመንካት ፈራ ተባ የተባለ ይመስለኛል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ዶ/ር ዳኛቸው አያይዘውም በአንድ ስርዓት ውስጥ የፖለቲካዊና የሕግ አይነኬዎች ከኖሩ ስርዓቱ ትልቅ ችግር ውስጥ የወደቀ መሆኑን እንደሚያሳይ ጠቁመዋል፡፡
መንግስት በራሱ ውስጥ ሙስና መኖሩን ማመኑ በራሱ ትልቅ ነገር መሆኑን ዶ/ር ዳኛቸው ጠቁመው ነገር ግን መንግስት በሙስና ዙሪያ የሚሰጠውን መግለጫ ዜጎች አሜን ብለው መቀበል እንደሌለባቸው መክረዋል፡፡
“በአሁኑ ወቅት እንደሚታየው ጥቂት ሰዎችን ከተወሰኑ ተቋማት በመውሰድ በማስር ብቻ ችግሩ የግለሰቦች የሞራል ዝቅጠት አድርጎ የማቅረብ ነገር እያየን ነው፡፡ ነገር ግን በኔ አስተያየት ሙስናው ከስርዓቱ ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው” ብለዋል፡፡
“ሁሉም ሹመኞች ሙሰኞች ስለሆኑ በምን የሞራል መመዘኛ አንዱ ከሳሽ ሌላው ተከሳሽ ይሆናል” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “ሁላችንም የሰው ልጆች እስከሆንን ድረስ እርስበርሳችን ተካሰን ለመተራረም እንሞክራለን እንጂ ከሰማየሰማያት የመላዕክት ዐቃቤ ሕግ አምጥተን ችሎት ልናቆም አንችልም” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በተያያዘም ያለፉት 22 ዓመታት የኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን ሕዝቡን ፍርሃት ውስጥ እንደጣለው ዶ/ሩ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “…ልክ የገንዘብ የመግዛት አቅም እንዳሽቆለቆለው ሁሉ የሕዝቡም በነጻነት የመናገር ድፍረት እየወረደ መጥቷል” በማለት አስረድተዋል፡፡
ይህንን አባባላቸውን በምሳሌ ሲያስረዱ “ ለሶስት አመታት ያህል በሕዝብ ትራንስፖርት ስገለገል ቢያንስ ቢያንስ ከምኖርበት አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ስድስት ኪሎ ድረስ
ስሄድና ስመለስ ስድስት ታክሲዎችን ስለምጠቀም ከበርካታ ሰዎች ጋር የመገናኘት ዕድል ነበረኝ፡፡ ይህንኑ ዕድል ተጠቅሜ አንዳንድ የፖለቲካ ጨዋታዎችን ስጀምር አብረውኝ የሚጓዙ ሰዎች ለማናገር ወይንም ከእኔ ጋር ለመወያየት እንደሚፈሩ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ይህ የፍርሃት ድባብ በታክሲ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሬስቶራንት፣ በቡና መጠጫ ስፍራዎች፣ በአጠቃላይ በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች የሚስተዋል መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ምናልባት እዚህ ላይ
የሶስዮሎጂ መምህራን አቀራረብህ ሳይንሳዊ አይደለም፣በቂ መረጃ የለህም ሊሉ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን በተለይ ከምርጫ 97 በኃላ የአፈናና የፍርሃት ድባቡ እንደተጠናከረ ከመንግስት ውጪ ያሉ ዜጎች እንደሚመሰክሩ ጥርጥር የለኝም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደዶ/ር ዳኛቸው ገለጻ ሕዝብን የማስፈራራትና የማቀብ ስርዓት በትክክል እየሰራ ነው የሚባለው ሕዝቡ ይህንን አድርግ፣አታድርግ ተብሎ ሳይታዘዝ ከፍርሃት በመነጨ ራስን ማገድ ሁኔታ ላይ ሲወድቅ ነው በማለት አገሪቱ የምትገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ ዳስሰዋል፡፡

No comments:

Post a Comment