Wednesday, May 1, 2013

መንግስት በድምጻችን ይሰማ አስተባባሪዎች ላይ በድጋሜ ዘመቻ ሊከፍት ነው


ሚያዚያ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኢሳት ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ባገኘው አስተማማኝ መረጃ  ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ድምጻችን ይሰማ በማለት በየሳምንቱ የሚያቀርቡት ተቃውሞ የስርአቱን ህልውና እየተፈታተነው በመምጣቱ መንግስት ችግሩን በድርድር ከመፍታት ይልቅ በከፍተኛ እና መካከለኛ እንዲሁም በቀበሌዎች አካባቢ ያሉ የተቃውሞ አስተባባሪዎችን በመለየት ሰብስቦ ለማሰር እና ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አላቸው የሚል ክስ ለመመስረት ማቀዱ ታውቋል።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ታማኝ የኢህአዴግ ካድሬዎች በቅርቡ በጦላይ እና በብርሸለቆ ለዚሁ ተግባር የሚያገለግል ስልጠና ለመውሰድ እንደሚገቡ ታውቋል። ከህብረተሰቡ፣ ከቀበሌ አመራሮች እና ከአባላት የሚውጣጡት ሰልጣኞች ስልጠናቸውን እንደጨረሱ የሙስሊሙን እንቅስቃሴ ይመራሉ የሚሉዋቸውን ሰዎች በመለየት ለዚህ ስራ ተብሎ ለተቋቋመው አካል ሪፖርት ያደርጋሉ።
መንግስት ልዩ ትኩረት ይደረግባቸዋል ብሎ የዘረዘራቸው አካላት የዩኒቨርስቲ እና የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ፣ነጋዴዎች እና በየአካባቢው የእስልምና ትምህርት በሚሰጥባቸው መደርሳዎች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ልዩ ትኩረት የተጣለባቸው የድምጻችን ይሰማ አመራሮች በድብቅ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑንም ከምንጫችን ለመረዳት ተችሎአል።
ለወደፊቱ በሚያዙት አመራሮች ላይ የግንቦት7 ቅጥረኞች፣ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙትን ደግሞ የኦነግ ቅጥረኞች እና የተለያዩ አክራሪዎች መናጆ በመሆን ለህገምንግስታዊ ስርአቱ አደጋ በመደቀን ክስ ለመመስረት መታቀዱንም ለማወቅ ተችሎአል።
መንግስት በአቶ አቡበክር አህመድ የሚመራው የድምጻችን ይሰማ ኮሚቴ አባላትን ካሰረ በሁዋላ የሙስሊሞች እንቅስቃሴ ሊበርድ ይችላል የሚል እምነት የነበረው ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ እምነቱ ወደ ተግባር ሲለወጥ አልታየም። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ጊዜ ተቃውሞውን በየአካባቢው ያስተባብራሉ በማለት የጠረጠራቸውን ሙስሊሞች በማጥናት በድጋሜ ለማሰር በዝግጅት ላይ ነው።
የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች በሙስሊሙ ጉዳይ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ መግባታቸውን ከከፍተኛ ባለስልጣናቱ ያገኘነው መረጃ የሚያመለክት ሲሆን፣ የሀይማኖት እንቅስቃሴው ቀስ በቀስ ወደ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ሊለወጥ እና መላውን ህዝብ ያሳተፈ እንቅስቃሴ ሊጀመር ይችላል የሚል ድምዳሜ ላይ እየደረሱ መምጣታቸውን ለማወቅ ተችሎአል። ችግሩን ውስብስብ ያደረገው ደግሞ አብዛኞቹ የኢህአዴግ ሙስሊም አባላትና ደጋፊዎች የድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴን መደገፋቸው ነው።

No comments:

Post a Comment