“የተከበራችሁ ባለስልጣናት ሆይ፡ እባካችሁ ጉድጓዱን አትቆፍሩ፣ ከቆፈራችሁም ጥልቅ አድርጋችሁ አትቆፍሩት እናንተም ልትገቡበት ትችላላችሁና ” ብለን ብንመክር ብናስመክር አልሰማ ብላችሁን ይሀው ዛሬ በቆፈራችሁት ጉድጓድ ውስጥ ጠልቃችሁ ስትገቡበት እያየን ነው ፡፡ በደረሰባችሁ የመብት ጥሰት ስትማረሩ እና ቤተሰቦቸችሁም ምን ያህል በስነ ልቦና እንደተጎዱ ስትነግሩን ፣ የእኛዎቹን ኮሚቴዎች ስቃይንና እሱን ተከትሎ የእኛም ስነ ልቦና ምን ያህል ተጎድቶ እንደነበር ስላያችሁልን በመጠኑም ቢሆን ደስ ብሎናል ፡፡ እንደ እናንተ ልጆችና ቤተሰቦች ሁሉ የኛዎቹ ንፁሃን ኮሚቴዎቻችን ልጆችና ቤተሰቦችም የከፋ ስነልቦናዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል ፡፡ እናንተ ዛሬ የፍርድ ቤት ወረቀት ሳይያዝ ቤታችሁ መበርበሩን ለፍርድ ቤቱ አቤት ከማለታችሁ ቀደም ብሎ የበርካታ ሙስሊም ኢትዮፕያዊያን ቤቶች በውድቅት ሌሊት እናንተ ባሰማራችኋቸው ጭንብል ለባሽ “ወሮበሎች “ ንብረቶቻቸው ተዘርፈዋል ፣ አካላዊም ጥቃት ደርሶባቸዋል ፡፡ የእናንተው ስራ ውጤት የሆነው እና ዛሬ እያማረራችሁት ያለው ፍትህ ስርዐት ትላንት ምንም ያላደረጉ እናቶችና ሴቶችን አስሮ አሰቃይቷል፡፡ አንዲት ወላድ ሴት (ከአራስ ቤት ከወጣች 5 ወር ቢሆናት ነው) በአንዋር መስጂድ ተገኝተሻል በመርካቶ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ አስረዋት አራስ ልጇ ተርቦ እሪሪ እያለ እያዩት አውሬዎቹ ፖሊሶቻችሁ ልጇን እንኳ እንዳታጠባ የከለከሏት ዘግናኝ ድርጊት ከተፈፀመ አመት እንኳ አልሞላውም ፡፡ እናም ክቡራን ባለስልጣኖቻችን ሆይ ፡ “ የመንግስት ሌቦች ” ተብላችሁ ዘብጥያ በወረዳችሁበት ቅፅበት ከሰብኣዊ መብት ጥሰት ጋር ተያይዞ ያቀረባችሁት አቤቱታ (ለዛውም እናንተ በቤተሰብ አያያዝ አይነት ተይዛችሁ እንደሆነ ልብ በሉ) ኮሚቴዎቻችንን ጨምሮ ሌሎች ንፁሃን ኢትዮፕያዊያን ላይ ከደረሰው ጋር ሲነጻጸር ምንም ማለት ነው፡፡ ቢሆንም ግን ቢያንስ ቢያንስ ለትዝብት ያህል እንኳ “ ጠፍጥፋችሁ ” የሰራችሁት የፍትህ ስርዐት ምን ያህል ሸውራራ እንደሆነ መታዘባችሁን ወደነዋል ፡፡ የሴራ ፖለቲካ ትኩሳቱን መቋቋም ተስኗችሁ ዛሬ “ በመንግስት ሌቦች ” የዳቦ ስም ዘብጥያ የወረዳችሁ ባለስልጣናት ሆይ እኛ ፍትህ ፍትህ እያልን በአደባባይ ስንጮህ የነበረው ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለእናንተም ፣ ለመላው ሀገራችን ህዝብ ጭምርም እንደነበር አያችሁት አይደል ?
ጠበቆቻችሁ ጋር እንዳትገናኙ መደረጋችሁም ሆነ በፍተሻ ወቅት እናንተው ባሰለጠናችኋቸው “ዋልጌ” የፀጥታ ሰዎች ባደረሱባችሁ ሰብአዊ ጥሰት ሀዘን ቢሰማኝም በኮሚቴዎቻችንና በሌሎች ወንድሞቻችን ላይ፣ በህፃናት ልጆቻቸው ፣ በሚስቶቻቸውና በሚያከብሯቸው ሰዎች ፊት የደረሰባቸውን እንግልት ስናስበው ደግሞ “በሰፈሩት ቁና …” የሚለውን ተረት እንድናስታውሳችሁ ተገደና ል፡፡ ይህን ስል ግን በድላችሁናል እንዲሁም የፍትህ ስርዐቱ በእናንተ የተፈበረከ ስለሆነ ደግ ሆናችሁ ፣ ይበላችሁ አንልም፡፡ ልክ ለኮሚቴዎቻችንና ለሌሎች ኢትዮፕያዊያን እንደምንመኘው ሁሉ ፍትሃዊ የፍትህ አያያዝ እና ፍትሃዊ ፍርድ እንድታገኙ እንመኛለን ፡፡ በእስር ቤት ሆናችሁም ቢሆን ግን “የፍትህ ያለህ ” ጩሀታችንን እንድትቀላቀሉት ግን የትግል ጥሪ እናቀርባለን፡፡ አብራችሁን “ የፍትህ ያለህ፣ ፍትህ ናፈቀን፣ ህግ ይከበር ፣ድምፃችን ይሰማ ” እንድትሉ ዘንድ እንጠይቃችኋለን፡፡ በእስር ቤትም ሆኖ መታገል እንዳለ ከሰላም አምባሰደሮቹ ኮሚቴዎቻችን እንዲሁም ከእነ ርእዮተ አለሙ እና እስክንድር መማር ትችላላችሁ ፡፡
እናንተም ዛሬ ለጊዜው አሳሪ የሆናችሁ ግና ስለነገው የማታውቁ ተረኛ “ ዘብጥያ ወራጆች ”፣ የዛሬ ባላስልጣናት ሆይ ፣ በልካችሁ ጠፍጥፋችሁ የሰራችሁት የመሰላችሁ “ ሸውራራው ” የፍትህ ስርዐት ነገ እናንተንም “ የመንግስት ሌቦች” ብሎ ሊበላችሁ እንደማይችል ምንም አይነት ዋስትና የላችሁምና ዛሬውኑ ከጓደኞቻችሁ በመማር የሀገሪቱ የፍትህ ስርዐት እንዲስተካከል ከአሁኗ ሰዐት ጀምሮ ለራሳችሁ ስትሉ እንድትታገሉ እንመክራለን፡፡ እናንተም ባላችሁበት የስልጣን ኮርቻ ላይ እንዳላችሁ አብራችሁን “ ፍትህ ናፈቀን ፣ ህግ ይከበር ፣ ድምፃችን ይሰማ ፣ ኮሚቴዎቻችን ይፈቱ፣ እነ እስክንድርና ርእዮተ ይፈቱ ” እያላችሁ ድምፃችሁን አሰሙ፡፡ ልብ በሉ ለኛ ብላችሁ አይደለም፡ ለራሳችሁ ስትሉ እንጂ! አለዛ በማንኛውም ሰዐት እንደ ጓደኞቻችሁ ሁሉ አንገታችሁን እያነቁ፣ በራቁታችሁ ዱብዱብ እያስደረጓችሁ ቃሊቲ መውረዳቸሁ ነው፡፡ ከሀገር መኮብለልን አማራጭ አድርጋችሁት ከሆነ እንድትረሱት በዚህ አጋጣሚ እመክራችኋለሁ፡፡ አንድ የውስጥ ወዳጄ የሞያሌም ሆነ የኤርፖርት መንገድ በስውር ጥበቃ እንደታሸገ ሹክ ብሎኛል፡፡ የማሪያም መንገድ እንደሆነ በጁነይዲን ሳዶ አብቅቷል ፡፡ እናም ነግ በኔ ነውና ባላችሁበት የመንግስት ስልጣን ላይ ሆናችሁም ቢሆን “ህግ ይከበር ፣ህግ ይከበር፣ ፍትህ ናፈቀን፣ ድምፃችን ይሰማ፣ ኮሚቴዎቻችን ይፈቱ ፣ እን እስክንድርና ርእዮተ አለሙ ይፈቱ በሉ ” ፡፡ እኛ ከመስጂዶቻችን ሆነን እንቀበላችኋለን፡፡ ህግ ይከበር፣ ኮሚቴዎቻችን ይፈቱ !
No comments:
Post a Comment