ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ አነቡ !
በኢትዮጵያ እንባ እንግዳ ነገር ባለመሆኑ የዶክተሩን ማልቀስ ምን የተለየ ያደርገዋል የሚለኝ አይጠፋም፡፡ነጋሶ በጀርመን አገር የሞቀ ኑሮና የሚያስመካ መተዳደሪያ ነበራቸው፡፡ኢህአዴግ ይዟቸው ከመጣ በኋላም ወደ ቤተመንግስት አስገብቶ በፕሬዘዳንትነት ሰይሟቸዋል፡፡ህገ መንግስቱ ሲረቅም ነጋሶ ከአርቃቂዎቹ አንዱ ነበሩ፡፡እነዚህ ነገሮች ዶክተሩን በአጀብ ለማኖር ከበቂ በላይ ነበሩ፡፡ነገር ግን አንድ ማለዳ ነጋሶ መለስን‹‹መንግስቱ ኃይለማርያምን መሰልከኝ ››በማለት መናገራቸው እንደ ሃጢአት ተቆጥሮባቸው የቤተመንግስት ቆይታቸው ተቀጨ፡፡ከስንብቱ በኋላ የተቆረጠላቸውን ጡረታ እየተቀበሉ አንደበታቸውን በመሸበብ መኖር እንደሚችሉ የሚገባቸው ቢሆንም ነጋሶ በግላቸው ተወዳድረው የህዝብ ድምጽ ማግኘት በመቻላቸው ፓርላማ ገቡ፡፡በዚህ ያልተደሰተው ኢህአዴግ ጡረታቸውን በመንጠቅ የሰጣቸውን የመኖሪያ ቤት ነሳቸው፡፡ምንም ያጡት ነጋሶ ኦነግን ወይም አንዱን የብሄር ድርጅት ይቀላቀላሉ ተብለው ሲጠበቁ ህብረ ብሄራዊ የሆነውን አንድነት ለዴሞክራሲና ፍትህ ፓርቲን ተቀላቀሉ፡፡
ነጋሶ እንባ አውጥተው በአደባባይ ያነቡት ዛሬ ስድስት ኪሎ በሚገኘው ሰበር ሰሚ ችሎት ነው፡፡የፖለቲካ፣የህሊና እና የነጻ ሚዲያው አባላት የተለያየ ኬዝ እየተጋገረባቸው ለእስራት ሲዳረጉ ነጋሶ በቻሉት መጠን ሁሉ በየፍርድ ቤቱ በመመላለስ ጉዳያቸውን ይከታተላሉ፡፡ድርጅታቸው አንድነት እስረኞችን ለማሰብ በየወሩ በሚያደርገው የመታሰቢያ ስነ ስርዓትም በመገኘት ነጋሶን የሚስተካከል አመራር የለም፡፡ዶክተሩ አንዷለም አራጌ፣እስክንድር ነጋ፣ናትናኤልና አበበ ቀስቶ የስር ፍርድ ቤት ያሳለፈባቸው ውሳኔ የህግ ጥሰት አለበት በማለት ለሰበር ሰሚ ይግባኝ ማለታቸው ተቀባይነት በማግኘቱ የተንዛዛውን የፍርድ ሂደት በትእግስት ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡የነጋሶ ተስፋ የተጋባባቸው የህሊና እስረኞቹ ቤተሰቦች፣ወዳጆችና ሌሎች በነጻ ተሰናብተዋል የሚል ቃል ለመስማት በመጓጓት የፍትህ አዳራሹን አጨናንቀዋል፡፡
ፍርደኞቹ ያቀረቡትን መከላከያ በንባብ በማስደመጥ የጀመሩት ዳኛ የአቃቤ ህግን ምላሽ በማስከትል ተገቢ ያሉትን ውሳኔ አስደምጠዋል፡፡የስር ፍርድ ቤት የወሰነውን አጽንተናል በማለት፡፡ይህንን መቋቋም የተሳናቸው ነጋሶ በተቀመጡበት ወንበር ሆነው ስቅስቅ ብለው አንብተዋል፡፡የእስክንድር ባለቤት ሰርካለም ድምጻን ከፍ አድርጋ ‹‹አንተ ንጽህ ነህ እንዲህ ስለተባለ ምንም ሊሰማህ አይገባም››በማለት ጋዜጠኛውን ለማጽናናት ራሷን ስታበረታ በብዙ መከራ ውስጥ ያለፉት ነጋሶ ግን እንባ ቀድሟቸዋል፡፡ወዳጆቼ ፕሬዘዳንት ሲያለቅስ ማየት ምን ስሜት ይፈጥርባችሁ ይሆን?
No comments:
Post a Comment