Tuesday, May 14, 2013

በባህር ዳር የ12 ሰዎችን ህይወት ያጠፋው ግለሰብ አስክሬን ተገኘ


አዲስ አበባ ፣ግንቦት 5 (ኤፍ.ቢ.) በባህር ዳር ከተማ ልዩ ስሙ አባይ ማዶ በተባለ አከባቢ ከትናንት በስቲያ አንድ ግለሰብ  12 ሰዎችን መግደሉ ይታወሳል፡፡
ከስፍራው የደረሰን መረጃ  ግለሰቡ  ሰክሮ እንደነበር ነው የሚያመለክተው ።
የባህር ዳር ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን መምሪያ ሀላፊ ኮማንደር ደረጀ አቻምየለህ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት ፥ ግለሰቡ በውል ባልታወቀ ምክንያት በመንገድ ላይ በከፈተው ተኩስ ከሞቱት 12 ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ሰዎች ክፉኛ ቆስለዋል ።
በሰዓቱም ግለሰቡን በቁጥጥር  ስር ለማዋል ፖሊስ ክትትል ሲያደርግ እንደነበርና  በመጨረሻም ራሱን  በወንዝ ውስጥ በመወርወር መሰወሩን ገልፀው ነበር ።
በአሁኑ ወቅት የግለሰቡ አሰክሬን በአባይ ወንዝ ውስጥ መገኘቱን ፖሊስ ገልጿል ።
ድርጊቱን የፈፀመው ግለሰብ የፖሊስ አባል መሆኑን  የገለፁት  ኮማንደሩ ፥  ድርጊቱን  የፈፀመበት  ምክንያት ግለሰባዊ እንደሆነ አመልክተዋል ።
ትናንት ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ በተፈፀመው ድርጊት ከሞቱት መካከል ሴቶች ፣ ህፃናትና  አዛውንቶች ይገኙበታል ።ከተገደሉት ግለሰቦች መካከልም የሰባቱ የቀብር ስነ ስርዓት በደብረ አባይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን በጋራ  ተፈፅሟል ።
ይህ በእንዲህ  እንዳለ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ግድያውን አስነዋሪ የጭካኔ ተግባር ሲል አውግዞታል ፤  ለሟች ቤተሰቦችም መፅናናትን ተመኝቷል::
በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ  የተገኙት የአማራ  ክልል  ርእሰ መስተዳድር  አቶ አያሌው ጎበዜም የክልሉ መንግስት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል ።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን  በበኩሉ በግለሰቡ ድርጊት ህይወታቸውን ባጡ ዜጎች  ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል ፡፡
በእንዲዚህ አይነቱ  ወንጀልም በህብረተሰቡና በፖሊስ መካከል ለዓመታት የቆየው መልካም ግንኙነትም አይሻክርም ብሏል በመግለጫው  ፡፡
የፖሊስነት ሙያዊ ዲስፕሊን  በጎደላቸው መሰል ፖሊሶችም ይህ አይነት ክስተት ደግም እንዳይፈጠር እንደሚሰራም ያለውን ቁጥርጠኝነት አረጋግጧል ፡፡
ፖሊስ በጉዳዩ ላይ እያደረገ ያለውን ምርመራ እንዳጠናቀቀም ተጨማሪ መረጃ እንደሚሰጥ ነው ያስታወቀው ::

No comments:

Post a Comment