Sunday, March 31, 2013

“የአዲሱ የናይል ሸለቆ ፕሮጀክት” በግብፅ


አሁን በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የግብፅ መሪ ሆስኒ ሙባረክ እ.ኤ.አ በ1997 “New Nile Valley Project” “የአዲሱ የናይል ሸለቆ ፕሮጀክት” በሚል ግዙፍ የሆነውን የሰሐራ በረሃን የማልማት ዕቅድ ነድፈው ያም ዕቅድ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል፡፡ በተያዘለት ዕቅድ ከተከናወነ ይህ ፕሮጀክት እ.ኤ.አ በ2017 ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ እየተጠበቀ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል የማጠናቀቂያ ጊዜው እስከ 2020 ድረስ መሆኑን በቅርብ ጊዜ ከወደ ግብፅ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ፕሮጀክት በዋናነት ሁለት ምዕራፎች ሲኖሩት አንደኛው በሰሜን ምሥራቅ ግብፅ የሚገኘው የአል-ሰላም ቦይ (canal) ፕሮጀክት ነው፡፡ እሱም ውኃ ከዓባይ ግርጌ በመጥለፍ ወደ ሲና በረሃ ማሻገር ነው፡፡
ይህን በማድረግ ብዙ መቶ ሺሕ ሔክታር መሬት በማልማት 750 ሺሕ ግብፃውያንን ለማስፈር ያለመ ነው፡፡ ዋናውና ትልቁ ፕሮጀክት ግን የቶሽካ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ይህም የደቡብ ምዕራብ ግብፅ በረሃን ለማልማት ያቀደ ፕሮጀከት ነው፡፡ በግብፃውያኑ ዘንድ ይህ ፕሮጀክት አሁን ባለው ሁኔታ እ.ኤ.አ 2020 ያልቃል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ፕሮጀክቱ በዋናነት አዲስ ግብፅን በበረሃው ለመፍጠር ያቀደ ሲሆን፣ የተለያዩ በርካታ የውኃ ቦዮችንና የውኃ መምጠጫ ፓምፖዎችን በመገንባት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህን በማደረግ በረሃውን በማልማት ወደ ሦስት ሚሊዮን ግብፃውያንን የማስፈር ዕቅድ አላቸው፡፡ እንደ ግብፃውያኑ ከሆነ ይህ ፕሮጀክት ውኃውን የሚያገኘው በናይል ላይ ከተሠራው የአስዋን ግድብ ጀርባ ከሚገኘው የናስር ሐይቅ ነው፡፡ ግብፃውያኑ ይህን ሥራ የትኞቹንም የላይኛውን የተፋሰስ አገሮች ሳያናግሩ ሲሠሩት ውኃውን ከየት እንደሚያመጡት ያሰቡ አልመሰሉም፡፡ እነሱ እ.ኤ.አ በ1959 ከሱዳን ጋር የተፈራረሙት በሌሎቹ አገሮች ውድቅ የተደረገው “ስምምነት” ለራሳቸው በሰጡትና በመደቡት 55.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ራሽን/ኮታ መሠረት “ያላቸውን” ውኃ ለመጠቀም በማሰብ ነው፡፡
ሆኖም ግን ይህ ኮታ በሌሎቹ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ዘንድ ተቀባይነት ስለሌለው ግብፃውያኑ ውኃውን ከየት እንደሚያመጡት አሁንም ግልጽ አይደለም፡፡
እንግዲህ የሳዑዲ ዓረቢያ ሚና በዚህ ፕሮጀክት ላይ ምንድን ነው? ስንል ታላቅ ኢንቨስትመንትን እናገኛለን፡፡ የሳዑዲው ልዑል አል ዋሊድ ቢን ጣላል ቢን አብዱላዚዝ አልሳዑድ “ዘ ኪንግደም አግሪካልቸራል ዴቨሎፕመንት” የተሰኘ ኩባንያ ባለቤት ሲሆኑ፣ ግብፅ ውስጥ በጥቅሉ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያንቀሳቅሳሉ፡፡ በቶሽካ ፕሮጀክት ደግሞ ከ10 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት ተረክበው የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ለማምረት ከግብፅ የውኃና የመስኖ ልማት ሚኒስቴር ጋር ተፈራርመዋል፡፡ በየዓመቱም በሚሊዮኖች ለዚሁ የቶሽካ ፕሮጀክት አካል ለሆነው መሬት እንደሚያፈሱ ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ግብፅ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ያሉት የሳዑዲ ቤተሰብ የሆኑት የንጉሡ ዘመድና ልዑሉ እንጂ ከኢትዮጵያዊ እናት የተገኙት ሼክ አል አሙዲ አይደሉም፡፡ ይህም ማለት ለሳዑዲ ዓረቢያ ቤተ መንግሥትም ሆነ ለምክትል መከላከያ ሚኒስትሩ የሚቀርቡት ሼክ አል አሙዲ ሳይሆኑ ልዑል አል ዋሊድ ቢን ጣላል ናቸው፡፡ ስለዚህ የምክትል መከላከያ ሚኒስትሩ ንግግር ከዚህ አንፃርም ሊታይ ይችላል፡፡
ዓባይ ኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ ከሚለው ፅሁፍ የተወሰደ
በዘሪሁን አበበ ይግዛው
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው zerihun.yigzaw@graduateinstitute.ch ማግኘት ይቻላል፡፡

No comments:

Post a Comment