Sunday, March 10, 2013

ኢሕአዴግ ከ15 የውጭ ፓርቲዎች ጋር የጋራ ጉባዔ ሊያካሂድ ነው



-    የግንባሩ መተዳደሪያ ደንብ አይሻሻልም

ኢሕአዴግ 9ኛ ጉባዔውን ምክንያት በማድረግ ከተመረጡ 15 የውጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለመማከር የጋራ ጉባዔ ሊያካሂድ ነው፡፡
“በመለስ አስተምህሮ ጠንካራ ድርጅትና የልማት ኃይሎች ንቅናቄ ህዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 14 እስከ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላ በሚካሄደው 9ኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ፣ የግንባሩ ሪፖርትን በዋነኛነትም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ግማሽ አፈጻጸም፣ የግንባሩን የፖለቲካና የድርጅት ሥራዎች በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢሕአዴግ 9ኛ ጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ የሕዝብ ግንኙነት አባል አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው ባለፈው ረቡዕ በኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ጉባዔው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን በሚዘክሩ በፎቶ ኤግዚቢሽን፣ በሙዚቃዊ ድራማና በተያዩ ዝግጅቶች ታጅቦ የሚከበር መሆኑን፣ የግንባሩ መተዳደርያ ደንብ ይሻሻላል ተብሎ ስለሚናፈሰው ወሬ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ “በዚህ ላይ እስካሁን የተያዘ አጀንዳ የለም፤” ብለዋል፡፡ 


እንደ አቶ ሴኩቱሬ ገለጻ፣ የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ታዋቂ ግለሰቦች በጉባዔው የተጋበዙ ሲሆን፣ በጉባዔው መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ከ2,500 በላይ ተሳታፊዎች ይገኛሉ፡፡

ኢሕአዴግ በአፍሪካ፣ በእስያና በምዕራብ አውሮፓ የሚገኙ 15 የውጭ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በጉባዔው እንዲሳተፉ የጋበዘ ሲሆን፣ እርስ በእርስ የሚመካከሩበትና በርዕዮተ ዓለም ላይ የሚወያዩበት የአንድ ቀን ጉባዔ ያዘጋጃል፡፡ ተጋባዥ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ የቀረበ አመለካከት ያላቸው ናቸው፡፡ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግሬስ (ደቡብ አፍሪካ)፣ የሱዳን ብሔራዊ ኮንግሬስ፣ የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ንቅናቄ፣ የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር፣ የኡጋንዳ ብሔራዊ ተቃውሞ እንቅስቃሴ፣ የታንዛንያ ቻማ ቻማ ፓርቲ፣ የየመን ሕዝቦች ኮንግሬስ ፓርቲ፣ የህንድ ብሔራዊ ኮንግሬስና የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ፣ የኖርዌይ ሌበር ፓርቲ፣ የብራዚል ሌበር ፓርቲና የጀርመን ሶሻሊስት ዲሞክራቲክ ፓርቲ ይገኙባቸዋል፡፡

በጉርብትና ከተጋበዙት ከደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳንና ከየመን ፓርቲዎች በስተቀር አብዛኛዎቹ ለግንባሩ የቀረበ አስተሳሰብ ያላቸው ሲሆኑ፣ ተሳታፊ የሆኑትም ከጋራ የምክክር ጉባዔው ልምድ ለመቅሰምና ለመማማር በማለም መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ እንዲሁም ከአሥራ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በላይ አካቶ የያዘው የኤርትራ ተቃዋሚዎች ግንባር (ኪዳን) በጉባዔው እንዲሳተፍ ተጋብዟል፡፡

በጉባዔው ኢሕአዴግ በሚከተለው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የተገኘውን ድልና ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ለውይይት በማቅረብ የፓርቲዎቹን ጉባዔ መነሻ ለማድረግ ታስቧል፡፡ ከፓርቲዎች ጋር በቀጣይነት መደበኛ ግንኙነት ስለሚደረግበት ሁኔታም ይመከርበታል ተብሏል፡፡

ጉባዔው በፎቶ አግዚቢሽን፣ በሙዚቃዊ ድራማና በተለያዩ ዝግጅቶች ለማድመቅ ዝግጅቱ የተጠናቀቀ መሆንና የአፍሪካ ኅብረት ምሥረታ 50ኛ ዓመት በአዲስ አበባ የሚከበርበት ወቅትም በመሆኑ፣ ጉባዔው የፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ የሚንፀባረቅበት እንደሚሆን አቶ ሴኩቱሬ ተናግረዋል፡፡

አራቱ የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ከጉባዔው አንድ ሳምንት ቀደም ብለው በተናጠል የየራሳቸውን ጉባዔ ያካሂዳሉ፡፡ እያንዳንዳቸው 250 ተሳታፊዎች ለግንባሩ ጉባዔ መርጠው የሚልኩ ሲሆን፣ እንዲሁም ደግሞ አራቱም ፓርቲዎች እያንዳንዳቸው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን መርጠው ይልካሉ፡፡

No comments:

Post a Comment